November 1, 2019

Source: https://www.zehabesha.com

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዉስጥ ብሔረተኝነት ትልቁን ስፍራ ይዟል። ሆኖም ይህ አንገብጋቢ ጉዳይ በብዙዎች ዘንድ ግልፅነት የለዉም። ምሁራን እንደሚሉት ብሔረተኝነት የተለያዩ ትርጉሞች አሉት። በጥቅሉ ግን የራስን ብሔር መዉደድ ተብሎ ሊገለፅ ይችላል። ይህ ደግሞ የብሔሩ ክብር እና ጥቅም እንዲረጋገጥ ከልብ መታገልን ያጠቃልላል።
.

በመሠረቱ የራስን ብሔር መዉደድ ሌላ ብሔርን መጥላት አይደለም። ይልቁንም ትክክለኛ ብሔረተኝነት ስለሌሎች ማሰብን ያማክላል። መጀመሪያ ነገር ሰዉ በራሱ ወገን ላይ እንዲደርስ የማይፈልገዉን ክፉ ነገር በሌላ ወገን ላይ ማድረግ የለበትም። ሁለተኛ ነገር በሌላ ቦታ ለራሱ ወገን እንዲሆንለት የሚፈልገዉን መልካም ነገር እሱም በያለበት ለሌሎች ወገኖች ማድረግ አለበት።
.
በአከባባያችን ሌሎች ወገኖችን መግፋት በሌላ ቦታ የወገናችንን መገፋት ሊያስከትል ይችላል። ስለሆነም ለራሱ ብሔር ጥቅምና ክብር በትክክል የሚቆም ሰዉ ስሌላዉ ብሔር ጥቅምና ክብርም ይጨነቃል። ከምንም በላይ ግን ጥቅሞቻችን እና ችግሮቻችን የተሳሰሩ መሆናቸዉን መገንዘብ ያስፈልጋል። ስለራስ ወገን ብቻ ማሰብ ረጅም ርቀት አይወስድም።
.
ስለ ወለጋ እና ጅማ የቡና እርሻ ግድ የሌለዉ ጉራጌ፣ ስለአፋር እና ጅቡቲ ሠላም የማይጨነቅ የጉጂ፣ የወለጋ ወይም የጅማ ኦሮሞ፣ ስለጅጅጋ ፣ ጎዴ ወይም ሀርጌሳ ጉዳይ ግድ የሌለዉ የሀረርጌ ወይም የባሌ ኦሮሞ፣ ስለ ጎጃም እና ጎንደር ልማት የማያስብ የገርበጉራቻ ኦሮሞ፣ ከሸኖ እስከ ሸገር ስላለዉ አከባቢ ሠላም እና ልማት የማይቆረቆር የደብረብርሃን አማራ፣ ስለጓፅዮን፣ ስለገርበጉራቻ እና ስለፊቼ ምንም የማይሰማዉ የጎንደር ወይም የማርቆስ አማራ፣ ስለሻሸመኔ፣ ስለባቱ እና ስለሞጆ ስሜት የሌለዉ የሀዋሳ ወይም የአለታ ወንዶ ሲዳማ፣ ስለመቂ፣ ስለአርባምንጭ፣ ስለአደአ፣ ስለሰበታ፣ ስለቡራዩ፣ ስለለገዳዲ ወይም ስለባሌ ሰላም እና ብልፅግና የማይጨነቅ አዲስ አበቤ፣ ስለሱዳን፣ ስለኬንያ፣ ስለኤርትራ፣ ስለሶማሊያ፣ ስለቻይና ወይም ስለጅቡቲ ሁኔታ የማያስብ ኢትዮጵያዊ ምንም ያህል በብሔሩ፣ በአከባቢዉ ወይም በሀገሩ ስም ቢፎክር የብሔር ነጋዴ እንጂ ብሔረተኛ አይሆንም።
.
ብሔረተኝነቴ ለወገኖቼ ጥቅም እንጂ ጉዳት ሊያመጣ አይገባም። እኔ ከሌሎች ጋር በሚኖረኝ መልካም ግንኙነት የኔ ወገኖች በሄዱበት ሁሉ በፍቅር እና በክብር የሚታቀፉ እና የሚስተናገዱ ከሆነ የምር ብሔረተኛ ነኝ። እኔ ከሌሎች ጋር በሚፈጥረዉ ንትርክ እና ሻካራ ግንኙነት ወገኖቼ በደረሱበት ሁሉ በጎሪጥ የሚታዩ ከሆነ ግን የስም እንጂ የተግባር ብሔረተኝነት አይኖረኝም።
.
የራስን ወገን መዉደድ ለሌሎች በሚኖረን ፍቅርና ክብር ሊታጀብ ይገባል። ሌሎችን በመጥላት እና ራስን ብቻ በማኮፈስ ላይ የተመሠረተ ብሔረተኝነት ትክክለኛ ስሙ እብሪተኝነት ይሆናል። እብሪተኝነት ደግሞ አደገኛ እሳትን በመፍጠር ሌሎችን ብቻ ሳይሆን የራስን ወገን ጭምር ያቃጥላል። በሁለተኛ የአለም ጦርነት ጊዜ ጀርመንን፣ ጣሊያንን እና ጃፓንን ያቃጠለዉ እና አለምን በሙሉ የለበለበዉ እሳት በብሔረተኝነት ካባ ተከሽኖ ከተስፋፋዉ እብሪተኝነት አብራክ የተወለደ ነዉ። ስለዝህ ብሔረተኝነትን ከእብሪተኝነት መለየት ያስፈልጋል።
.የሚያወጣን መደመር ነዉ!