October 9, 2023 – EthiopianReporter.com 


የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ዜና የፓርላማው ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ነገ ሰኞ ከሰዓት በኋላ ይጀመራል

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: October 8, 2023

ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ፣ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለሁለቱ ምክር ቤቶች የመንግሥትን የትኩረት አቅጣጫዎችን አስመልክተው በሚያደርጉት ንግግር ይጀመራል፡፡

ከሁለት ወራት የክረምት ዕረፍት የተመለሰው የምክር ቤቱ አባላት ያደሩና ከሚኒስትሮች ምክር ቤት የተላኩ ረቂቅ አዋጆች ላይ ውይይት በማድረግ፣ የአስፈጻሚውን አካል የ2016 ዓ.ም. ዕቅድና የሩብ ዓመት አፈጻጸም በመገምገም ወደ ሥራ ይገባል፡፡

በተመሳሳይ የፌደሬሽን ምክር ቤት ከዚህ በፊት መካሄድ የነበረባቸውና ሳይካሄዱ የቀሩ አገራዊና አካባቢያዊ ምርጫዎችን፣ እንዲሁም ለምክር ቤቱ በቀረቡ የሕዝበ ውሳኔ ጥያቄዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

በተጠናቀቀው የ2015 ዓ.ም. ለሁለት ዓመታት ያህል የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ደቡብ አፍሪካ  በፕሪቶሪያ ከተማ በተደረገው የሰላም ስምምነት ቢገታም፣ እንደ አዲስ ባገረሹ ግጭቶችና ጦርነት አገሪቱ እየታመሰች መሆኗ ይታወቃል፡፡

የሸቀጦች ዋጋ መናር፣ የገበያ አለመረጋጋት፣ የዜጎች መፈናቀል፣ የሰላምና የፀጥታ ችግር፣ በሕገወጥ መንገድ በየቦታው በተደራጁ ኃይሎች ምክንያት ዜጎች በሰላም   ከአንዱ ወደ ሌላው ቦታ ተንቀሳቅሰው መሥራት አለመቻላቸው፣ የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ በእሮሮ የተሞላ እንዲሆን ያደረጉ ሰንኮፎች በአዲሱ ዓመት መፍትሔ የሚሹ የመንግሥት ከባድ የቤት ሥራ ናቸው፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ መስከረም 28 ቀን 2015 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮችና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የመንግሥትን ዕቅድ ባቀረቡበት ወቅት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ዘርፎች የመንግሥትን የትኩረት አቅጣጫ ሲያስረዱ መንግሥት ሕዝቡን ያሳተፈ የፍትሕ ተቋማዊ ሪፎርም እንደሚያደርግና የሕዝቡን የፍትሕ ዕጦት ችግር ለመፍታት እንደሚሠራ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በተጨማሪም በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሥር የሰደደ ያሉትን የመልካም አስተዳደር ችግር ሰፊ፣ ጥልቅና ተግባር ተኮር ሥራ በማከናወን የችግሩ ምንጭ የሆኑ አሠራሮችንና ሠራተኞችን በመለየት ማስተካከያ እንደሚደረግ ተናግረው ነበር፡፡

በ2015 ዓ.ም. በጀት ዓመት የመንግሥት በጀት ድህነትን በፍጥነት ሊቀንሱ የሚችሉ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዘርፎች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ፣ እየጨመረ የመጣውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋትና ጤናማ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ ለመፍጠር በጥረት እንደሚሠራ ለጋራ ምክር ቤቶቹ ያስተላለፉት መልዕክት ነበር፡፡ አክለውም ግጭቶችን በውይይትና በድርድር በመፍታት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን ተግባር በመደገፍ፣ ሕዝቡን ካጋጠመው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለማላቀቅ ‹‹በከፍተኛ ሁኔታ የምንነሳበት ጊዜ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፤›› ብለው ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በንግግራቸው ተጀምሮ የተጠናቀቀው 2015 ዓ.ም. በጀት ዓመት አጠቃላይ አፈጻጸም ሲታይ፣ አገሪቱ ከአንዱ ግጭት ወደ ሌላ የግጭት የገባችበትና የኑሮ ውደነቱ ተባብሶ የቀጠለበት ጊዜ ስለመሆኑ በየጊዜው የሚሰማ የሕዝብ የብሶት ምንጭ ሆኗል፡፡ ለአብነትም በኩንታል 5,000 ብር ይሸጥ የነበረው ጤፍ ዋጋው ከሁለት እጥፍ በላይ ሲጨምር፣ የሽንኩርትና የቲማቲም ዋጋ ከእጥፍ በላይ ጨምሯል፡፡ አምስት ብር የነበረው የዳቦ ዋጋ አሥር ብር ገብቷል፣ የቤት ኪራይ ዋጋም አልቀመስ ብሏል፡፡

