
አሜሪካ ኢትዮጵያን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ጋር በመሆን ገንቢ ሚናዋን እንድትወጣ የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት ጠይቋል፡፡
ምክር ቤቱ ለአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጻፈው ደብዳቤ፣ የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት እና ነጻነት ባከበረ መልኩ አሜሪካ እንድትንቀሳቀስ ጠይቋል፡፡
በኢትዮጵያ የተካሄደው የህግ ማስከበር እና የህልውና ዘመቻ በሀገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ላይ የተቃጣ ጥቃትን ለመቀልበስ የተካሄደ መሆኑን የጠቀሰው ም/ቤቱ፣ እርምጃው የትኛውም ሐገር ሊያደርገው የሚችለው ስለመሆኑ ገልጿል፡፡
ይህን የኢትዮጵያ መንግስት እርምጃ አሜሪካ ልትደግፈው ይገባል ያለው ም/ቤቱ፣ ቀጠናውን ለማተራመስ የሚሰራው እና በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው ሕወሃትን እና ደጋፊዎቹን በአይነ ቁራኛ እንድትከታተልም ጠይቋል፡፡
ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ አንዱ ማሳያ የሆነውን ምርጫ ለማድረግ እየሰራች ብትገኝም ይህ ምርጫ እንዳይካሄድ የሚጥሩ እና ጣልቃ ለመግባት የሚሞክሩ ኃይሎችም ሥራ ተገቢነት የሌለው መሆኑን ም/ቤቱ አስታውቋል፡፡
ም/ቤቱ ለአሜሪካ ፕሬዝዳንት በጻፈው ደብዳቤ ኢትዮጵያ ለምታደርገው ሀገራዊ ምርጫ፣ ለሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ያላትን ድጋፍ እንድትሰጥ እና በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል ያለው የድንበር ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ እንዲሁም በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል ለሚካሄደው የመልሶ ግንባታ እና የሰብዓዊ ድጋፍ እንድትደግፍ ጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ እና አሜሪካ ግንኙነት በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በነበሩት ቴዲ ሩዝቬልት ዘመን ተጀምሮ ለ115 ዓመታት መዝለቁን ያነሳው ም/ቤቱ፣ ይህ ግንኙነት አሁንም ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሜሪካ ገንቢ ሚናዋን እንድትወጣ ሲል ጠይቋል፡፡


