የብሔርና የመደብ ጥያቄ ንትርክ ወደ ሕልውና ጥያቄ ሲቀየር! (ጌታሁን ሔራሞ)
የዶ/ር አብይ “መደመር” መፅሐፍ አጀማመሩ በ”የሰው ፍላጎቶች” መሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነው። የየትኛውም መንግስት የማታ ማታ ግቡ (Ultimate goal) የዜጎችን ፍላጎት በተቻለ አቅም ማሟላት ነው። መፅሐፉ ገና በገፅ 2 ላይ የሰው ልጅ ፍላጎቶችን እንደሚከተለው አስቀምጧል።
1. ቀጥተኛ የሕልውና ፍላጎት
2. ተዘዋዋሪ የሕልውና ፍላጎቶች
ተዘዋዋሪ የሕልውና ፍላጎቶች የሥጋ(ባዮሎጂካል) ፣ የስም/የክብር/ እና የነፃነት ተብሎ በንዑሳን ፍላጎቶች ተከፍለዋል።
ካለንበት ወቅት ጋር ቁርኝት ስላለው በዚህኛው ፖስት ላይ ስለ ቀጥተኛ የሕልውና ፍላጎት ጥቂት ልበል። መፅሐፉ ላይ ቀጥተኛ የሕልውና ፍላጎት፦
” ከግልፅና ቅርብ የሕልውና አደጋ ራስን የማዳን ፍላጎት ነው።”
የሚል ገለፃ ተሰጥቶታል። እነዚህ የሕልውና አደጋዎች በደራሲው ” ግድያ፣ ጦርነት ፣ የመጠቃት ስጋት” እንደሆኑ ተዘርዝረዋል። ታዲያ ግለሰብንም ሆነ ማህበረሰብን ከእንደዚህ ዓይነት የሕልውና ስጋት ለመከላከል የሰው ልጆች ያዋቀሩት መንግስታዊ መዋቅሮች እንዳሉ የመፅሐፉ ደራሲ ዶ/ር አብይ ያስቀመጡት ኦንደዚህ በማለት ነው፦
“በግለሰብም ይሁን በሕብረተሰብ ደረጃ የዜጎችን ቀጥተኛ የሕልውና ፍላጎት ለማሟላት ማለትም በጦርነት፣ በግድያ እና በመሳሰሉት ከሚመጣ የህልውና አደጋ ለመከላከል ሀገራት የፖሊስ፣ የመከላከያ ፣ የደህንነት እና መሰል ተቋማትን ያዋቅራሉ።”
በእኔ እይታ ቀጥተኛ የሕልውና ፍላጎት ዜጎች ሊጎናፀፉት የሚገባ መሠረታዊና ተፈጥሮአዊው ፍላጎት ነው፣ ይህ ፍላጎት ከሰው ልጅ ባለፈ በእንስሳት ዓለምም በደመነፍስ የሚንፀባረቅ ፍላጎት ነው። እስቲ በቅርብ ርቀት እዛፍ ላይ ቁጭ ወዳለች ወፍ ጠጠር ብጤ ወርውርባት፣ በሕይወት የመቆየት ፍላጎት ስላለት አድረሻዋን ፈጥኖ በመቀየር ቀጥተኛ የሕልውና ፍላጎቷን ታንፀባርቃለች። ትልልቆቹ የዱር እንስሳት ደግሞ ሕልውናቸው ላይ ከመጣህባቸው በመልስ ምቱ የአንተን ሕልውና ጥያቄ ውስጥ እስከመክተት ይደርሳሉ።
ወትሮ ቀጥተኛ የሕልውና ፍላጎት የሕዝባችን ዋነኘ ጥያቄ አልነበረም። ቀደም ሲል ማንም ከቤቱ ሲወጣ ድንገተኛ አደጋ ካላጋጠመው በቀር ወደ ቤት በሰላም የመመለሱ ጉዳይ አሳሳቢ አልነበረም። አሁን ግን ወላጆች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ሲልኩ ከስጋት ጋር ነው፣ ባልና ሚስት ጧት ሲለያዩ “Take care my honey! …ደግሞ እንዳታመሽ!” የምትለዋ አባባል የተለመደች ማሳሰቢያ እየሆነች ነው፣ ከባሕር ማዶ ያሉ ወገኖቻችንም በአካል ውጪ ይሁኑ እንጂ ልባቸው እኛ ዘንድ ነው…ለምን ቢባል የወገኖቻቸው ቀጥተኛ የሕልውና ፍላጎት ጥያቄ ላይ ወድቋላ!
