የሄዝቦላህ ምክትል መሪ የሆኑት ናይም ቃሲም
የምስሉ መግለጫ,የሄዝቦላህ ምክትል መሪ ናይም ቃሲም በኢብራሒም አቂል ቀብር ላይ ተገኝተዋል

ከ 4 ሰአት በፊት

እስራኤል እና ሄዝቦላህ ድንበር አካባቢ የሚያደርጉትን የተኩስ ልውውጥ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ደግሞ ሁለቱ ወገኖች ከለየለት ጦርነት እንዲቆጠቡ እያሳሰበ ይገኛል።

የእስራኤል ጦር ኃይል እንዳለው ቅዳሜ ምሽት እና እሑድ ንጋት 150 ሮኬቶች፣ ሚሳዔሎች እና ሌሎች የጦር መሣሪያዎች ወደ እስራኤል ተተኩሰዋል።

አንዳንድ ጥቃቶች ከዚህ ቀደም ከሚመቱት ዒላማ ዘልቀው በመውደቃቸው በሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላዊያን ከቦምብ አደጋ ለመከላከል በተሠሩ መጠለያዎች ውስጥ ተሸሽገው እንደነበር ተሰምቷል። አብዛኛዎቹ ጥቃቶች የደረሱት ሀይፋ ከተማ አቅራቢያ ነው።

እስራኤል በአፀፋው በደቡባዊ ሊባኖስ በወሰደችው እርምጃ በሺዎች የሚቆጠሩ የሄዝቦላህ ሮኬት ማስወንጨፊያዎችን አውድሚያለሁ ብላለች።

እሑድ ንግግር ያሰሙት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ሀገራቸው “ፀጥታዋን ለማስከበር የትኛውንም ዓይነት እርምጃ ትወስዳለች” ብለዋል።

“ሄዝቦላህ ላይ ሊታሰብ የማይችል ኪሳራ አድርሰናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስራኤል-ሊባኖስ ድንበር ያሉ እስራኤላዊያንን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ቃል ገብተዋል።

የሄዝቦላህ ምክትል መሪ የሆኑት ናይም ቃሲም በበኩላቸው “ማስፈራራቶችን አያግዱንም። የትኛውንም ወታደራዊ እርምጃ ለመመከት ዝግጁ ነን” ሲሉ ተደምጠዋል።

እስራኤል ባለፈው አርብ በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት በፈፀመችው ጥቃት ምክንያት የተገደሉት የሄዝቦላህ ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑት ኢብራሒም አቂል ቀብራቸው ተካሂዷል። በቀብር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ቃሲም “አሁን አዲስ ምዕራፍ ላይ ነን። በግልፅ [ከእስራኤል ጋር] ተፋጠናል” የሚል ንግግር አሰምተዋል።

ሼኽ ናይም ቃሲም ለቡድኑ አባላት ባስተላለፉት መልዕክት እስራኤል ዒላማዎቿን እየሳተች ነው ብለው ነገር ግን ሄዝቦላህ ባለፉት ሶስት ቀናት ጥቃት ማድረስ መቀጠሉን ገልፀዋል።

የሀይፋ ሆስፒታል ታካሚዎችን ወደ ተሸሸገ ሥፍራ መውሰድ ጀምሯል
የምስሉ መግለጫ,የሀይፋ ሆስፒታል ታካሚዎችን ወደ ተሸሸገ ሥፍራ መውሰድ ጀምሯል

አክለው በሚቀጥሉት ቀናት በሰሜናዊ ሊባኖስ የሚኖሩ በርካታ የእስራኤል ነዋሪዎች ከመኖሪያቸው እንደሚፈናቀሉ እና እስራኤል የቡድኑን ጥንካሬ መቋቋም እንዳቃትት ተናግረዋል።

ሄዝቦላህ የሐማስ አጋር ሲሆን ሐማስ ደግሞ ኢራን “አክሲስ ኦፍ ሬዚዝስታንስ” እያለች የምትጠራው ጥምር ቡድን አባል ነው።

የኢብራሒም አቂልን ቀብር ለመታደም በርካታ ቁጥር ያለው ሰው አደባባይ የወጣ ሲሆን የሄዝቦላህ አባላት የሆኑ ሰዎች “ሞት ለአሜሪካ” የሚሉ እና ሌሎች የተቃውሞ ድምፆቻን ሲያሰሙ ነበር።

የሊባኖስ ባለሥልጣናት በተደረገ ጥቃት ኢብራሒም አቂልን እና 15 አብረዋቸው የነበሩ የሄዝቦላህ አባላትን ጨምሮ 45 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቀዋል።

በርካታ ጠላቶች እንዳሏቸው ይነገራል። ሰውየውን ለያዘ አሊያም ያሉበትን ለጠቆመ 7 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ቃል ተገብቶ ነበር። በ1980ዎቹ ቤይሩት ውስጥ ለተገደሉት በመቶዎች በሚቆጠሩ አሜሪካዊያን ሳቢያ ነው ዩናይትድ ስቴትስ ግለሰቡን ትፈልገው የነበረው።

እስራኤል አርብ ዕለት ባደረሰችው ጥቃት አንድ ሙሉ ቤተሰብን ጨምሮ 30 ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸው ተዘግቧል። የሟች ዘመዶች በጥቃቱ ከፈራረሱ ሕንፃዎች መካከል በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎችን የተበታተነ አስከሬን ሲፈልጉ ታይተዋል።

የሊባኖስ የሕዝብ ሥራ ሚኒስትር የሆኑት እና ከሄዝቦላህ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የሚጠረጠሩት አሊ ሀይሜ እስራኤል ቀጣናውን ወደ ጦርነት እየጎተተችው ነው ሲሉ ወቅሰዋል።

“በስተመጨረሻ ማወቅ የሚገባን ሊባኖስ አይደለችም ጦርነት ማድረግ የፈለገችው የሚለውን ነው። ሕዝቡም ጦርነት አይፈልግም። እስራኤል ግን ወደ ጦርነት ግቡ እያለችን ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሄዝቦላህ ሊባኖስ ውስጥ በጣም ፈርጣም ጉልበት ያለው ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ድርጅት ነው። የሺያ ሙስሊም ድርጅት የሆነው ሄዝቦላህ ከበርካታ ሀገራት የተሻለ የጦር መሣሪያ አለው። ዩናይት ስቴትስ እና ዩናይትድ ኪንግደም ቡድኑ ሽብርተኛ ነው ሲሉ ፈርጀዋል።

በእስራኤል እና ሄዝቦላህ መካከል ያለው ግጭት እየተባባሰ የመጣው ሐማስ በእስራኤል ላይ ካደረሰው ጥቃት በኋላ እስራኤል ወደ ጋዛ መዘለቋን ተከትሎ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ “ሊባኖስ ሌላኛዋ ጋዛ እንዳትሆን እሰጋለሁ” ብለዋል። የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በበኩላቸው ሀገራቸው ሰፊ ጦርነት እንዳይከፈት የበኩሏን እንደምታደርግ አስታውቀዋል።

የእስራኤል ጦር ኃይል እሑድ ዕለት የተተኮሱትን ሮኬቶችን አብዛኛዎቹን ማውደም ገልፆ ሁለት ሮኬቶች የተተኮሱት ከኢራቅ ነው ብሏል። ኢስላሚክ ሬዚዝታንስ ኢን ኢራቅ የሚባለው በኢራን የሚደገፍ ቡድን ለጥቃቱ ኃላፊነት ወስዷል።