ከ 6 ሰአት በፊት

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ ጎረቤት አገር ሱዳን ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድም ወደ ካርቱም አቅንተዋል።
ፖምፔዮ ከሰባት ዓመታት በኋላ ሱዳን የጎበኙ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣን ናቸው። ለመጨረሻ ጊዜ አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ልዑክ ሱዳን የጎበኘው በፈረንጆቹ 2013 ሲሆን የኦባማ ውጭ ጉዳይ ኃላፊ የነበሩት ኮንዶሊዛ ራይስ ነበሩ ካርቱምን የረገጡት።
ፖምፔዮ በእስራኤል የነበራቸውን ጉብኝት አጠናቀው ነው ወደ ሱዳን የመጡት።
ለመሆኑ የማይክ ፓምፔዮ ወደ ሱዳን ማቅንት አንደምታው ምንድነው? የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በሥፍራው መገኘት ፋይዳስ?
የሰውዬው ጉብኝት ለሱዳንም ሆነ ለቀጣናው ትልቅ ፋይዳ አለው የሚሉት በኪል ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አወል አሎ (ዶክተር) ናቸው።
“እንደሚታወቀው ሱዳን ለውጥ ላይ ናት። አሁን ሥልጣን ላይ ካለው የሽግግር አስተዳደር በፊት የነበረው መንግሥት ከአሜሪካ ጋር እንዲሁም ከሌሎች የአውሮፓ አገራት ጋር የነበረው ግንኙነት ሻካራ ነበር።”
ይሁን እንጂ የሽግግር መንግሥቱ ከእነዚህ አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ነበር ይላሉ ባለሙያው።
“ጥረት ከማድረግ አልፎ አሜሪካ እንደ ቅደም ሁኔታ ያስቀመጠችውን ነገር ማሟላት ጀምረዋል። ለምሳሌ የቀድሞው ፕሬዝደንት ኦማር አል-ባሽርን ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኞ እንደሆኑ ሲገልፁ ነበር። የሁለቱን አገራት ግንኙነትን ለማሻሻል እየሠሩ እንዳለ ማሳያ ነው።”
አወል (ዶ/ር) ሱዳን ካሳየችው ፈቃደኝነት ባለፈ የትራምፕ መንግሥት ወደ ሁለተኛ ዙር ምርጫ እየሄደ ስለሆነ በውጭ ጉዳይ በኩል የታየውን ደካማ ሥራ ማከም ይፈልጋና ለዚህ ነው የሚኒስትሩ አመጣጥ ይላሉ።
በዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስና በእስራኤል መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነትም የዚህ አካልም እንደሆ ይጠቅሳሉ።
ሱዳን፤ በአሜሪካ መንግሥት ሽብርን ከሚደግፉ ተብለው ከተዘረዘሩ አገራት መካከል ናት። ባለሙያው፤ አሜሪካ ሱዳን ከዚህ መዝገብ ላይ ብትፋቅ የትራምፕ አስተዳደር የበለጠ ይጠቀማል ይላሉ።
የአባይ ጉዳይ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከሱዳኑ አቻቸው አብደላ ሐምዶክና ከአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ ጋር ስለ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ይወያያሉ ተብሎ በብዙዎች ዘንድ ግምቱ አለ፤ ምንም እንኳን የተረጋገጠ መረጃ ባይኖርም።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጉብኝት አጋጣሚ ነው ወይስ የታሰበበት?