በአሁኑ ወቅት “ጤፍ ስንት ገባ?” የቅንጦት ጥያቄ ሆኗል፣ ጤፍ የሚመገበው የሰው ሥጋ/አካል ረክሶ ጎዳና ላይ በድንጋይ ሲቀጠቀጥ፣ ጉሮሮ ላይ ሜንጫ ግዛት ተሰጥቶት ሲጨፍር፣ አካል በገጀራ ሲተለተል ስለጤፍ ውድነት ማውሳት የዚያ የሰላሙ ጊዜ የድሎት ወሬ ነው። ባዮሎጂካል፣ የስም ክብር(ለምሣሌ የብሔር መብት)ና የነፃነት ፍላጎቶች ትርጉም የሚኖራቸው የቀጥተኛ የሕልውና ፍላጎት ዋስትና ሲኖር ነው።
ያኔ በሰላሙ ጊዜ ወያኔና የአይዲዮሎጂ ወዳጇቿ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ የብሔር ጥያቄ ነው ይሉ ነበር አሉ፣ እነ መኢሶን ደግሞ የለም ጥያቄው የመደብ እንጂ የብሔር አይደለም እያሉ ይጨቃጨቁ ነበር አሉ…ውይ ታድለው! እንዴት ዓይነት ጆሮ ገብ ቆንጂዬ ጥያቄዎች ናቸው! ለዛሬው ጆሮአችን ለዛ ያላቸው ጥዑም ጥያቄዎች!
የዛሬው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ ግን ለጆሮ ይሰቀጥጣል። አዎን አሁን በዚህች ደቂቃ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ የብሔር ወይም የመደብ ጥያቄ አይደለም፣ ይሰማል አብይ? ይሰማል ደመቀ? ይሰማል ለማ? የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ የቀጥተኛ ሕልውና ጥያቄ ሆኖ ተቀይሯል። የብሔርና የመደብ ጥያቄ ዲስኩራችሁን ለጊዜውም ቢሆን ገለል አደርጉት። የሕዝቡን የቀጥተኛ ሕልውና ጥያቄ ሳትፈቱ ፣ ሕልውናውን ከውጪም ከውስጥ ሆነው የሚፈታተኑትን እንክርዳዶች ሳትነቅሉ ስለ ዳቦ ፋብሪካ መቋቋም አትተርክሉን፣ ስለ አባይ ግድብ አተካራ አትንገሩን፣ ስለ ራሺያው የዕደ ስረዛ አትንገሩን። መጀመሪያ ሕዝብ ይኑር፣ ከሕዝብም ደግሞ በናንተ በፖለቲካ ሊህቃኑ ንትርክ፣ ግጭትና የርስ በርስ ሽኩቻ ሕይወቱን እየገበረ ያለው ድኻው የሀገሬ ሕዝብ ይኑር። ትኩሱ ድንች እየወረደ፣ እየወረደ የማታ ማታ ከነግለቱ የሚያርፈው ድኻው እጅ ላይ አይደል?
መቼስ መፍትሄው ምን ይሁን የሚለኝ አይጠፋም? መፍትሄውማ መች ጠፋን? ልድገመው መሠለኝ ፣ መደጋገም አፅንዖት መስጫ አንዱም መንገድ አይደል?
