October 30, 2019

Source: https://fanabc.com

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 19 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኦቶማን ስርወ መንግስት በአርሜኒያውያን ላይ የተፈፀመውን ግድያ በዘር ማጥፋት ፈረጀ።

ምክር ቤቱ በፈረንጆቹ ከ1915 እስከ 1923 በአርሜኒያውን ላይ በኦቶማን ስርወ መንግስት የተፈፀመውና 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎች ህይወታቸውን ያጠቡትን ጥቃት በማውገዝ በዘር ማጥፋት ፈርጆታል።

አባላቱ ከክፍለ ዘመን የተፈጸመውን ግድያም 405 ለ11 በሆነ ድምፅ በዘር ማጥፋት ፈርጀውታል።

የቱርክ መንግስት በበኩሉ የሚቀርብበትን ታሪካዊ ወቀሳ በመቃወም ክሱ በወቅቱ ህይወታቸውን ያጡ ቱርካውያንን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ አይደለም ብሏል፡፡

ምክር  ቤቱ ያሳለፈው ውሳኔ በውስጡ ሶስት ነገሮችን የያዘ ሲሆን እነዚህም የአሜሪካ መንግስት የዘር ፍጅቱን ያስባል፣ የዘር ፍጅቱን የሚቃወሙ ተግባራትን ያወግዛል እንዲሁም የዘር ፍጅቱን በተመለከት ህብረተሰቡን ያስተምራል ነው የተባለው፡፡

የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶግሉ የአሜሪካ ምክር ቤት ውሳኔ ሃሳብ ታሪክን በፓለቲካዊ ውሳኔ የበዘበዘ ሲሉ ወቀሳ አቅርበዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተላለፈው ውሳኔ ቱርክ  በሰሜን ሶሪያ በሚንቀሳቀሱት የኩርድ አማፂያን ላይ እየወሰደች ለሚገኘው ዘመቻ ለመበቀል ነው ብለዋል፡፡

በአንደኛው የአለም ጦርነት ወቅት ተፈፀመ የሚባለው ይህ ጥቃት በሩሲያ ፣ በተለያዩ የአውሮፓ ህብረት ሀገራት እና በአለም አቀፉ የቤተ ክርስቲያናት ምክር ቤት እውቅና የተሰጠው ነው፡፡

ጥቃቱን የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ በየአመቱ በአርሜኒያ ዋና ከተማ ዬሬቫን ያካሂዳሉ፡፡

ጉዳዩ የዘር ፍጅት ነው እና የዘር  ፍጅት አይደለም በሚል በአርሜኒያና ቱርክ መካከል ከፍተኛ የሆነ የፓለቲካ ውጥረት እየፈጠረ እስከ አሁን ዘልቋል፡፡

አርመኒያ በኦቶማን ኢምፓየር ወቅት የተፈጸመው ጥቃት 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎቿን እንደቀጠፈ መግለፅ በዘር ፍጅት እንዲመዘገብ ፍላጎት አላት፡፡

ምንጭ፡- ፕሬስ ቲቪ