ከ 8 ሰአት በፊት

ኤምአይ5 (MI5) የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የስለላ ድርጅት ነው።
ቢቢሲ ሕግን ላለመተላለፍ ሲል ስሙን ለጊዜው የማይጠቅሰው የዚህ ታሪክ ባለቤት የስለላ ድርጅቱ አባል ነው።
ለስለላ ሥራ ወደ ሌላ አገር ከመላኩ በፊት ታዲያ ሴቶችን ለከፍተኛ ሥነ ልቡናዊና አካላዊ ስቃይ መዳረጉን ቢቢሲ ባከናወነው በዚህ የምርመራ ጋዜጠኝነት አረጋግጧል።
ይህ ዘገባ በሰላዩ የተሰቃዩትን ቤቲ እና ሩት ላይ ብቻ አተኩሯል።
ቤቲ የለግሰቡ የፍቅር ጓደኛ ሆና ቆይታለች። ጨርቋን እስክትስት ድረስ ለሥነ ልቡና ስቃይ ዳርጓታል።
የዚህን ሰላይ ገመና ለማጋለጥ ቢቢሲ ረጅም ርቀት ሄዷል።
ሆኖም ዘለግ ካለ ምርመራ በኋላ ያጠናቀረውን ዘገባ ለማተም በዝግጅት ላይ ሳለ ጽሑፉ ለሕዝብ እንዳያደርስ በዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ጥያቄ ቀርቦለታል።
ቢቢሲ ይህን ዘገባ እንዳያትም ፍርድ ቤት ተከሶ የነበረ ሲሆን በመጨረሻ ግን ሙግቱን በመርታቱ ዘገባው እነሆ ሊቀርብ ችሏል።
የእንግሊዙ ሰላይ ማን ነው?
ቢቢሲ የሰላዩን እውነተኛ ስም ለመጥቀስ ፍርድ ቤት አልፈቀደለትም። በጠላት እጅ እንዳይወድቅ በመስጋትና ከሥራው ባህሪ አንጻር ነው ገደቡ የተቀመጠበት።
ሆኖም የቢቢሲ ምርመራ እንዳረጋገጠው ግለሰቡ በፖለቲካ አቋሙ ቀኝ አክራሪ፣ በባህሪውም ፍጹም ሞገደኛ የሚባል ነው።
መጤዎችን፣ ጥቁሮችንና አይሁዶች አምርሮ ይጠላል።
ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ስሟ የተቀየረላት ቤቲ የብሪታኒያ ዜጋ ናት።
ከዚህ ሞገደኛ ሰላይ ጋር ትውውቅ የፈጠረችው በፍቅር አሰናኝ መተግበሪያዎች አማካኝነት ነው።
መጀመሪያ አካባቢ የተረጋጋና የፍቅር ሰው ሆኖ ነበር ያገኘሁት ትላለች።
እየቆየን ስንመጣ ግን እውነተኛ ማንነቱ እየተገለጠ መጣ።

“በአጠቃላይ ለሴት ልጅ ከፍተኛ ንቀትና ጥላቻ ያለው፣ በፖለቲካ አመለካከቱ ነጭ አክራሪ የሆነ፣ ደሙ በጥላቻ የተሞላ ሰው ነው” ትላለች ቤቲ።
ይህ ሰላይ ከቤቲ ጋር በኖረበት ወቅት ሕይወቷን የገሀነብ አምሳያ አድርጎት ቆይቷል።
ከሁሉም በላይ አነጋጋሪ የሆነው ጉዳይ ታዲያ ቤቲ ይህን ጾታዊ ጥቃት ወደ ሕግ ለመውሰድ አለመቻሏ ነው።
ሕግን ስታስብ የሰላይነቱን መለያ መዞ ያስፈራራታል። እሱን መክሰስ ከንቱ እንደሆነም አሳምኗታል።
“በሙሉ ቁጥጥሩ ሥር አዋለኝ፤ ያን ነበር የሚሻው፤ እኔ ለእሱ ሰው ሳልሆን ጥላ ነበርኩ” ትላለች ቤቲ።
ግንኙነታቸው እየቆየ፣ ሥነ ልቡናዊ ጉዳቱ እየሰፋ ሄደና የቤቲ የአእምሮ ጤና በከፍተኛ ሁኔታ እየተሸረሸረ መጣ።
“የት እንደምሄድ፣ ማንን እንደማገኝ፣ ምን እንደምሠራ እያንዳንዷን እንቅስቃሴዬን ይቆጣጠር ነበር።”
- ከመጋረጃ ጀርባ የሚካሄደው የሩሲያና የምዕራባውያን ሰላዮች ጦርነት
- የጃፓን ወንዶች በሚስቶቻቸው ላይ ለምን ሰላይ ይቀጥራሉ?
