የ20 ዓመቷ ዘፋኝ ኤደን ጎላን
የምስሉ መግለጫ,እስራኤልን ወክላ በውድድሩ ሥራዋን የምታቀርበው የ20 ዓመቷ ዘፋኝ ኤደን ጎላን ናት

ከ 3 ሰአት በፊት

እስራኤል ዩሮቪዥን ለተሰኘው የአውሮፓ አገራት የሙዚቃ ውድድር ያስገባችውን የሙዚቃ ግጥም ለመቀየር ተስማምታለች።

ይህን ያሳወቀው የእስራኤል መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ነው።

የውድድሩ አዘጋጆች ሙዚቃው “ከፖለለቲካ ይዘት የፀዳ” የሚለውን መርኅ ያልተከለ ነው ሲሉ ሙዚቃውን ከልክለ ነበር።

የእስራኤል መንግሥት ሚድያ የሆነው ‘ካን’ ኦክቶበር ሬይን የተሰኘውን የሙዚቃ ግጥም አልቀይርም ሲል አሻፈረኝ ብሎ ነበር።

ኦክቶበር ሬይን በግርድፍ ትርጉሙ የጥቅምት ዝናብ የተባለው ዘፈን በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7 ሐማስ እስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት የሚዳስስ ነው።

ነገር ግን የእስራኤል ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ አገራችው በውድድሩ እንድትሳተፍ በሚል “አስፈላጊ ማሻሻያ” ይደረጋል ብለዋል።

እስራኤል ከዚህ ቀደም አራት ጊዜ የዩሮቪዥን ውድድርን አሸንፋለች።

የዘንድሮው ውድድር በአምናው የውድድሩ አሸናፊ አገር ስዊድን በሚመጣው ግንቦት ይካሄዳል።

ካን፤ ለውድድሩ የሚያስገባውን ሙዚቃ እየመረጠ ሲሆን፣ ኦክቶበር ሬይን አንደኛ፤ ዳንስ ፎሬቨር ደግሞ ሁለተኛ ምርጫ ሆነው ተቀምጠዋል።

እሑድ ዕለት መግለጫ ያወጣው ካን የሁለቱንም ሙዚቃዎች ገጣሚዎች “ጥበባዊ ነፃነታችን ሳይገፉ ግጥሙን እንዲያሻሽሉት” መጠየቁን ገልጧል።

መግለጫው አክሎ ፕሬዝዳንት ሄርዞግ፤ “በለተይ ጠላቶቻችን እስራኤል ላይ አድማ ለመምታት ባቀዱበት በዚህ ወቅት በዓለም አቀፍ መድረክ ድምፃችን ሊሰማ ይገባል” ማለታችን አስነብቧል።

ባለፈው ወር የአውሮፓ ብሮድካስቲንግ ማኅበር የእስራኤልን ሙዚቃ ግጥም እያጤንኩ ነው ማለቱን ተከትሎ ካን “ሙዚቃውን አልቀይርም” ብሎ ነበር።

እስራኤልን ወክላ በውድድሩ ሥራዋን የምታቀርበው የ20 ዓመቷ ዘፋኝ ኤደን ጎላን ናት።

ከዚህ ቀደም የዩሮቪዥን አዘጋጅ አገራት ለውድድሩ ያስገቡትን ሙዚቃ እንዲቀይሩ አስገድዶ ያውቃል።

በአውሮፓውያኑ 2009 ጆርጂያ ለውድድሩ ያስገባችው “ዊ ዶንት ዋና ፑት ኢን” የተባለው ሙዚቃ የታገደው የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ስለሚነካ ነበር።

በሌላ በኩል እስራኤል በጋዛ በምታካሂደው እርምጃ ምክንያት በውድድሩ መሳተፍ የለባትም ሲሉ አንዳንድ አገራት ጥያቄ አቅርበዋል።

ይህን ያሉት አይስላንድ፣ ፊንላንድ፣ ኖርዌይ፣ ዴንማርክ እና ስዊድን ናቸው።

እኒህ አገራት ሩሲያ ዩክሬን ላይ በፈፀመችው ወረራ ምክንያት ከሁለት ዓመታት በፊት ከውድድሩ መታገዷን ዋቢ አድርገው እስራኤልም ልትታገድ ይገባል ይላሉ።

ነገር ግን የዩሮቪዥን አዘጋጆች በዩክሬን እና በጋዛ ያለው ሁኔታ የተለያየ ነው ሲሉ ጥያቄውን ውድቅ አድርገውታል።