May 27, 2021


የሕግ ባለሙያ ውብሸት ሙላት

(ምርጫ ቦርድ የሕግ የበላይነትን ካላከበረ፣ የፍርድ ቤት ውሳኔን ካልተቀበለ ሌላ ማን ያክብር፣ ማን ይቀበል?!)

No photo description available.

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የቦርድ አባላት “አንቱ” የተባሉ የሕግ ባለሙያዎችን ይዟል። በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ያልተባሉ ሰዎችን በወንጀል ተጠርጥረው በማረፊያ ቤት ስላሉ ብቻ “የምርጫ ተወዳዳሪ እጩ አድርጌ አልመዘግብም፤ ጥፋተኛ ቢባሉ ለሚወዳደሩበት ምክር ቤት በመግባት ወይም በመገኘት ሕዝባዊ ውክልናቸውን መወጣት ስለማይችሉ” የሚል ይዘት ባለው ምክንያት አልመዘግብም ማለቱ ከሕግ አተረጓጎም አንጻር በአሉታ አስገርሞን ነበር።

እንደ ክሱ ጥፋተኛ ተብለው እስራት ከተፈረደባቸው (ከታሠሩ) እና በምርጫ ውድድሩ አሸንፈው የምክር ቤት አባል ከኾኑ፣ ሕጉ ግልጽ መፍትሔ አለው-የማሟያ ምርጫ። ምርጫ ቦርድም ማድረግ ያለበት ይሔንኑ ነው። የማሟያ ምርጫ፣ የምክር ቤት አባላት የኾነ ሰው ሲሞት፣ በወንጀል ተከሶ ሲታሠር፣ ውክልናው ሲነሳ ወዘተ ይደረጋል። በሕግ ነው እንዲህ የተባለው።

ከተመረጡ በኋላ እስራቱ ከቀጠለ ድጋሜ የማሟያ ምርጫ በሚል ለምን እለፋለሁ፣ እደክማለሁ በሚል ሰበብ ይመስላል በዕጩነት ያልመዘገቡት። (ወርቁን ትተነው ቢያንስ ሰሙ።)

አሁን ደግሞ የባሰው መጣ። ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር ሰሚ ችሎት የወሰነውን፣ ትእዛዝ የሰጠበትን “የመምረጫ ካርዶችን ስላሳተምኩ፣ በታተመበት ወረቀት ላይ የእጩዎቹ አቀማመጥ ማን ቀድሞው ማን ይከተል ለሚለው እጣ ስላወጡ በእጩ ተወዳዳሪነት ለመመዝገብ እቸገራለሁ በሚል የሕግ ባለሙያ የኾኑት የቦርድ አባላት “አስደምመውናል”። ድጋሜ የምርጫ ካርድ አላሳትምም። ወይም ለማሳተም ይቸግረኛል በሚል። ወረቀት አላባክንም ዓይነት ሰበብ ይመስላል።

ፍርድ ቤቱ ለአራት ሰዎች ውሳኔ የሰጠው። አራቱም የተለያዩ የምርጫ ወረዳዎች ከኾነ የሚወዳደሩት ምርጫ ቦርድ በድጋሜ የሚያሳትመው (ኅትመቱ አልቆ ከኾነ ማለት ነው) ለአራት የምርጫ ወረዳዎች ብቻ መኾኑን ልብ ይሏል።

የአፈጻጸም ክስ ለፍርድ ቤቱ ሲቀርብ ውጤቱን የምናየው ቢኾንም (ይህንን ፍርድ ማስፈጸም እምብዛም አስቸጋሪም ከባድም ስላልሆነ) የምርጫ ቦርድ ምላሽ ግን ከሕግ አንጻር ሲመዘን፣ ሚዛን ላይ ለመውጣት ወይም ለመቀመጥ እንኳን የማይችል ነው። ከጅምሩ ለመመዘንም አይበቃምና።

[ እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎች (ምላሾች) ሕዝብ ምርጫ ቦርድ ላይ ያለውን አመኔታ የሚሸረሽሩ ብቻ ሳይሆኑ ሙልጭ አድርጎ የሚያሳጡ ናቸው። ሕዝብን ተስፋ ያስቆርጣልም።