- የቀድሞው የእስራኤል ሰላይ ሞሳድ ኢራን ላይ ያካሄዳቸውን ዘመቻዎች አጋለጡ
ቤቲ የአእምሮ ጤናዋ ይበልጥ አሳሳቢ እንዲሆን ያደረገው ሰላዩ አንድ ጥቃት በመፈጸም አይደለም። በተደጋጋሚ አእምሮዋን በማወክ እንጂ።
ለምሳሌ ሽጉጥ ግንባሯ ላይ በመደገን አብሯት ይቀመጣል። ከዚያም የአእምሮ ጤናን የሚያውኩና ከሥራው ጋር የሚያያዙ አሸባሪዎ የሚፈጽሙትን ግድያ በቪዲዮ እንድትመለከት ያደርጋታል።
ቤቲ ቁጥጥሩና ስቃዩ ከልክ በላይ ሲሆንባት ጉዳዩን ወደ ሕግ ለመውሰድ ቆርጣ ትነሳለች።
ሆኖም ይህን እሷ ማድረግ እንደማትችል ይነግራታል። ምክንያቱም እሱ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ሰላይ በመሆኑ ማንኛውም ክስ ውድቅ እንደሚሆን በዝርዝር በማስረዳት ተስፋ እንድትቆርጥ አድርጓል።
በሌላ ቀን ደግሞ ቀኝ አክራሪዎች የሚፈጽሟቸውን አሰቃቂ ግድያዎች እያዳነቀ ያወራል። እሱም አንድ ቀን ተመሳሳይ ግድያ የመፈጸም ጉጉት እንዳደረበት ይነግራታል።
እንዲያውም እሷን በመግደል ነገሩን እንደሚጀምረው ኮስተር ብሎ እየነገራት ዕቅድ ያወጣል።
የቤት ውስጥ ጥቃት በየቀኑ ያደርስባት ነበር።
አንድ ዕለት ታዲያ ገጀራ ይዞ መጣ። ጥቃት ሊፈጽምባት እንደሆነ ነገራት። በድብቅ ካሜራ ደቅና ነበር።
በገጀራ ጭንቅላቷን ሊፈልጥ ሲዘጋጅ ድርጊቱን እየቀረጸችው እንደሆነ ትናዘዛለች። በዚህ ጊዜ ገጀራውን ትቶ በቡጢ ይነርታል ጀመር።
ቢቢሲ እጅ የገባው ተንቀሳቃሽ ምሥል ልክ እዚህ ቦታ ላይ ያቆማል። እሷ ስታለቅስ፣ ሰላዩ ሲያምባርቅባት ይሰማናና ይቋረጣል።
ቤቲ ግን ታሪኩ በዚህ እንዳላበቃ ትናገራለች።
በሌላ ቀን ካራ ይዞ በመምጣት እንደ ዶሮ አንገቷን ቀንጥሶ እንደሚጥለው እየዛተ ሲያስፈራራት እንደነበር ቤቲ ለቢቢሲ ተናግራለች።
ከብዙ ጥረት በኋላ ቤቲ ክስ መሠረተች።

የፖሊስ ምርመራና ጥርጣሬ
ፖሊስ ጥቃቱን ተከትሎ መኖርያ ቤታቸውን ያሰሰ ሲሆን ቢቢሲ ባገኘው መረጃ የፖሊስ ምርመራው ግድፈት እንዳለበት ተረድቷል።
በመጨረሻ ይህ ግለሰብ ተከሶ ፍርድ ቤት መቅረብ ቢችልም ዐቃቤ ሕግ ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ ክሱን አንስቷል።
ክሱ ከተቋረጠ በኋላም ሰላዩ ተመልሶ በመምጣት ቤቲን ማስፈራራቱን ቀጥሎበታል።
ፖሊስ የቤቲን ቃል ለመውሰድ አልሞከረም። ጥቃት ሲያደርስባት የሚያሳየውን ምሥልም ለምርመራ አልተጠቀመበትም።
ክሱ የተቋረጠውም በውል ባልታወቀ ምክንያት ነበር።
- የእስራኤሉ የስለላ ተቋም ሞሳድ የኢራንን ጥብቅ የደኅንነት መዋቅር እንዴት ዘልቆ ገባ?
