አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ

ህዳር 20 ቀን 2013 ዓ.ም

አዲስ አበባ ሸዋ

ህወሀት በጉልበት፣በሴራና በሸፍጥ ከአማራ በመውሰድ በከፋፋይነት ሴራውም ለበርካታ ዓመታት ግፍና በደል ሲፈፅምበት የነበረው ማክሰኞ ገቢያ/ከተማ ንጉስ በተከፈለው መስዋዕትነት በቁጥጥር ስር መዋሉ ይታወቃል።

ትናንት ህዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም ማክሰኞ ገቢያ ላይ የተካሄደውን ስብሰባ የአማራ ክልል ቢሮ ሀላፊዎች፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች የመሩት ሲሆን በወረዳው ውስጥ ከሚገኙ ከ8 በላይ ቀበሌዎች የተወጣጡ የሀይማኖት አባቶች ተሳታፊ ሆነዋል።

በውይይቱም መንግስት ህግና ስርዓትን ለማስከበርና አጥፊውን የትህነግ ቡድን ለህግ ለማቅረብ እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ አካባቢውን በማረጋጋት፣ ማህበረሰቡን ወደነበረበት ሰላማዊ እንቅስቃሴ ይመለስ ዘንድ የሀይማኖት አባቶች ካላቸው የተሻለ ሁለንተናዊ ቅርበት አኳያ አልፎ አልፎ የሚታዩ የተዛቡና ያልተረጋጉ አስተሳሰቦችን፣አካሄዶችን፣ እይታዎችንና ክስተቶችን አርሞ ሰላማዊ ህይወቱን እንዲመራ በመምከር፣ በማስተማርና የተራራቀውን በማቀራረብ እረገድ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ተጠቁሟል።

እድሜ ጠገብ የሀይማኖት አባቶች በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት አባቶቻቸውና ቅድመ አያቶቻቸው በጀግንነታቸው፣ በሰው አክባሪ እንግዳ ተቀባይነት ባልተመረዘ ቱባ ባህላቸው ኮርተው፣ ለማይደራደሩባት ሀይማኖታቸው ቆመውና በማንነታቸው ፀንተው በኖሩበትና ባስረከቧቸው የወልቃይት ጠገዴ ምድር ላይ የፅንፈኛው ህወሀት የአገዛዝ ሰርዓት አካባቢውን በሀይል ባስተዳደረባቸው በእነዚያ የስቃይና የሰቆቃ ዘመናት በሀይማኖት ተቋማት፣ በሀይማኖት አባቶችና አማኞች ላይ በርካታ ግፍና በደሎች ሲፈፀሙ እንደቆዩ ገልፀዋል።

በተለይ አሸባሪው ቡድን የሚታወቅበት ለእራሱ የጭቆና አገዛዝ በሚመቸው መንገድ ባረቀቀው ህገ መንግስት ላይ ያሰፈረውን “መንግስት በሀይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤ ሀይማኖትም በመንግስት ስራ ጣልቃ አይገባም” ብሎ ለይስሙላ የፃፈውን አንቀፅ በማናለብኝነት ሲጥሰው፣መጠራጠርና አለመተማመን ብሎም ግጭት እንዲነሳ በማሰብም ሲንቀሳቀስ መክረሙን ተናግረዋል።

ሕወሓት ሀይማኖታዊ ተቋማት የተሰጣቸውን ሀላፊነት እንዳይወጡ ሀይማኖታዊ ሰርዓቱና ትውፊቱ እንዲጠፋ ፣ቅርሶችና ንዋየ ቅዱሳት እንዲዘረፉ ሲያደርግ መቆየቱን የሀይማኖት አባቶች በግልፅ አስረድተዋል።

በጨካኙ ቡድን ከአካባቢያቸው እርቀው የቆዩ በርካታ የሀይማኖት አባቶችም ዛሬ ላይ በተገኘው የድል ጮራ መደሰታቸውን በውይይቱ ላይ በመግለፅ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ የሆኑት ዶ/ር ሙሉቀን ተገኘ በውይይቱ ማጠቃለያ እንደተናገሩት አሁን ላይ በአካባቢው በተከናወነው ህግን የማስከበር ተግባር ይፈፀምባቸው ከነበረው የመከፍፈል ግፍና በደል ጭምር ነፃ እንደወጡና የሀይማኖት ተቋማትም ተረጋግተው ወደ ቀደመው ስርዓታቸው ተመልሰው አማኞቻቸውን እንደየ እምነታቸው ማገልገል እንዳለባቸው አሳሰበዋል።

ዶ/ር ሙሉቀን አክለውም የሀይማኖት አባቶች በየአካባቢያቸው ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በመረዳት ማህበረሰቡን በማረጋጋት ወጣቱ ነገሮችን በሰከነ መንገድ እንዲረዳና የተገኘውን መልካም የሆነ የነፃነት አጋጣሚ ዳር ለማድረስ አካባቢያቸውን በንቃት እንዲጠብቁ፣ ያልተፈለጉ እንቅስቃሴዎችን እንዲያስወግዱ በመምከርና በመገሰፅ እንዲሰሩ አሳስበዋል።

ከዚህ ቀደም በአካባቢው በአመራርነት፣በፖሊስነት፣በልዩ ሀይልነት፣በዞባዊ ሚሊሻነት ሲያገለግሉ የነበሩ እጃቸውን ያልሰጡ አካላት መንግስት እርምጃ ከመውሰዱ በፊት በሰላማዊ መንገድ መሳሪያቸውን አውርደው ከማህበረሰባቸው ጋር በሰላም እንዲኖሩ በማድረግ ረገድም የሀይማኖት መሪዎችና ትልልቅ አባቶች ሀላፊነታቸው ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል። የጠገዴ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ሙሉጌታ በበኩላቸው መካርና አዋቂ ፣አስተዋይ ትዕግስተኛ ህዝብ ያለበትን ወልቃይት ጠገዴን ግፈኛውና ሴረኛው የህወሀት ቡድን ታሪኩን በማጥፋት ወንድማማች ህዝቦችን በተለያየ መንገድ እየከፋፈለ በደል ሲያደርስ የቆየ ቢሆንም በአባቶች ፀሎት በግፍ የታረዱ ሰማዕት ጀግኖቻችን በከፈሉት የደም መስዋትነት ዛሬ ቀኑ ደርሶ ይህ ታላቅና ጀግና ባለ ታሪክ ህዝብ ለዚህ ድል በቅቷል ብለዋል።

ድሉንም እስከ መጨረሻው ለማጣጣም ሲባል የአካባቢያችንን ሰላም የበለጠ ለማረጋገጥ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባና በተለይ የሀይማኖት አባቶች ሰላምን በመስበክ ፣ በማስተማር፣ጥንት አባቶች ባቆዩልን በሀገራችን ወግ ባህል መሰረት በማስታረቅ ማህበረሰቡን በማረጋጋት እረገድ አስተዋፅኦ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ምንጭ_የጠገዴ ወረዳ ኮሚዩኒኬሽን