May 27, 2021


አሜሪካና አውሮፓ ሲፈልጉ እንጂ ስንፈልግ ረድተውን አያውቁም!  (በድሉ ዋቅጅራ ዶ/ር))

አገራችን በጣልያን ስትወረር የአለም መንግሥታት በኢትዮጵያ ላይ የጦር መሣርያ ግዢ ማዕቀብ ጥለዋል፡፡ የሚፈልጉት ኢትዮጵያም እንደመላው አፍሪካ በቅኝ ግዛት ስር እንድትወድቅ ነበር፡፡ የእኛ ነጻነት ፍላጎታቸው አልነበረም፡፡ እንደፍላጎታቸው አደረጉ፡፡ አሸንፈን ነጻነታችንን አስጠበቅን፡፡ ጥርሳቸውን ነከሱብን፡፡

ኢትዮጵያ ላለፉት 15 ዓመታት በአመት ከሰባት መቶ ሺሕ ቶን በላይ የምግብ እህል እርዳታ ተቀብላለች፡፡ አብዛኛው ከምእራባውያን የተገኘ ነው፡፡ እነዚህ አገራት ዓባይን ለመገደብ ሳንቲም ለመስጠት ፍቃደኛ አልነበሩም፡፡ ፍላጎታቸው በእለት ጉርስ ሊለጉሙን ነው፤ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ተግብረን ከልጓማቸው እንድናመልጥ አይፈልጉም፡፡ ከሌለን ቆንጥረን ዓባይን ገደብን፡፡ የስንዴ ልጓማቸው ሲላላ – ሲወልቅ ታያቸው፤ ዛሬም ማእቀብ ጣሉብን (በነገራችን ላይ የአውሮፓ ኅብረትም አሜሪካን እንደሚከተል አዝማሚያው ያመላክታል)፡፡ ከቅኝ ግዛት ቀንበራቸው አምልጣ የነጻነት ምሳሌ የሆነችው ሀገራችን፣ ከድህነት ወጥታ እራስን የመቻልና የ”እንቢባይነት” ምሳሌ እንድትሆን አይፈልጉም፡፡

በ1969 ዓ.ም. ሱማልያ ስትወረንም አሜሪካ ከወራሪዎቻችን ጋር ነበረች፡፡ በሶቭየት ኅብረት እና ኩባ እርዳታ በድል ተወጣነው፡፡

አሜሪካ በሱማልያ ታላቅ ውርደት ከገጠማት በኋላ፣ ጦርነቷን እኛ እንድንዋጋላት ፈለገች፡፡ ስለፈለገች ዶላር ሰጠችን፤ መሳሪያ አስታጠቀችን፤ መድሀኒትና ስንዴ አፈሰሰችብን፡፡ ከሩብ ምእተአመት በላይ ጦርነቷን ተዋጋንላት፡፡ ሞቷን ሞትንላት፡፡ ዛሬ “አፍሪካውያን ተገቢ ቦታችን ያለንበት አይደለም፤ አፍሪካውያን መተባበር አለባቸው፤ እራሳቸውን መቻል አለባቸው፤” እያለ የሚፎክር መሪ በኢትዮጵያ መጣ፡፡ ዛሬ “ተላላኪ መንግሥት በኢትዮጵያ ከእንግዲህ አይኖርም፤ ለአገሬ ጥቅም ግንባሬን እሰጣለሁ” የሚል መሪ መጣ፡፡ ይህ የምእራባውያን ፍላጎት አይደለምና ያሳስባቸዋል፤ እንቅልፍ ይነሳቸዋል፡፡ እንቅልፍ የሚነሳቸው የመሪዎች አንባገነንነትና ዲሞክራትነት አይደለም፤ ይህ ለእነሱ የመጫወቻ ካርድ ነው፡፡

ዛሬ እውን በትግራይ ሕዝብ ላይ የደረሰውና እየደረሰ ያለው አስከፊ ችግር አሳስቧቸው ቢሆን ኖሮ፣ በየመግለጫቸው ለዚህ ጥፋት ከዳረገው ሕወሓት ጋር ጎን ለጎን አይጠቅሱትም ነበር፡፡ ሕወሓት በሰሜን እዝ ላይ ያደረሰውን ጥቃት፣ በማይካድራ የጨፈጨፋቸውን ንጹሀን ዜጎች አያስታውሱን፡፡ ምክንያቱም ፍላጎታቸው የሰብአዊ መብት መከበር፣ የፍትሕና ሰላም መጠበቅ አይደለም፡፡ ፍላጎታቸው ታዛዥ መንግስት እንዳለ ማረጋገጥ፣ ኢትዮጵያን በስንዴ ልጓማቸው እስከዘለአለም መጎተት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እውነት፣ ፍትሕና ሰብአዊነት ቢንኮታኮት ደንታቸው አይደለም፡፡ ከድሃ አገራት ጋር ያላቻው ታሪክ የሚመሰክረውም ይህን ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን ድሆች ነን፡፡ የምዕራባውያን ፍላጎት ፍላጎታችን እስካልሆነ ድረስ የእኛ ፍላጎት ፍላጎታቸው እንደማይሆን ማወቅ አለብን፡፡ ፍላጎታችንን ፍላጎታቸው ማድረጉ አይደለም ትልቁ ቁምነገር፡፡ ትልቁ ቁምነገር ለፍላጎታችን እውን መሆን አንድ ሆነን መነሳት፣ መሥራት ነው፡፡ አባቶቻችን መስዋእትነት ከፍለው ነጻ አገር ሰጥተውናል፡፡ እኛ ልዩነታችንን መፍታት ቢያቅተን እንኳ አጥበን፣(ያም ካቃተን ለጊዜው ችላ ብለን)፣ ሬትን ተጎንጭተን፣ ተግተንና ተባብረን ለልጆቻችን በነጻነት ላይ ራስን መቻል ጨምረን አገራችንን ለማስተላለፍ እንጀግን ዘንድ ጊዜው ዛሬ ነው፡፡ አገራችን በአሜሪካና ሌሎች ጣልቃ ገብነት እንድትጨልም አንፈቅድም፤ ኢትዮጵያ ለልጆቻችን፣ ለልጆቻቸው፣ ለልጅ ልጆቻቸው . . . ለዘለዓለም መንጋት አለባት፡፡

Source – Sirara