የሰላም ሁኔታውም እንደታሰበው ሳይሆን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚታዩት ግጭቶች መባባስ ያሳሰበቸው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት፣ የመብቶች ተሟጋቾች ድርቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ዓለም አቀፍ ተቋማትና አገሮች ሰላም እንዲወርድ ጥሪ እያቀረቡ መፍትሔ ሳይገኝ አዲሱ ዓመት ገብቷል፡፡

በአዲሱ 2016 ዓመት በመልካም ምኞት መልዕክታቸው የአገሪቱ ሁኔታ ያሳሰባቸው የሚመስሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፣ ‹‹ፈጣሪያችን በቸርነቱ ያቀዳጀንን አዲስ ዓመት ተቀብለናል፡፡ እኔም ዛሬ ለአምስተኛ ጊዜ ከፊታችሁ ቀርቤያለሁ፤›› ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

በዚህ የመገናኛ ብዙኃን ያን ያህል ሽፋን ባልተሰጠው የፕሬዚዳንቷ ጠንካራ መልዕክት፣ ‹‹ሕዝባችን ካለፈው ሳያገግም አሁንም ከሰላም ዕጦት አላመለጠም፡፡ ዛሬም በርካታ ዜጎቻችን በእርስ በርስ ውጊያ ውድ ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ እያጡም ነው፡፡ ቆስለዋል፣ ተፈናቅለውም በመጠለያ ጣቢያ ይገኛሉ፤›› የሚል መልዕክት ተላልፎ ነበር፡፡ ‹‹መናገርን፣ ማሳመንን፣ መወያየትንና መደራደርን ማስቀደም ለሰላም ዋስትና ሊታሰብበት የሚገባ በመሆኑ አደራ፤›› በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ፕሬዚዳንቷ አክለውም፣ ‹‹ብዙ ጊዜ እንደምለው የእርስ በርስ ግጭትም ሆነ ውጊያ ወገንን እየገደሉ ስለሆነ አሸናፊ የለም፡፡ ችግሩን ከሥር መሠረቱ ዓይቶ ዘላቂ መፍትሔ ከማስገኘት ሌላ የተለየ መንገድ የለንም፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

በመልዕክታቸው  ማሳረጊያ በሰላም ግንባታ፣ በውይይትና በምክክር፣ በጋራ ጉዳይ አገራዊ መግባባት ላይ በመድረስ፣ ጥላቻ፣ መናናቅ፣ መገፋትና ጥቃትን በፅኑ በመታገል መብቶችን በማክበርና በማስከበር፣ ‹‹ሁላችንም ድርሻ አለን፣ ይህ የዓመቱ ዋና ትኩረታችን ይሁን፡፡ ከመፈክር ባሻገር የሐሳብ ልዕልናን፣ አካታችነትን፣ አሳታፊነትን በተግባር ማሳየት ይጠበቃል፤›› የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በዚህ የአዲስ ዓመት መልዕክታቸው ማግሥት የሌላኛውን ዓመት የመንግሥት ዕቅድ ነገ ያቀርባሉ ተብሎ በሚጠበቀው የፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ አዲሱ መልዕክታቸው፣ ምን ሊሆን እንደሚችል በምክር ቤቶቹ የጋራ መክፈቻ ላይ ይጠበቃል፡፡

በዚህ በሚጠበቀው የሁለቱ ምክር ቤቶች ስብሰባ በፕሬዚዳንቷ መነሻ ንግግርና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጣይ መልስ ምን ይጠበቃል ሲል ሪፖርተር ያነጋገራቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የፓርላማ አባል፣ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተካሂዶ ፓርላማ ከገቡ ጀምሮ በሕዝቡ ዘንድ በተደጋጋሚ ሲጠየቁ የነበሩና ሲንከባለሉ እዚህ የደረሱ የመልካም አስተዳደርና የሰላም ጥያቄዎች በእጅጉ ቁርጠኛ መልስ ይሻሉ ብለዋል፡፡   

የምክር ቤት አባሉ አንደሚሉት በምርጫ አሸንፎ መንግሥት የመሠረተው ገዥ ፓርቲ አባል ከሆኑበት ቀን ጀምሮ በተመረጡበት አካባቢ ተንቀሳቅሰው መራጩን ሕዝብ ለማወያየት ቢያንስ ለሦስት ተከታታይ ጊዜ ሄደዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ሁሉ ግን የሚነሱት ጥያቄዎች ተመሳሳይ መሆንና የሚሰጡት መልሶች አጥጋቢ አለመሆን፣ ከምክር ቤት አባልነት አልፎ በተመረጡበት አካባቢ የሚያውቋቸው ሰዎች ‹‹ዋሾ›› የሚል ተቀጥላ ስም እንደሰጧቸው ይናገራሉ፡፡