- የአሜሪካን የአቪዬሽን ንግድ ሚስጥርን ሰርቋል የተባለው ቻይናዊ ተቀጣ
- አሜሪካ ተማሪው የቻይና ሰላይ እንደሆነ እንዴት ደረሰችበት?
ቤቲ በሌላ ጊዜ በድብቅ በቀረጸችው ምሥል ሰላዩ እሱን ዳግም ለፖሊስ ብትከሰው ልትገደል እንደምትችል ሲያስረዳት ይታያል።
በተንቀሳቃሽ ምሥሉ ይህ ሰላይ እንዲህ ሲል ይሰማል።
“…ሰውን አንቆ የመግደል መንፈስ እኔ ውስጥ የኖረ ነው። ከ6 ዓመት ጀምሮ ይህ ስሜት አልተለየኝም። አደርገዋለሁ። አንድን ሰው መግደል አለብኝ። ደግሞም አደርገዋልሁ።”
ግንኙነታቸው ሊቋረጥም ሊቀጥልም ሳይችል በዚህ ሁኔታ የተወሰነ ጊዜ ከቆየ በኋላ፣ ሰላዩ ቤቲን ከጋራ መኖሪያቸው አስወጣት።
እሱም ተሰወረ። ለተወሰነ ጊዜም የት እንዳለ ሳይታወቅ ቀረ።
ከዚህ በኋላ ነበር ምርመራው በአዲስ መልክ እንዲጀመር የሆነው።
ፖሊስ ለሁለተኛ ጊዜ ባደረገው አሰሳ ሰላዩ ቤት ውስጥ የናዚ ሰነዶች እና የጥላቻ ወረቀቶች ተገኝተዋል።
አይሁዶችን የመግደል እቅድ እንደነበረውም ከግል ማስታወሻ ደብተሩ ላይ ሰፍሮ ተገኝቷል።
ከዚህም ባሻገር ቤቲን ለመግደል ዝርዝር ዕቅድ እንደነበረው በጽሑፍ አስፍሮ ነበር።
ቤቲ ይህ ምርመራ ሲካሄድ ለከፍተኛ የአእምሮ ጤና ቀውስ ተጋልጣ ሆስፒታል ገብታለች።
እሷ ሆስፒታል ሳለች ታዲያ አንድ ፀጉረ ልውጥ ወደ ቤቲ ወላጆች መኖርያ መጣ።
ምንም ትንፍሽ ሳይል የሰላዩን እና የቤቲን ንብረቶች ለቤተሰቦቿ መልሶ ተሰወረ። በዚህ ጊዜ ቤተሰቡ ተረበሸ።
ይህ ማንነቱን ያልገለጠው ግለሰብም የኤምአይፋይቭ ስለላ ድርጅት ባልደረባ እንደሆነ ቢቢሲ አረጋግጧል።
ይህ ብቻ አይደለም አስገራሚው ነገር። በፖሊስ ጭምር ለምርመራ ተወስደው የነበሩ ሰነዶች በሙሉ ለስለላ ድርጅቱ ተላልፈው እንደተሰጡ ቢቢሲ ደረሰበት።
ቤቲ ጤናዋ ተመልሶ ወደ ቤቷ ከተመለሰች በኋላ ስለምን ክስ እንደተቋረጠ፣ ለምን ማንነቱ ያልታወቀ ሰው ቤተሰቧ ዘንድ ሄዶ ንብረት እንደመለሰ ጥያቄ ያነሳች ሲሆን መልስ ግን ማግኘት አልቻለችም።

ሰላዩ የት ተሰወረ?