“በግለሰብም ይሁን በሕብረተሰብ ደረጃ የዜጎችን ቀጥተኛ የሕልውና ፍላጎት ለማሟላት ማለትም በጦርነት፣ በግድያ እና በመሳሰሉት ከሚመጣ የህልውና አደጋ ለመከላከል ሀገራት የፖሊስ፣ የመከላከያ ፣ የደህንነት እና መሰል ተቋማትን ያዋቅራሉ።”
ፖሊስ፣ መከላከያ፣ ደህንነት….እነዚህ ተቋማት ከእግዜሩ በታች እኛን ሊጠብቁን በኛው የቀረጥ ገቢ የሚተዳደሩ መንግስታዊ ተቋማት ናቸው። በክርስትናው እምነት ደግሞ ሹማምንት የተሰየሙት ሥርዓተ አልባኛውን ሥርዓት ያስይዙ ዘንድ እንደሆነ በቅዱሱ መፅሐፍ ተፅፏል። ለመሆኑ የደህንነት ተቋሙ የት ነው? ለራሱ ግን ደህና ነው? አይመስለኝም! ለነገሩ የደህንነት ተቋሙን ደህንነት ከተጠራጠርን ቆየ፣ ያኔ በጠራራ ፀሐይ ያ ሁሉ የመከላከያ ቡድን አባላት ለደመወዝ ጥያቄ ውሎ ሲያድር ደግሞ ለመፈንቅለ መንግስት ነው ተብሎ በተናገረን ትንግርት ከቡራዩ እስከ ቤተመንግሥት ሰተት ብሎ ሲሄድ የደህንነት ተቋሙ የት ነበር? ፍልቅልቁ አምባቸው፣ የሀገሩን አንድነት መርጦ ከአብይ ጎን ቆሞ የነበረው የእርጋታ ተምሣሌቱ ቁጥቡ ጀኔራል ሰዓረ፣ ሌሎች የአማረ ክልል አመራሮች በግልፅ በጥይት አረር ሲቆሉ ደህንነቱ የት ነበር? አስቀድሞ እኮ ውሽንፍሩና ፉከራው ስለመኖሩ እኮ ተራው ሕዝብ ራሱ ጠርጥሮ ነበር እኮ! ጀዋር “ከወያኔ ሽማግሌዎች ጋር ስትራቴጂካዊ ቁርኝትን እፈጥራለሁ” ባለ ማግስት በለጠፋት የአንድ አንቀፅ የፌስ ቡክ ልጥፍ ሰበብ 7ዐ ያህል ዜጎች ሲቀሰፉ ደህንነቱ የት ነበር? መከላከያና ፌዴራል ፖሊስስ የበላዮቹን ትዕዛዝ ጠብቆ ይሰማራል እንቀል፣ የደህንነት መስርያ ቤቱም ለስለላው ደጅ ይጠና ይሆን? ፈቃድ ይጠይቅ ይሆን? ጥያቄዬን ከሌላ ፕላኔት አላመጣሁም፣ ከዚሁ ከቅርብ ከአብይ መፅሐፍ ላይ ነው። እሱ ደራሲው “ፖሊስ መከላከያና የደህንነት ተቋማት” የዜጎችን የሕልውና አደጋን ይከለከላሉ ብሎ ፅፎልን የለ? ሕዝቡ በሕልውና አደጋ ላይ ከሆነ እነዚህ ተቋማት ግዳጃቸውን እየተወጡ አይደለም ማለት ነው። ለሦስተኛ ጊዜ ልድገመው፦
“በግለሰብም ይሁን በሕብረተሰብ ደረጃ የዜጎችን ቀጥተኛ የሕልውና ፍላጎት ለማሟላት ማለትም በጦርነት፣ በግድያ እና በመሳሰሉት ከሚመጣ የህልውና አደጋ ለመከላከል ሀገራት የፖሊስ፣ የመከላከያ ፣ የደህንነት እና መሰል ተቋማትን ያዋቅራሉ።”
በመጨረሻም አንድ ነገር ልበል፦ ፖሊስ፣ መከላከያና ደህንነቱ የሕዝብን ሕልውና ከአደጋ ካልታደጉ በናዝሬት፣ በደብረ ዘይት፣ በዱከም፣ በካራቆሬ ወዘተ እንደተስተዋለው ሕዝብ የራሱ ፖሊስ፣ የራሱ መከላከያ፣ የራሱ ደህንነት መሆን ይጀምራል። አሁን ያለው አዝማሚያም ይህን ይመስላል። ይህ አዝማሚያ ደግሞ ሀገሪቱን ለበለጠ እልቂት፣ ለከፋ ውድመት አሳልፎ የሚሰጥ አካሄድ ነው። ከሁሉም በላይ ደህንነቱ ከየትኛውም ወገን የሰው ልጅ ሕልፈት እንዳይከሰት የመረጃ መረቡን እስከ ቀበሌና ሰፈር ድረስ ዘርግቶ በንቃት መስራት ይጠበቅበታል።
ቅድሚያ ለቀጥተኛ የሕዝብ የሕልውና ጥያቄ!!! ይህን ተልዕኮ እንድትፈፅሙ መሪዎች እግዚአብሔራዊም ሕጋዊም ኃላፊነት አለባችሁ።
►