በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በኽር
የምስሉ መግለጫ,በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በኽርን ጨምሮ በዲፕሎማቶቹ ላይ ምንም ዓይነት አደጋ አልደረሰም

ከ 2 ሰአት በፊት

በሰሜን ምዕራብ ፓኪስታን በጉብኝት ላይ የነበሩ የኢትዮጵያ አምባሳደርን ጨምሮ ሌሎች ዲፕሎማቶች በነበሩበት በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት አንድ የፖሊስ መኮንን መሞቱን የአገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የስዋት ግዛት ፖሊስ ኃላፊን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው የውጭ አገር ዲፕሎማቶቹ በአካባቢው ያለን ቱሪስት ሥፍራ ለመጎብኘት ሲጓዙ ነው መንገድ ዳር በተጠመደ ቦምብ ጥቃቱ የደረሰው።

“ዲፕሎማቶቹን እየመራ ሲሄድ የነበረው የደኅንነት ቡድን ነው መንገድ ዳር በተቀበረ ቦምብ የተመታው” ሲሉ ኃላፊው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቹ ላይ ባወጣው መግለጫ በፓኪስታን ኺቤር ፓኽቱንኽዋ ክልል የደረሰውን “የሽብር ጥቃት” አውግዟል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደርን ጨምሮ ሌሎች የውጭ አገር ዲፕሎማቶች በሥፍራው እንደነበሩ አረጋግጧል።

አክሎም በቦምብ ጥቃት ምክንያት ለተገደለው የፖሊስ መኮንን ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝቷል።

ሮይተርስ እንደዘገበው በጥቃቱ አራት የፖሊስ መኮንኖች መቁሰላቸውን የግዛቲቱ የፖሊስ ኃላፊ አስታውቀዋል።

የፓኪስታን ፕሬዝደንት አሲፍ አሊ ዛርዳሪ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሼባዝ ሻሪፍ ጥቃቱን ያወገዙት ሲሆን፣ እስካሁን ለጥቃቱ ኃላፊነት የወሰደ የለም።

ዲፕሎማቶቹ ስዋት ቫሊ ወደተባለው አካባቢ ለጉብኝት ሲያቀኑ የነበረው በአካባቢው የንግድ ምክር ቤት ግብዣ በስፍራው ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅ መሆኑ ተገልጿል።

ጥቃቱ ዒላማ ያደረገው የኢትዮጵያን ጨምሮ ኢንዶኔዢያ፣ ፖርቱጋል፣ ካዛክስታን፣ ቦሲኒያ ሄርዜጎቪና፣ ዚምባብዌ፣ ርዋንዳ፣ ቱርክሜንስታን፣ ቬትናም፣ ኢራን፣ ሩሲያ እና ታኪጅስታን ዲፕሎማቶች ያሉበት የተሽከርካሪዎች አጀብን ነው።

የፖሊስ እና የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት ዲፕሎማቶቹ በቀረበላቸው ጥሪ መሠረት እሑድ ጠዋት በአካካቢው ወደሚገኝ ማላም ጃባ ወደተሰኘ ሪዞርት እያቀኑ ነበር።

ፖሊስ አክሎ እንደገለፀው ከ10 በላይ የሚሆኑት ሁሉም ዲፕሎማቶች በጥቃቱ ምንም ዓይነት አደጋ አልደረሰባቸውም። ዲፕሎማቶቹ ወደ ዋና ከተማዋ ኢዝላማባድ በሰላም እንደተመለሱ ፖሊስ አክሏል።

“ሁሉም አምባሳደሮች ሰላም ናቸው። ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ ወዲያውኑ ደኅንነቱ ወደተረጋገጠ ቦታ ተወስደዋል። ቀጥሎ ደግሞ ወደ ኢዝላማባድ አቅንተዋል” ሲሉ የአገሪቱ ፖሊስ ምክትል ኃላፊ ሞሐመድ አሊ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

የፓኪስታን ፀረ-ሽብርተኛ ኃይል በስዋት ቫሊ አካባቢ በስፋት ይገኛል። ሥፍራው ለበርካታ ዓመታት የእስላማዊ ታጣቂዎች መናኸሪያ ነበር። ታጣቂዎቹ ከመንግሥት ጋር የገቡትን የተኩስ አቁም ስምምነት ካፈረሱ በኋላ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ጥቃቶች እየፈፀሙ ይገኛሉ።

የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊዋ ማላላ ዩሳፍዛይ እዚህ አካባቢ ነው በአውሮፓውያኑ 2012 በታጣቂዎች በደረሰባት ጥቃት የቆሰለችው።

እሑድ ዕለት ዲፕሎማቶቹ ላይ ከተቃጣው ጥቃት በኋላ ወታደሮች እና ፖሊስ ቦታውን የከበቡት ሲሆን በአካባቢው ሰዓት እላፊ ተጥሏል።

የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኢዝላማባድ በይፋ ተመርቆ የተከፈተው ግንቦት 2015 ዓ.ም. ነው። ዲፕሎማቱ ጀማል በኽር ነሐሴ 2014 ዓ.ም. ነው በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት።