በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች ላይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ

በጀግኖች ሰማእታት ብርቱ ተጋድሎና ክቡር መስዋእትነት የተገነባዉ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (...)፣ በታሕሳስ 4 እና 5/2012 .9ኛ ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ አድርጎ አመራሮቹን መምረጡ ይታወቃል። የኢሕአፓ ቋሚ ኮሚቴ በሐገራዊና ድርጅታዊ አጅንዳዎቸ ላይ ከነሐሴ 2 – ነሐሴ 8/2012 .ም ድረስ በወቅታዊ የኢትዮጵያ የፖለቲካኢኮኖሚ ሁኔታዎች ላይ፤ በኢትዮጵያ ስላለው የሰላም፣ የዴሚክራሲና የልማት ክንዉን ሂደቶች በስፋት መክሯል፡፡ ፓርቲው የ2012 .ም የ6 ወራት የእቅድ አፈጻጸሙን ግምግሞ የ2013 .ም የበጀት ዓመት የፓርቲዉ እቅድ ላይ ከፍተኛ ዉይይት አድርጓል። በተጨማሪም፣ የፓርቲው አባላትና ድጋፊዎች የሰላማዊ ትግል መርሆዎችና ስልቶችን ተግባራዊ በሚያደርግ፣ የትግል ቁርጠኝነታቸውን ጠብቀው ለማይቀረው ድል እንዲሰለፉና ሃገራቸውንና ሕዝባቸውን ካንዣበበባቸው አደጋ እንዲከላከሉ ጥሪውን አቅርቧል።

የኢሕአፓ ቋሚ ኮሚቴም የሚከተሉትን ዉሳኔዎችና ያቋም መግለጫዎችን በሰፊው ከተወያየ በኋላ አዉጥቷል፡፡

1. መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ና በቅርቡ የጀመረውን ለሰላም፣ ለልማትና ለዲሞክራሲ እውን መሆን የሚያደርገዉን ጥረት እያደነቅን፣ ይህን መሰሉ ሕግን የማስከበር ጉዳይ አስቀድሞ ተከናውኖ ቢሆን ኖሮ ዜጎች በጠራራ ጸሐይ ከመገደልና ሃብት ንብረታቸውም ከመውደም መታደግ ይቻል እንደነበር፤ ኢሕአፓ እምነቱን እየገለጸ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ግጭት ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር ለንጹሀን ዜጎች ሞት ስደት እንግልትና መፈናቀል፤ምክንያት የሆኑ ንብረት ያወደሙና የዘረፉ ወንጀለኞችን ለህግ በማቅረብ ተጠያቂ የማድረገረ ሂደቱን አጠናክሮ እንዲቀጥልና ተጠርጣሪዎችና ከሁከቶች ጋር ግንኙነት ያላቸው ሁሉ አፋጣኝ የፍርድ ሂደት እንዲያገኙ ኢሕአፓ መንግስትን ይጠይቃል።

2. የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በታቀደለት ጊዜ በመጠናቀቁ ኢሕአፓ የተሰማውን ልባዊ ደስታ እየገለጸ፣ መንግስት በጣና ሐይቅ ዙሪያ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም ችግርና በወንዞቻችን፣ ሐይቆቻችንና በተፈጥሮ ሃብቶቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን ብሔራዊ አደጋ ለማስቀረት ሕዝባዊ ንቅናቄ አስፈላጊ በመሆኑ፣ የኢሕአፓ አባላትና ደጋፊዎች የተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤንና ጥበቃን ለማጎልበት በንቃት እንዲሳትፉ ጥሪውን ያስተላልፋል።

3. በደቡብ ክልል እየተከስቱ ያሉት ግጭቶችና ሰሞኑን በወላይታ ዞን የተፈጸመው ሁከትና ብጥብጥ ወደከፋ ሁኔታ ከመቀየሩ በፊት መንግስት የክልል እንሁን ጥያቄዎችና የአከላልለ ጉዳይን በተመለከተም፣ በተጠናና በማያዳግም ሁኔታ እንዲፈታው እየጠየቅን፤ ችግሮችን በክልሉ በሚኖሩት ሕዝቦች ፍላጎትና ውይይት መሰረት አድርጎ መፍታት አለበት። የአስተዳደር በደል ጥያቄዎቹንና አለመረጋጋቱን ተገን አድርገዉ በሚቀሰቀሱ ግጭቶች ተከትሎ የሚጠፋዉ የሰዉ ሕይወትና የሃገር ሃብት ውድመት በአስቸኳይ እንዲያቆምና ችግሮችም በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ እንዲፈቱ ኢሕአፓ በአንክሮ ይጠይቃል። በግጭቱ ሰበብ ለሞቱት ወገኖች የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እየገለጽን፤ በየትኛውም የፌዴራሉ ክልሎች ውስጥ ለዘመናት ተዋዶና ተከባብሮ የሚኖረውን ሕዝብ ርስበርስ ለማጋጨትና ሃገራችንን ወዳልተፈለገ የርስበርስ ግጭት ለመክተት የሚሯሯጡ ቡድኖችና ሃይሎችን ለፍርድ ለማቅረብ መንግስት እየወሰደ ያለውን ርምጃ ኢሕአፓ ይደግፋል።

