የአሜሪካ ባንዲራ እና ካፒቶል ሕንፃ ያለበት ፎቶ

ከ 5 ሰአት በፊት

አሜሪካውያን በቀጣይ ወር ጥምት መጨረሻ ላይ ቀጣይ ፕሬዝደንታቸውን ለመምረጥ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ያቀናሉ። ይህ ምርጫ የአሜሪካ ብቻ ሳይሆን የተቀረውን ዓለም ቀልብ የሚስብ ነው።

በዘንድሮው ምርጫ ፕሬዝደንት ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ ምክር ቤት (ሕግ መወሰኛው ምክር ቤት) አባላትም ይመረጣሉ። የምክር ቤቱ አባላት ሕግ አውጪዎች በመሆናቸው በአሜሪካውያን ሕይወት ላይ ተፅዕኖ አላቸው።

የአሜሪካ ባንዲራ

ምርጫው መቼ ይካሄዳል?

የ2024 የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም. ዕለተ ማክሰኞ ይካሄዳል። ተመራጩ አሊያም ተመራጯ ፕሬዝዳንት ከጥር ወር ጀምሮ ለአራት ዓመታት አሜሪካን ይመራሉ።

የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው የሚመረጡ ግለሰቦች በራሳቸው አንዳንድ ሕግጋትን የማውጣት ሥልጣን አላቸው። ከዚያ ውጪ ግን ከምክር ቤቱ አባላት ጋር በመተባበር ነው ሕግ የሚያወጡት።

በዓለም አቀፍ መድረክ ደግሞ የአሜሪካ ፕሬዝደንት አገሪቱን ወክለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውን ያስፈፅማሉ።

የአሜሪካ ባንዲራ

ዕጩዎች እነማን ናቸው? እንዴትስ ተመረጡ?

በአሜሪካ ሁለቱ ንዑስ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዲሞክራቲክ እና ሪፐብሊካን ይባላሉ። እነዚህ ፓርቲዎች ከዋናው ምርጫ በፊት በሚያካዷቸው ቅድመ ምርጫዎች ተወካዮቻቸውን ያስመርጣሉ።

የሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለው የሚወዳደሩት የቀድሞው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ናቸው። ትራምፕ ተቀናቃኞቻቸውን በሰፊ ድምፅ በማሸነፍ ነው ፓርቲውን ወክለው በዕጩነት ለመወዳደር የተመረጡት።

የቀድሞው ፕሬዝደንት በዊስኮንሲን ግዛት በሚልዋውኪ በተካሄደ የፓርቲው ስብሰባ ላይ ተገኝተው በይፋ የዕጩነት ማዕረጋቸውን ተቀብለዋል።

ወደ ዲሞክራቶች ስንመጣ ምክትል ፕሬዝደንቷ ካማላ ሃሪስ በቺካጎዋ ኦገስት ከተማ በተካሄደ የፓርቲው ስብሰባ ላይ ተገኝተው በይፋ የፓርቲው ዕጩ እንዲሆኑ ተሰይመዋል።

ካማላ ሃሪስ የፕሬዝደንታዊውን ምርጫ የተቀላቀሉት ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ራሳቸውን ከውድድሩ ካገለሉ በኋላ ነው።

ከሁለቱ ንዕስ ፓርቲዎች በተጨማሪ በግላቸው የሚወዳደሩ ዕጩዎችም አሉ። የቀድሞው ፕሬዝደንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ወንድም ልጅ የሆኑት ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ጁኒየር በግላቸው የሚያደርጉትን ጉዞ ትተው ዶናልድ ትራምፕን እንደሚደግፉ ይፋ አድርገዋል።

የአሜሪካ ባንዲራ

ዲሞክራቶች እና ሪፐብሊካኖች ምን ይለያያቸዋል?

ዲሞክራቶች ‘ሊበራል’ (ለዘብተኛ) ፖለቲካዊ ፓርቲ ናቸው። ለሲቪል መብቶች፣ ሰፋ ላለ ማኅበረሰባዊ ደኅንነት የሚታገሉ እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመመከት የሚታገሉ ናቸው።

ዘ ግራንድ ኦልድ ፓርቲ አሊያም ጂኦፒ በመባል የሚታወቁት ሪፐብሊካኖች ደግሞ ወግ አጥባቂ ናቸው። የግብር ክፍያ እንዲቀንስ፤ የመንግሥት አቅም ዝቅ እንዲል፤ የጦር መሣሪያ የመያዝ መብት እንዲጠበቅ እንዲሁም ስደት እና ጽንስ ማቋረጥ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ የሚታገሉ ናቸው።

የአሜሪካ ባንዲራ

ፕሬዝደንታዊ ምርጫው እንዴት ይወሰናል?

የአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ዕጩዎች በርካታ ድምፅ ስላገኙ መንበረ-ሥልጣኑን ማግኘት ይችላሉ ማለት አይደለም።

ሁለቱ ዕጩዎች የሚፎካከሩት በ50ዎቹ ግዛቶች የሚደረጉትን ምርጫዎች ለማሸነፍ ነው።

እያንዳንዱ ግዛት የተለያየ መጠን ያለው ኢሌክቶራል ኮሌጅ የሚባል ቁጥር አለው። ይህም በሕዝብ ቁጥር ብዛት ላይ የተመሰረተ ነው። በአጠቃላይ 538 ኢሌክቶራል ኮሌጆች አሉ። አንድ ዕጩ ከእነዚህ መካከል 270 እና ከዚያ በላይ ማግኘት አለበት/አለባት።

ከሁለት ግዛቶች በቀር ሁሉንም ግዛቶች ያሸነፈ ሁሉን ይወስዳል የሚል ሕግ አላቸው። ይህ ማለት ከፍተኛ ውጤት ያመጣ/ች ዕጩ የግዛቲቱን ኢሌክቶራል ኮሌጅ ሙሉ በሙሉ ይወስዳል አሊያም ትወስዳለች ማለት ነው።

አብዛኞቹ ግዛቶች ከሁለቱ ለአንዱ ፓርቲ ያደላሉ። ለዚህ ነው ብዙ ጊዜ ‘ስዊንግ ስቴት’ ወይም ደግሞ ቁርጥ ባለ ሁኔታ የየትኛው ፓርቲ መራጮች መሆናቸው ያልተለዩ ግዛቶች ላይ ትኩረት የሚደረገው።

በአገር ደረጃ አንድ ዕጩ ብዙ የሕዝብ ድምፅ ሊያመጣ/ልታመጣ ትችላለች። ለምሳሌ በ2016 (እአአ) ምርጫ ሂላሪ ክሊንተን በርካታ ድምፅ ቢያገኙም በኢሌክቶራል ኮሌጅ ተበልጠው ነበር የተሸነፉት።

የአሜሪካ ባንዲራ

ከፕሬዝደንታዊ ዕጩዎች በተጨማሪ

እርግጥ ነው ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ለፕሬዝደንታዊ ምርጫ አሸናፊው ነው። ነገር ግን ከዚህ በተጨማሪ የኮንግረስ አባላት ይመረጣሉ። የኮንግረሱ አባላት ሕግ አውጭዎች ናቸው።

ኮንግረስ ማለት 435 የተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና 34 የሴኔት አባላት ያሉት ሲሆን፣ አሜሪካውያንን እነዚህን ፖለቲከኞች ለመምረጥ ድምፅ ይሰጣሉ።

በአሁኑ ወቅት ሪፐብሊካኖች የገንዘብ ፍጆታን የሚቆጣጠረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን አብላጫ ድምፅ የያዙ ሲሆን፣ ዲሞክራቶች ደግሞ ቁልፍ የመንግሥት ሹመቶች የሚወሰኑበትን ሴኔት በአብላጫ ይዘውታል።

እነዚህ ሁለት ምክር ቤቶች ሕግ ከማወጣት ባለፈ ዋይት ሐውስን በመቆጣጠር አንድ ፕሬዝደንት ከሕግ ውጪ እንዳይንቀሳቀስ ይቆጣጠራሉ።

የአሜሪካ ባንዲራ

አሸናፊው መቼ ይለያል?

ለወትሮው የምርጫው አሸናፊ የሚለየው በድምፅ መስጫው ቀን አመሻሹ ላይ ሲሆን፣ ባለፈው የ2020 ምርጫ ግን አሸናፊውን ለመለየት 5 ቀናት ፈጅቷል።

ከምርጫው በኋላ ያለው ጊዜ የሽግግር ወቅት የሚባል ሲሆን፣ በተለይ አዲስ ፕሬዝደንት ከተመረጠ ሥራዎችን ለመረካከብ የሚሆን ጊዜ ነው።

አልፎም አዲስ መንግሥት እስኪመሠረት ያሉት ጥቂት ወራት የካቢኔ ሚኒስቴሮችን ለመምረጥ እና ዕቅድ ለማውጣት የሚሆኑ ናቸው።

አዲስ ፕሬዝደንት በይፋ መንበሩን የሚረከቡት ጥር ላይ በሚካሄድ በዓለ ሲመት ነው። ይህ ሥነ ሥርዓት ዋሺንግተን ዲሲ ውስጥ ከካፒቶል ሕንፃ ፊት ያካሄዳል።