ባለፉት ዓመታት ከሕዝብ የተነሱ ጥያቄዎችን ወደ ምክር ቤት በማምጣት ከአስፈጻሚ ተቋማት ጋር በሚደረግ የፊት ለፊት ውይይቶችና ማብራሪያዎች የሚሰጡ መልሶች መሬት ላይ ካለው ጋር እውነታ የማይገናኙ ስለመሆኑ የሚናገሩት የፓርላማ አባሉ፣ ለሕዝብ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ የማይሰጡ አመራሮች ተጠያቂ መሆን አለባቸው ይላሉ፡፡

ፕሬዚዳንቷ የሚያደርጉትን ንግግር አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች በሌላ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ እንደሚሰጡ የሚጠበቅ ሲሆን፣ አዳዲስ ሹመቶች ይኖራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የምክር ቤት አባሉ አክለው ገልጸዋል፡፡ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በየዓመቱ አዳዲስ ሚኒስትሮችን በመሾም የሚመጣ ለውጥ የለም የሚሉት የፓርላማ አባሉ፣ አዳዲስ ሹመት መሰጠቱን አይስማሙበትም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 74 በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረት የመንግሥታቸውን ፖሊሲ ያስፈጽሙልኛል የሚሉዋቸውን ሚኒስትሮች ከሁለቱም ምክር ቤቶች፣ ወይም ለሥራው ብቃት ካላቸው ግለሰቦች መካከል መርጠው ለፓርላማው ዕጩ በማቅረብ እንደሚያሾሙ ተደንግጓል፡፡

አሁን በሥራ ላይ ያለው ካቢኔ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ጨምሮ ከገዥው ፓርቲ የተውጣጡ 21 ሚኒስትሮች ስብስብን የያዘ ነው፡፡ በ2016 ዓ.ም. ይኖራል ተብሎ በሚጠበቀው ሹመት በፌዴራል መንግሥቱ ሥራ አስፈጻሚ ውስጥ ከጦርነት ከወጣው የትግራይ ክልልና በደቡብ እንደ አዲስ ከተመሠረቱ ክልሎች የሚካተቱ ይኖራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጭምጭምታዎች አሉ ሲሉ የፓርላማ አባሉ ተናግረዋል፡፡

በትግራይ ክልል ያለው አሁናዊ እንቅስቃሴ ግልጽ ባይሆንም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር በሚያደርገው ድርድርና ምክክር፣ ክልሉን የሚወክል የካቢኔ አባል ሊካተት እንደሚችል የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ባለሙያ አቶ አሮን ደጎል ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ጊዜያዊ አስተዳድሩ ሕወሓትን ጨምሮ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካተታቸው ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላትን ዕጩ ሲመለምሉ በሕገ መንግሥቱ በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረት ከሁለቱም ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በብቃት፣ በብሔር፣ በሃይማኖት ወይም በፓርቲያቸው አሠራር መሠረት እንዲያቀርቡ እንጂ፣ የክልል ወይም የብሔር ውክልናን ብቻ መሠረት እንዲያደርጉ የሚያስገድዳቸው ሕግ እንደሌለ አቶ አሮን አስረድተዋል፡፡

የመንግሥት አስተዳደርና የፌዴራሊዝም  ጉዳዮች ባለሙያው ዘሪሁን መሐመድ (ዶ/ር)፣ ብዙውን ጊዜ የሚዋቀረው ካቢኔ የብሔር አስተዋጽኦን ግምት ውስጥ ያስገባ ይመስላል ይላሉ፡፡ ምንም እንኳ የብሔር ወይስ የክልል ውክልና? የሚለው ጉዳይ አከራካሪ ቢሆንም፣ ውክልና ፍትሐዊነትን እንደሚያመጣ ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ብቃትንና የአመራር ልምድን ግምት ውስጥ ሳያስገባ በብሔር ወይም በክልል ውክልና የሚሰጥ ሹመት ድምር ውጤቱ የታሰበለትን ግብ አይመታም ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ዘሪሁን (ዶ/ር) በሕገ መንግሥቱ መሠረት አሸናፊ ፓርቲ መንግሥት ሲመሠርትና የአስፈጻሚውን አካል ሲያዋቅር፣ ተሿሚዎቹ በብሔራቸው ብቻ እንዲመረጡ የሚያስገድድ ሕግ የለም የሚለውን የአቶ አሮንን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አባልና የፓርላማ ተመራጩ አብርሃም በርታ (ዶ/ር)፣ ‹‹የካቢኔ አወቃቀር ላይ ካድሬ ሲቀያየርና ከተፎካካሪ ፓርቲ ሚኒስትር ሲሾም ወይም በየዓመቱ ተቋማት ሲቀያየሩ ዕድገትና ሰላም ይመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ በዚህ ዓመትም እንደዚህ ዓይነት መቀያየር ካለ እኔ አልቀበለውም፤›› ይላሉ፡፡ ዕውቀትና ጠንካራ ብቃት ባለው አመራር በተገቢው ቦታና ጊዜ ካቢኔን አዋቅሮ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ሲሉ ይሞግታሉ፡፡

ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ካላጋጠመ በቀር አንድን ተቋም ይመራል ተብሎ የተሾመ ግለሰብ፣ ተቋሙን እንደሚመራ ታምኖበት ለተወሰነ ጊዜ ተቋማዊ የአመራር ጥበብና ልምድ አካብቶ እንዲቆይ መደረግ አለበት የሚሉት አብርሃም (ዶ/ር)፣ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ባልሠራው ሥራ መጠየቅ ካለበት ተጠያቂ እንዲሆን ሊደረግ ይገባል እንጂ በየጊዜው መለዋወጡ ትርጉም የለሽ ነው ብለዋል፡፡ አክለውም  በየጊዜው ሪፎረም እየተባለ በሰበብ በአስባቡ ተፎካካሪን አስገባሁ፣ የሆነ ሰው ወከልኩ ለማለት ብቻ በየዓመቱ ተሿሚ መቀያየር ምንም ዓይነት ለውጥ ሊያመጣ እንደማይችል ተናግረዋል፡፡

ምክር ቤት ሥራውን ሲጀምር መንግሥት አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ ዕቅድ ይዞ ይቀርባል ብለው የሚጠብቁት አብርሃም (ዶ/ር)፣ ፓርላማው በሕገ መንግሥቱ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት መንግሥት በሚያቀርበው ዕቅድ  ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ መሥራት አለበት ብለዋል፡፡

ምክር ቤቱም አስፈጻሚውን አካል የሚቆጣጠርበት ጠንካራ አሠራር መዘርጋትና መንቀሳቀስ አለበት ያሉት አብርሃም (ዶ/ር)፣ እንደ ኢዜማ ምናልባት በትይዩ ካቢኔ አማካይነት ውይይት ተደርጎበት አገሪቱ ካለችበት ችግር አኳያ ለፓርላማ የሚቀርብ ጉዳይ ይኖራል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አባልና የፓርላማ ተመራጭ አቶ አበባው ደሳለው ሹም ሹር ሊያመጣው የሚችለው መፍትሔ የለም ይላሉ፡፡ ‹‹ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም ነው ነገሩ›› ሲሉም ያስረዳሉ፡፡ አንድ ተቋምን እንዲመራ የተቀመጠ ወይም ሥራውን የለመደ ሰው ባለበት ቢቆይ ይሻላል እንጂ መቀያየሩ የሕዝቡን ጥያቄ አይመልስም በማለት ስለጉዳዩ ያላቸውን ምልከታ ያጋራሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ ምናልባት አዳዲስ አመራሮችን ማምጣት የሚያስቡ ከሆነ ሹመቱ በክልል ውክልና ዕሳቤ ሳይሆን፣ የሕዝብን አንገብጋቢ ጥያቄዎች የሚመልስ አቅምና ብቃት ያለው ግለሰብ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

ብልፅግና ከብሔር ዕሳቤ ወጥቻለሁ ቢልም አሁንም እዚያው አስተሳሰብ ውስጥ ነው የሚሉት አቶ አበባው፣ ምንም እንኳ አንድ ሹመት ለአንድ ብሔር መሰጠቱ በራሱ እንኳን ችግር ባይሆንም ይህ ግለሰብ ከላይ የወረደለትን ብቻ ተቀብሎ ለማስፈጸም፣ አለቃውን ለማስደሰትና እሰይ እሰይ የሚል መሆኑ ነው ይላሉ፡፡ በመሆኑም ብቃትን መሠረት አድርጎ ፖሊሲን ለሕዝብ በሚጠቅም መንገድ መፈጸም የሚችል ሰው ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

አቶ አበባው በተያዘው ዓመት ከዚህ በፊት ይጠየቁ የነበሩ በተለይም ባለፉት ሁለት የፓርላማ ዓመታት ከመራጮቻቸው ጋር በነበራቸው ውይይት፣ በመሠረታዊነት ሲጠየቁና ሲንከባለሉ የነበሩ የሰላምና ፀጥታ፣ የኑሮ ውድነት አንገብጋቢ ጉዳዮች መልስ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

አገራዊ ሁኔታው እየተባባሰ ነው የሚሉት የፓርላማ አባሉ፣ ለዚህ ጉዳይ ከመንግሥት ቁርጠኛ መፍትሔ ሊያመጣ የሚችል ንግግርና ድርድርን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ ለአገር ያስፈልጋታል ብለዋል፡፡

ሰኞ ከቀትር በኋላ የሚጀምረው የምክር ቤት መክፈቻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ዲፕሎማቶች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