ቢቢሲ ባደረገው ምርመራ ይህ ሰላይ ከዚህ ክስተት በኋላ ወደ ሌላ አገር በመዛወር የስለላ ተግባር ውስጥ ሥራውን ቀጥሏል።
ቢቢሲ ሰላዩ ወደተመደበበት አገር በመሄድ ግለሰቡ ላይ ክትትል ያደረገ ሲሆን በዚያም አገር ተመሳሳይ ወንጀል ሲፈጽም ደርሶበታል።
የአገሩንም ስም መጥቀስ በሕግ አግባብ ተገቢ ሳላልሆነ ቢቢሲ ይህን ከማድረግ ተቆጥቧል።
ሆኖም በዚያ አገር የምትኖር የሰላዩ አዲስ ፍቅረኛ ልክ እንደ ቤቲ ሁሉ በተመሳሳይ ስቃይ ውስጥ እንደኖረች ቢቢሲ ተረድቷል።
ይህቺን ሴት ለደኅንነቷ ሲባል ሩት ተብላ በዚህ ታሪክ ውስጥ ተጠቅሳለች።
ሩትና ቤቲ በአንድ አገር አልኖሩም። ተደዋውለውም አያውቁም። ነገር ግን አንድ ሰላይ ወደው ሕይወታቸው ገሀነም ሆኗል።
ተመሳሳይ የስቃይ ጊዜን ከማሳለፋቸው የተነሳ የአንዷ ታሪክ ለሌላኛው ሲነገር አንድን ፊልም መልሶ የመተረክ ያህል ነው።
ይህ ሁሉ የሆነው በዚሁ ማንነቱን በሕግ ክልከላ ምክንያት በማይገለጸው የዩናይትድ ኪንግደም ሰላይ አማካኝነት ነው።
ሩት እንዲህ ትላለች፣ “መጀመሪያ ያወቅኩት ሰሞን ጤነኛና ደስ የሚል ሰው ነበር። ድንገት ወደ አውሬነት ተለወጠ። እኔንም ልጄንም እንደሚገድለን ይዝት ነበር። ሬሳችንን ማንም በማያገኘው ሥፍራ እንደሚጥለው በዝርዝር ያብራራልን ነበር።”
ቢቢሲ በግለሰቡ ማስታወሻ ላይ የሚከተለው ሐተታ ተጽፎ አግኝቷል።
“ደም ማፍሰስ እፈልጋለሁ፣ ነፍስ ማጥፋት እሻለሁ፣ የሰው ሥጋ መቦጫጨቅ ይናፍቀኛል፣ ሕጻን ልጅን ከነነፍሱ መብላት እፈልጋለሁ።”
ቢቢሲ ባገኘው ሌላ ማስታወሻ ይህ ሰላይ እንዲህ ሲል ጽፏል።
“ሴቶች ተደፍረው መገደል ያለባቸው ፍጡራን ናቸው።”
ቢቢሲ የሁለቱን ሴቶች ታሪክ፣ የሰላዩን ሞገደኝነት ይዞ ወደ መንግሥት አካል ቢወስድም መንግሥት ነገሩን ከመፈተሽ ይልቅ ዘገባው እንዳይታተም ለማስገደድ እግድ እንዲጣልበት ወደ ፍርድ ቤት ወሰደው።
ፍርድ ቤት የግለሰቡን ስም መግለጽ ለብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ሊሆን ስለሚችል ስሙን ሳይጠቀስ ዘገባው እንዲወጣ ፈቀደ።
ሩት አሁን በከፍተኛ ጭንቀት የአእምሮ ጤናዋ ተቃውሶ ሆስፒታል ገብታለች።
