18 ግንቦት 2021, 11:28 EAT

የኢትዮጵያ መንግሥት ከአጋር አገራት እየቀረበለት ያለውን ‘ከህወሓት ጋር ተደራደሩ’ የሚሉ ምክረ ሐሳቦች በፍጹም እንደማይቀበል በድጋሚ አስታወቀ።
ይህ የተገለጸው የኢፌድሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ ነው።
ሚኒስቴሩ ከአጋር አገራት ጋር በቅርብ መሥራቱን እንደሚቀጥል በመግለጫው አረጋግጦ ሆኖም ግን፤ እጅ ለመጠምዘዝ የሚሞክሩ ያላቸውን መንግሥታትን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና የአገሪቱን ሉዓላዊነት እንዲያከብሩ አስጠንቅቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚህ ጠንከር ያለ መግለጫው በኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን የሚያስገቡ የውጭ መንግሥታትን የኮነነው የሚነሱበትን ክሶች በአምስት ፈርጅ በመክፈል አንድ በአንድ ከዳሰሰ በኋላ ነው።
- ኢዜማ የምርጫው መራዘም ‘ምክንያታዊ’ ነው ሲል ባልደራስ በበኩሉ ‘ማብራሪያ እፈልጋለሁ’ አለ
- የምርጫው መራዘም የቆሰቆሳቸው ስጋቶች
- ናይጄሪያ ጽንፈኛውን ቦኮ ሃራምን ‘ማስወገድ’ ያልቻለችባቸው 6 ምክንያቶች
የኢትዮጵያ መንግሥት በርካታ ጊዜ ከእነዚህ መንግሥታት ጋር በበጎ ስሜት ለመነጋገር መሞከሩን ያስታወሰው መግለጫው፤ ነገር ግን ከአጋር አገራት ተመሳሳይ ስሜት ባለማየቱ አጋር የሚባሉ አገራትን እውነተኛ ፍላጎት ለመጠራጠር እየተገደደ መምጣቱን ያወሳል።
አጋር አገራት ኢትዮጵያ በተጨባጭ ያለችበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመረዳት አለመሞከራቸውን እና ከዚያ ይልቅ ችግሩን የሚያባብሱ ሆነው መገኘታቸውንም ይዘረዝራል።
እነዚህ በስም ያልተገለጹት አጋር አገራቱ በሐሰተኛ ሚዲያዎችና ዜናዎች እየተመሩ ወደተሳሳተ አቅጣጫና ድምዳሜ እየሄዱ እንደሆነም ይጠቅሳል።
ይህም በመሆኑ መንግሥት በ5 ጉዳዮች ላይ የማያሻማና ግልጽ መልእክት ማስተላለፍ አስፈልጎታል ሲል እነዚህን አንኳር የተባሉ ጉዳዮችን ይዘረዝራል።
እነዚህ አንኳር የተባሉት ጉዳዮች በዋናነት በትግራይ ስላለው ሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት፣ በአገሪቱ የለተያዩ አካባቢዎች እየተፈፀሙ ነው ስለሚባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ ከህወሓት ጋር የተኩስ አቁም ስለማድረግና በጠረጴዛ ዙርያ ንግግር እንዲጀመር የሚቀርቡ ውትወታዎች እና የመብት አራማጆችን ድምጽ ስለማፈን በተነሱ ጉዳዮች ዙርያ ዘርዘር ያሉ ማብራሪያዎች በመግለጫው ተካተውበታል።
የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት
መንግሥት ሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ላይ ያለውን ዝግጁነት ብቻም ሳይሆን ቆራጥነቱን በሥራ አሳይቷል የሚለው መግለጫው፤ በትግራይ ለሚዳረሱ ሰብአዊ ድጋፎች ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሙሉ አጋርነት መስጠት ብቻም ሳይሆን በመላው ትግራይ ገብተው እንዲሰሩም ፈቅዷል ይላል።
መግለጫው እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ አሁንም ሰብአዊ ድጋፍ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መድረስ አልቻልንም ብለው መናገራቸው ከእውነት የራቀ ነው ብሏል።
በደኅንነት ስጋት የተነሳ አንዳንድ አካባቢዎች ለሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት ምቹ እንዳልሆኑና ይህንንም ድርጅቶቹ እንደሚረዱ አብራርቷል። ሀቁ ይህ ሆኖም ዓለም አቀፍ ሰብአዊ ድጋፍ ሰጪዎች ተመሳሳይ ቅሬታ ማቅረባቸው እንዳሳዘነው ገልጧል፡፡
የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች
የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተም የሚደርሱትን ቅሬታዎች ለማጣራት በፌዴራል ዐቃቤ ሕግ እና በፌዴራል ፖሊስ የሚመራ ቡድን መቋቋሙን፣ ምርመራ ለማድረግም ወደ ትግራይ ማቅናቱን አስታውሶ፤ የምርመራ ውጤታቸውን ባለፈው ሳምንት ይፋ ማድረጋቸውን ገልጧል። በዚህም ጥፋተኞች ተጠያቂነት እንደሚኖርባቸው ማረጋገጡን አስምሮበታል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የማይካድራ ጭፍጨፋን ጨምሮ በርካታ ምርመራዎችን አድርጎ መግለጫ ያወጣ መሆኑን አውስቷል።
- ባይደን እስራኤል እና ፍልስጤም የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ጠየቁ
- የዞን አመራርን ጨምሮ በምዕራብ ኦሮሚያ 5 ሰዎች በታጣቂዎች ተገደሉ
- የፕሬዝደንት ባይደን ዓመታዊ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱ ተነገረ
ከዚህም ባሻገርም መግለጫው ኢሰመኮ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጀት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በቅንጅት ምርመራ ለማድረግ መስማማቱንም አስታውሷል።
በኢትዮጵያ መንግሥት ግብዣ የአፍሪካ ኅብረት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ራሱን የቻለ ምርመራ እያደረገ እንደሆነም ጠቅሶ፤ ይህ ሁሉ እየሆነ ባለበት ሁኔታ ኢትዮጵያን ቸልተኛ እንደሆነች አድርጎ መክሰስ ፖለቲካዊ ጫና ለማሳደር ከመሻት የመነጨ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም ብሏል የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ።
ግጭት ይቁም
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ በተለይ ግጭት እንዲቆም ከስምምነት እንዲደረስ እና ብሔራዊ ምክክርን በተመለከተ የውጭ መንግሥታት እየሰነዘሩ ያሉትን ሐሳብ ክፉኛ ተችቷል።
ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ከሲቪል ማኅበረሰቡና ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራንና የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ንግግሮችን እያደረገ ያለበት ሁኔታን በዝርዝር ጠቅሶ፤ ነገር ግን አጋር አገራት መንግሥት ከህወሓት ጋር ንግግር እንዲጀምር ግፊት ማድረጋቸው በጭራሽ ተቀባይነት እንደሌለው አትቷል።
ፓርላማው ድርጅቱን በአሸባሪነት በፈረጀበት ሁኔታ ከህወሓት ጋር በጠላትነት መተያየቱ እንዲቀርና ድርድር እንዲጀመር የሚጠይቁ አጋር መንግሥታትን ተደጋጋሚ ጥያቄዎቻቸውን በፍጹም እንደማይቀበል የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
“ህወሓት ሕገ-ወጥ ቡድን ነው። የአገሪቱን ሉዓላዊነት አደጋ ውስጥ የከተተና ሕገ-መንግሥቱን የጣሰ ቡድን ነው። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ቡድን ተርታ ውስጥ እንዲገባ ወስኗል። ለዚህም ነው የኢትዮጽያ መንግሥት የአጋር አገራትን ግጭት ቆሞ ከህወሓት ጋር የተደራደሩ ጥሪ በፍጹም ሊቀበለው የማይችለው” ይላል መግለጫው።
መግለጫው አንዳንድ አጋር መንግሥታት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባታቸውን እንዲያቆሙም ጠይቋል።
በተለይም የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን በተመለከተ የሚሰነዘሩ ሐሳቦችን እንደማይቀበል የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ገልጧል።
“ኢትዮጵያ ሉዓላዊት አገር ናት። የራሷን የጸጥታ ኃይልና ሠራዊት በግዛቷ በፈለገችው ሁኔታና መልክ ማሰማራት ትችላለች። የአማራ ልዩ ኃይል በትግራይ መሰማራትም በዚህ አግባብ የተፈጸመ ነው” ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በጋራ ጉዳዮች ላይ አሁንም ቢሆን ከአጋር መንግሥታት ጋር ለመነጋገር ዝግጁ ቢሆንም እጅን ለመጠምዘዝ የሚሞከሩ ሁኔታዎች የሚቀጥሉ ከሆነ ግን ይህን ግንኙነት በድጋሚ ለማጤን ይገደዳል ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ።