ዶናልድ ትራምፕ
የምስሉ መግለጫ,ዶናልድ ትራምፕ

ከ 4 ሰአት በፊት

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንትና የአሁኑ የካማላ ሐሪስ ተፎካካሪ ዶናልድ ጄ ትራምፕ በመጪው ምርጫ ካላሸነፉ በፈረንጆቹ 2028 እንደማይወዳደሩ ጠቆሙ።

የ78 ዓመቱ የዕድሜ ባለጸጋ ትራምፕ ላለፉት ሦስት ተከታታይ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫዎች ሪፐብሊካንን ወክለዋል።

በቅርቡ ባደረጉት አንድ ቃለምልልስ በቀጣይ ምርጫ በካማላ ሐሪስ ከተሸነፉ ከ4 ዓመት በኋላ ዳግም ይወዳደራሉ ወይ ተብለው ሲጠየቁ፣ “አይመስለኝም። አላደርገውም” ብለዋል።

ይሁንና መጪውን ምርጫ እንደሚያሸንፉ በጽኑ ተስፋ አድርገዋል።

የአሜሪካ ሕግ አንድ ፕሬዝዳንት ከሁለት የሥልጣን ዘመን በላይ በዋይት ሐውስ መቆየትን ይከለክላል። ይህም ማለት ትራምፕ መጪውን ምርጫ ቢያሸንፉ እንኳ በ2028 በድጋሚ ለፕሬዝዳንትነት መወዳደር አይችሉም።

ባለፈው ሐሙስ በአይሁድ-እስራኤላዊያን ካውንስል ጉባኤ ላይ የተገኙት ትራምፕ “ከተሸነፍኩ አንዱ ምክንያት እናንተ ናችሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

“ለመሆኑ እኔ ከተሸነፍኩ ምን ዓይነት መአት ሊወርድ እንደሚችል ያውቃሉን?” ሲሉ ወደ ካማላ ሐሪስ ያዘነበሉ አይሁድ-አሜሪካዊያንን ወቅሰዋል።

ይህ አስተያየታቸው በካማላ ሐሪስ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን እና በገለልተኛ አይሁድ መራጮች ዘንድ ቅሬታን አሳድሯል።

ከዚህ ቀደም ትራምፕ የመሸነፍ እጣ ሊገጥማቸው እንደሚችል የሚጠቁም ንግግር ከአንደበታቸው ወጥቶ አያውቅም። ያለፈው ምርጫም ተጭበርብሮ ነው እንጂ አሸናፊው ጆ ባይደን ሳይሆኑ እኔ ነኝ ሲሉ ይከራከራሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ትራምፕ መሸነፍም እንዳለ የገባቸው ይመስላል።

የፖለቲካ ተንተኞች ይህ የትራምፕ አስተያየት ከጆ ባይደን ገለል ማለት ወዲህ የመጣ አዲስ አመል ነው ይላሉ። በተለይም ካመላ ሐሪስ ከፍተኛ ተቀናቃኛቸው እንደሆኑ በመረዳታቸው እንደሆነ ይገምታሉ።

ካማላ ሐሪስ ጆ ባይደንን ከተኩ ወዲህ በዲሞክራቶች ዘንድ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ መነቃቃት ተፈጥሯል።

በታኅሣሥ ወር ብቻ በምርጫ ቅስቀሳ ካማላ ሐሪስ 190 ሚሊዮን ዶላር መሰብሰብ የቻሉ ሲሆን ትራምፕ ግን 130 ሚሊየን ብቻ ነው ማሰባሰብ የቻሉት።

ትናንት እሑድ በተሰበሰበ የሕዝብ አስተያየት ሐሪስ ዶናልድ ትራምፕን 52% ለ48% እየመሩ እንደሆነ ተመላክቷል።

ወሳኝ በሚባሉት ግዛቶች ግን ዶናልድ ትራምፕ እየመሩ ነው።

ይሁንና ቀድሞ ይመሩበት ከነበረው ነጥብ ልዩነቱ እየጠበበ መጥቷል።

የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ በሠራው የሕዝብ አስተያየት ቀመር በወሳኝ ግዛቶች ትራምፕ 51% ለ49% እየመሩ ነው።

ኤንቢሲ ትናንት ይፋ ባደረገው ሌላ የሕዝብ አስተያየት ቀመር ደግሞ ሐሪስ ትራምፕን በ5 ነጥብ እየመሩ ነው።

48% የሚሆኑ ድምጽ ለመስጠት የተመዘገቡ መራጮች ካማላ ሐሪስን በበጎ ማየት እንደጀመሩ አንድ ጥናት አመላክቷል።

ይህ የሕዝብ አስተያየት መራጮች በስደተኞች ጉዳይ፣ በምጣኔ ሃብት ጉዳይ እና በኑሮ መወደድ ጉዳይ ልባቸው ወደ ትራምፕ ያጋደለ እንደሆነ አሳይቷል።