4. የኮቪድ-19 ወረርሽኝኝ በሀገራችን ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ፣ በመላው ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት፣ የኢኮኖሚ ጫና በመላው ሕዝባችን ላይ ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ በመሆኑና የለትተለት የምግብና ሸቀጣሸቀጦችም ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋንረት እየተከሰተ ስለሆነ፣ የዋጋ ንረቱም የሃገራዊ ምርት እጥረት ሳይሆን የአቅርቦት ውሱንነት ያስከተለው በመሆኑ፣ መንግስት በአፋጣኝ ገበያውን በመቆጣጠርና ሕዝቡን ካልተገባ የኢኮኖሚ ምዝበራ እንዲታደገው እንጠይቃለን፤ከዚህ በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ ያለዉ ከፍተኛ የህዝብ ትራንስፖርት እጥረት ረጃጅም ሰልፎችን እየፈጠረ ህብረተሰቡን ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዲሆን እያደረገዉ ስለሆነ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲፈለግለት አሕአፓ በአጽንኦት ያሳስባል፡፡

5. በተለያዩ የሃገራችን ክልሎች በሰላምና መረጋጋት እጦት ምክንያት ፣ አካላቸው ለጎደለባቸው፣ ንብረታቸው ለወደመባቸው፣ ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉና ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ዜጎች መንግስት ወደ ሰላማዊ ኑሮአቸው መመለስ የሚችሉበትን ካሳ እንዲከፍል ና ዜጎች በብሔራቸዉና በማንነታቸዉ እየተለዩ የሚደርስባቸዉን ጥቃት እንዲከላከል ኢሕአፓ ጥሪዉን ያቀርባል፡፡

6. የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና የብልጽግና ከፍተኛ አመራሮች በተለያዩ ሕዝባዊ መድረኮች ስብሰባዎችና ብዙሀን መገናኛ ድርጂቶች ላይ የሚያደርጉት ከፋፋይ ና በተወሰኑ ብሄሮችላይ የሚያነጣጥር ንግግር በኢትዮጵያዉያን ዜጎች መካከል ለብዙ ዘመናት አብሮ የኖረዉን የመቻቻልና የመከባበር እሴት የሚሸረሽርና ለጥላቻ፣ለግጭትና እርስበርስ በጥርጣሬ አይን ለመተያየት በር የሚከፍት አደገኛ ተግባር ስለሆነ ኢሕአፓ እንደዚህ አይነት ንግግሮች እንዲታረሙ በጥብቅ ያሳስባል፤ ለአብነትም ፤.ሰሞኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬእዳነት አቶ ሺመለስ አብዲሳ ብልጽግናን በተመለከተ ያደረጉት ንግግር በኢትዮጵያዉያን መካከል የነበረዉን የእርስበረስ ግንኙነትና ዉሁድ ኢትዮጵያዊነትን የሚሸረሽር አደገኛና ዘረኛ ሀሳብ መሆኑ ግልጽ ነዉ፤ይህ ሀሳብ እዉን የብልጽግና ፓርቲ ሀሳብ ከሆነ የተረኝነት ጉዳይ እንጂ የለዉጥ ጉዳይ ሊሆን ስለማይችል ሀሳቡ የግለሰብ ወይም የፓርቲዉ ሀሳብ መሆን አለመሆኑን መንግስት ግልጽ እንዲያደረግ እንጠይቃለን፡፡

7. በፌደራል መንግስትናአምባገነኑ ህዉሀት በሚመራዉ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መካካል ከጊዜ ወደጊዜ እየተካረረ የመጣዉ ዉዝግብና አለመግባባት በንጹሀን የአማርኛና የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰቦች የእለት ተእለት እንቅስቃሴና ኑባሬ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እየፈጠረ መሆኑ እሙን ነዉ፤ስለዚህ መንግስት ለንጹሀን ዜጎች ሲል የህግ የበላይነትን በማስከበር በኩል ጥብቅ እርምጃ በመዉሰድ ስርአት አልበኞችንና አምባገነኖችን ለህግ እንዲያቀርብ እየጠየቅን፣ያለምርጫ ቦርድ ፈቃድና እዉቅናሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሳያካትት ሕዉሀቶችና በተናጠል የፊታችን ጳጉሜ 4/2012.ም ሊያደርጉት ያቀዱትን ምርጫም ጣልቃ ገብቶ እንዲያስቆም ኢሕአፓ በአጽንኦት ይጠይቀል፡፡

8. ፓርቲያችን ኢሕአፓ ባለፉት 6 (ስድስት) ወራት ውስጥ ያከናወናቸዉን ዋናዋና ተግባራት በጥልቀት የገመገመ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ደማቅና ጉልሕ ስፍራ ያለውና ዘመን ተሻጋሪ የሆነዉ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ታግሎበማታገል መርሆውና አይበገሬነቱ ጸንቶ የሚገኝ ድርጅት መሆኑን ለመላው አባላቱና ደጋፊዎቹ እየገለጸ፤ ከርእዮትኣለማችን ከማሕበራዊ ዴሞክራሲ (ሶሻልዴሞክራሲን) ጋር ተመሳሳይነትና ተቀራራቢነት ያላቸውንና በኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነትና እኩልነት ላይ ጽኑ እምነት ያላቸውን ፓርቲዎችና የፖለቲካ ሃይሎች ሁሉ የትብብርና የአጋርነት ጥሪ ያቀርብላችኋል።

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!!

...ፓ ለተሻለ ነገ!!