“በጭራሽ የአንድ አገር መሪና ለዚያውም የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአጋጣሚ ሊገናኙ አይችሉም” ይላሉ አወል (ዶ/ር)፤ ሁለቱ እዚያ እንዲገናኙ የተፈለገበት ምክንያት እንደሚኖር በመገመት።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሱዳን ጉብኝት የተቃደና የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ሊሆን ከተቻለም የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ሌላው መነጋገሪያ አጀንዳ እንደሚሆን ባለሙያው ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አሜሪካ ጠንከር ያለ የግብጽን ፍላጎት የሚደግፍ የሚመስል አቅጣጫ እየተከለች ነው። አሜሪካ ይህን እያደረገች ያለችው መርህ ላይ በተመሠረተ መልኩ አይደለም። እርግጥ ነው ሁለቱ አገራት [ግብጽና አሜሪካ] ለረዠም ጊዜያት አጋር ሆነው ቆይተዋል። ይህ እስራኤልንም የሚመለከት ነው” ይላሉ አወል (ዶ/ር)።
አክለውም “ግብጽ አሜሪካና አንዳንድ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትን በመጠቀም ጫና እያሳደረች ነበር። ስለዚህ የአሜሪካ አቅጣጫ ምን እንደሆነ መገመት ይቻላል። ሐሳባቸው ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የቀረበውን ስምምነት እንደትቀበል ነው። በአርግጠኝነት ፖምፔዮና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በዚህ ጉዳይ ላይ ይወያያሉ” በማለት ሊነሱ ከሚችሉ ጉዳዮች መካከል ይጠቅሳሉ።

የኮንግረስ አባላት ጥያቄ
በቅርቡ የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ መንግሥት ላይ ጫና እንዲያሳድር የሚጠይቅ ደብዳቤ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማይክ ፖምፒዮ መፃፋቸው አይዘነጋም። ቢዘህ ጉዳይ ላይ ውይይት ያደርጉ ይሆን?
“ይሄ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ መነሳቱ ምንም ጥያቄ የለውም። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኮንግረስ የፃፈላቸውን ደብዳቤ እንዲሁ ችላ ማለት አይችሉም። ስለዚህ ይህንን ርዕስ ማንሳታቸው የሚቀር አይደለም” ይላሉ።
ባለሙያው አሜሪካ የራሷን ጥቅም ለማስከበር ስትል እንጂ ለሰብዓዊ መብት በማለት ምንም ነገር እንደማታደርግ አፅንዖት በመስጠት ይናገራሉ። “ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ካለው ሁኔታ አንጻር ሰብዓዊ መብትን ለማስከበር ሳይሆን አሜሪካ ከኢትዮጵያ የምትፈልገውን ነገር ለማግኘት ይህንን አጋጣሚ ልትጠቀምበት ትችላለች።”
አሜሪካ ከኢትዮጵያ ምን ትፈልጋለች?
አሜሪካ ከኢትዮጵያ የምትሻው ትልቁ ነገር በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሆነ ባለሙያው ያስረግጣሉ።
“ፕሬዝደንቱ [ትራምፕ] አሁን በቀጣይ ኅዳር ወር ላይ ለሚካሄደው ምርጫ የሚፈልጉት ነገር ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፍ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ስምምነት ላይ ደረሱ የሚለውን ጉዳይ ነው። ይሄ ለፕሬዝደንቱ ትልቅ ድል ነው።”
እንደማንኛውም ከዚህ ቀደም የነበረ ፕሬዝደንት የአሁኑ ፕሬዝደንትም የውጭ ጉዳይን በተለመከተ ያገኙት ድል ምንድነው? የሚለው ይነሳል። ስለዚህ አሜሪካ በተቻለ መጠን ኢትዮጵያን ተጭናም ቢሆን ስምምነቱን እንድትቀበል ለማድረግ ጥረት ሊያደርጉ እንደሚችሉ ያምናሉ።
ባለሙያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ መለሳለስ ያሳያሉ አያሳዩም የሚለው ትልቅ ጥያቄ ነው፤ ነገር ግን ምላሹን መገመት ያዳግታል ይላሉ። የአሜሪካን ፍላጎት መገመት ግን ብዙም አዳጋች አይደለም እንዳልሆነ ያምናሉ።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ የሱዳን ጉብኝት፤ በእስራኤል፣ በባህሬንና በተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች የሚያደርጉት የጉዞ ፕሮግራማቸው አካል ነው።