እርግጥ ነው፤ የተገኘው ድል የሚያስደስትና የሚያኮራ ነው፤ ሆኖም ”ህወሓት ተቀብሯል“ ለማለት አለመቸኮል ብልህነት ነው። ከአሁኑ የተጠናከረ ጥረት ካልተደረገ ህወሓት ለመንቀል የሚያስቸግር የሽብር ድርጅት ሊሆን ይችላል፤ ዛሬም በትግራይም ከትግራይ ውጭም ተባባሪዎች አሉት።

ህወሓትን ከ ISIS ጋር ሳነፃፅር ከሀይማኖት ጋር እያያዙ አጓጉል ትርጓሜ ለሚሰጡ አንባቢዎቼ ሽብርተኝነትን እኔ እንዴት እንደምረዳው ጥቂት ዓረፍተ ነገሮችን ልበል።

ሽብርተኝነት ሀይማኖት፣ ርዕዮተ ዓለም፣ ወይም ፍልስፍና አይደለም። ሂንዱ፣ ቡድሃ፣ አይሁድ፣ ክርስቲያን፣ … ኢአማኒን የሆኑ አሸባሪዎች ነበሩ፣ አሉ። ማርክሲስት፣ አናኪስት፣ ግና ዘመም፣ ቀኝ ዘመም፣ ብሄረተኛ፣ ፋሺስት፣ ፀረ-ኮሎኒያሊስት፣ ፀረ-ካፒታሊስት፣ ዓለም ዓቀፋዊ የነበሩ ሽብርተኞች ነበሩ፣ አሉ። ለአብዛኛዎቹ ሽብርተኛ ድርጅቶች ሽብርተኝነት በራሱ ግብ አይደለም። ሽብር ለመፍጠር ብቻ ሲሉ የሽብር ጥቃት የሚፈጽሙ ድርጅቶች እምብዛም የሉም። ብዙዎቹ ሽብርተኛ ድርጅቶች ሊያሳኩት የሚፈልጓቸው – ለአንዳንዱ ሀይማኖታዊ፣ ለሌሎቹ ዓለማዊ – ግቦች አሏቸው።

እና ሽብርተኝነት ምንድነው?

ሽብርተኝነት ስትራቴጂ ወይም ታክቲክ ነው። ለአንዳንድ ድርጅቶች ሽብርተኝነት ቋሚ ”የትግል ስትራቴጂያቸው“ ነው። እነዚህ ድርጅቶች መንግስትና ሕዝብን በማሸበር ዓላማቸውን ማሳካት እንችላለን ብለው ያምናሉ። ለአንዳንድ ድርጅቶች ደግሞ ሽብርተኝነት እንደሁኔታው ገባ ወጣ የሚሉበት ታክቲክ ነው

ሁኔታው ሲመች ሰላማዊ፣ ሳያመች ደግሞ ከሽብርተኝነት ውጭ የሆነ የአመጽ ትግል፣ ሁኔታው በጣም ሲከፋ ለአጭር ጊዜ ሽብርተኛ የሚሆኑ ድርጅቶች አሉ። ”በስትራቴጂ“ እና ”በታክቲክ“ መካከል ያለው ዋነኛው ልዩነት ጊዜ ነው። ስትራቴጂ – የረዥም ጊዜ ስልት ሲሆን፤ ታክቲክ የአጭር ጊዜ ስልት ነው።

ስለሆነም ስለ ISIS ወይም አልቃይዳ ስጽፍ ድርጅቶቹ ስለሚከተሉት እምነት አይደለም፤ የኔ ትኩረት ”የትግል ስትራቴጂያቸው“ ነው።

ወደ ዋናው ርዕሴ ልመለስ። አንዳንድ የህወሓት ወዳጅ የውጭ አገር ”ምሁራን“ ህወሓት ወደ ሽምቅ ውጊያ ሊመለስ ይችላል እያሉ ነው። “ሽምቅ ውጊያ” በቀጥታ በሽብርተኝነት ማዕቀፍ ውስጥ የማያስገባ የአመጽ ትግል ነው። እኔ ከዚህ የተለየ ሀሳብ አለኝ። ህወሓት የሚገኝነት ጂኦ ፓለቲካ ከባቢ በማጤን፣ ድርጅታዊ ባህሉ፣ አቅሙና ልምዱ እግምት ውስጥ በማስገባት ህወሓት ልክ እንደ ISIS፣ አልቃይዳ እና ቦኮ ሀራም ዓይነት ሽብርተኛ ድርጅት ይሆናል። ህወሓት አቅም እስካለው ድረስ ከተሞችን በሚሳይል ከመደብደብ፣ ሕዝብ በበዛባቸው ቦታዎች ፈንጂዎችን ከማፈንዳት የሚያቅበው የሞራልም ሆነ የድርጅታዊ ባህል ልጓም የለበትም። በክፋት ከቀድሞዎቹ መሪዎች የባሱ ወጣት መሪዎች ከህወሓት ወጣት ክንፍ፣ ዓባይ ትግራይ፣ ትግራይ ነጻነት እና ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ይወጣሉ። ይህንን ሽብርተኛ ድርጅት ለመተባበር የሚፈቅዱ ቡድኖች በሁሉም ክልሎች ውስጥ አሉ። ISIS እና አልቃይዳም ወደዚህ ማትኮራቸው አይቀርም።

ስለሆነም የደህንነቱ መስሪያ ቤት ወገቡን ጠበቅ ያድርግ። በምርጫ ለመወዳደር የሚዘጋጁትን ፓርቲዎችን ለመሰለል የሚያጠፋውን ጊዜና ሀብት ቀንሶ ይህ አደጋ ስር ከመስደዱ በፊት ይከላከል። አደጋው ለቀጠናው አገሮች በሙሉ በመሆኑ የቀጠናው አገሮች ትብብር መጠናከር ይኖርበታል። በተለይ ደግም ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ጁቡቲ ግኑኝነታቸውን ከፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

የፀረ-ሽብር ትግሉ ከወታደራዊ መፍትሄ በተጨማሪ የፓለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ገጽታዎች ሊኖሩት ይገባል። ሽብርተኝነት አክሳሪ ስትራቴጂ ማድረግ የሚቻለው ፓለቲካችንን ከዘርና ከሀይማኖት መካረር ነፃ ስናደርገው ነው። የሰላም ሚኒስትር እጅግ ብዙ ኃላፊነቶችን ተሸክሟል፤ ለሸክሙ የሚመጥን ትከሻ ይኑረው። የእርቀሰላም እና የድንበርና የማንነት ኮሚሽኖችም ሥራ ይስሩ። ሲቢክ ማኅበረሰቡና ኃላፊነት የሚሰማን ዜጎች ሁሉ ለጊዜው መንግስትን ማጨናነቅ ትተን እንደግፈው።

የተገኘው ድል፤ ትልቅ ድል ነው – ሆኖም አንዝናና፣ አንዘናጋ !

ምንጭ : Tadesse Biru Kersmo