26 ግንቦት 2021, 12:39 EAT

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ አርማ
የምስሉ መግለጫ, የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ

በትግራይ ክልል ውስጥ በርካታ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አባላት በህወሓት በተፈጸመባቸው ጥቃት መገደላቸውን፣ መቁሰላቸውን እና ታፍነው መወሰዳቸውን መንግሥት ገለጸ።

የአስቸኳይ ጊዜ መረጃ ማጣሪያ ማዕከል ያወጣው መግለጫ፤ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከተቋቋመ በኋላ በተለያዩ አካባቢዎች በአስተዳደሩ አባላት ላይ በህወሓት በተፈጸሙ ጥቃቶች 22 ሰዎች መገደላቸውን አመልክቷል።

በተጨማሪም በአራት የጊዜያዊው አስተዳደር አባላት ላይ በተፈጸመባቸው ጥቃት ጉዳት ደርሶባቸው በህክምና ላይ እንደሚገኙ ማዕከሉ ያወጣው መግለጫ ጠቅሷል።

በዚህም ሳቢያ በአጠቃላይ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 46 የጊዜያዊው አስተዳደር ሲቪል አባላት በህወሓት ኃይሎች ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ተገልጿል።

መግለጫው ጨምሮም በክልሉ መረጋጋት በማምጣት ሕዝቡ ወደ መደበኛው ሕይወት እንዲመለስ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ ባሉት የጊዜያዊ አስተዳደሩ አባላት ላይ ቡድኑ ከሚፈጽመው ጥቃት ባሻገር በንብረት ላይም ውድመት መድረሱን ጠቅሷል።

መግለጫው በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ውስጥ በህወሓት ኃይሎች ጥቃት ተፈጸመባቸው ያላቸውን የጊዜያዊውን አስተዳደር አባላት ቁጥር በዝርዝር ያወጣ ሲሆን፤ ከፍተኛው ግድያ የተፈጸመው በሰሜን ምሥራቅ ክፍል ውስጥ ዘጠኝ ሰዎች የተገደሉበት መሆኑን አመልክቷል።

ከዚህ ባሻገርም በማዕከላዊ ዞን 6፣ በደቡብ 3 እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ አንድ አንድ የጊዜያዊው አስተዳደር አባላት ተገድለዋል ይላል መንግሥት ያወጣው መግለጫ።

በተጨማሪ ደግሞ በደቡብ ዞን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጊዜያዊው አስተዳደር አባላት የታፈኑ ሲሆን ቁጥራቸውም ዘጠኝ ነው። በሌሎች ቦታዎች ደግሞ በደቡብ ምሥራቅ 5፣ በማዕከላዊ 4 እና በምሥራቅ 2 የአስተዳደሩ አባላት ታፍነዋል ተብሏል።

ከጊዜያዊ አስተዳደሩ አባላት መካከልም በህወሓት ተፈጸመባቸው በተባለው ጥቃት አራት ሰዎች በተለያዩ ዞኖች ውስጥ የመቁሰል ጉዳት እንደደረሰባቸው መግለጫው አመልክቷል።

ለሦስት አስርት ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣን ላይ ከፍተኛ ሚና የነበረው ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገሪቱ የመጣውን የአመራር ለውጥ ተከትሎ ዋነኛ ማዕከሉን ትግራይ ውስጥ አድርጎ ቆይቶ ነበር።

ህወሓት ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር የነበረው አለመግባባት የአገራዊውን ምርጫ መራዘም ተከትሎ በትግራይ ክልል ውስጥ በተናጠል ባካሄደው ምርጫ ሳቢያ የፌደራል መንግሥቱ በወሰደው እርምጃ የበለጠ ተባብሶ መቆየቱ ይታወሳል።

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የህወሓት ኃይሎች ትግራይ ውስጥ በነበረው የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ላይ የፈጸሙትን ጥቃት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ካዘዙ ከሳምንታት በኋላ ህወሓት ከ30 ዓመታት በላይ ከተቆጣጠረው የክልሉ የሥልጣን መንበር ተወግዷል።

በዚህም በርካታ ከፍተኛ አመራሮቹ በውጊያዎች ውስጥ መገደላቸውና በፌደራል መንግሥቱ መያዛቸው አይዘነጋም።

ቢሆንም ግን ቡድኑ አሁንም ድረስ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ጥቃት እየፈጸመ እንደሆነ ከዚህ በፊት የሚወጡ መረጃዎች ያመከቱ ሲሆን፤ አሁን ከመንግሥት በኩል የወጣው ቡድኑ የፈጸማቸው ግድያዎችና ጥቃቶችን የሚያመለክተው መረጃ ይህንኑ ያረጋግጣል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይን (ህወሓት) የሽብር ቡድን ብሎ መሰየሙ ይታወሳል።