የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር እና ሌሎች ባለሥልጣናት በሞቃዲሾ ወደብ
የምስሉ መግለጫ,የሶማሊያ የመከላከያ ሚኒስትር አብዱልካዲር ሞሐመድ ኑር በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ይህንን ምሥል አጋርተው ከግብፅ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት አድንቀዋል

23 መስከረም 2024, 15:16 EAT

ሶማሊያ የተለያዩ ከባድ የጦር መሳሪያዎች ከግብፅ እንደተሰጧት እና ተጨማሪ መሳሪያዎችን በቀጣይነት እንደምትጠብቅ አንድ የሶማሊያ ከፍተኛ ባለሥልጣን አረጋገጡ።

ስማቸው ሳይጠቀስ ለቢቢሲ ሶማሊኛ የተናገሩት ባለሥልጣን ባለፉት ቀናት በመርከብ ተጭነው ወደ ሞቃዲሾ ወደብ የደረሱት የጦር መሳሪያዎች የሶማሊያ መንግሥት ጦር የሚታጠቃቸው መሆኑን አመልክተዋል።

ወደ ሶማሊያ የገቡት የጦር መሳሪያዎች ፀረ አውሮፕላን ሚሳኤሎች፣ መድፎች እና ሌሎች አነስተኛ የጦር መሳሪያዎች መሆናቸውን ባለሥልጣኑ ጨምረው አረጋግጠዋል።

ሶማሊላንድ ለሶማሊያ መንግሥት ከግብፅ የተሰጡት ከባድ የጦር መሳሪያዎች በአካባቢው አሳሳቢ ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚችል በመግለጽ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቃለች።

ይህንን ከፍተኛ መጠን ያለውን የጦር መሳሪያ በሞቃዲሾ ወደብ በኩል ወደ ሶማሊያ መግባቱን በተመለከተም የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ሲሆን፣ በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይም ይህንን የሚያሳዩ ምሥሎች ተሰራጭተዋል።

በርካታ የሶማሊያ መገናኛ ብዙኃን የጦር ማሳሪያዎቹ ወደ ሞቃዲሾ ወደብ ደርሰው የተራገፉት በግብፅ መርከብ አማካኝነት መሆኑን ዘግበዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ከትናንት እሁድ ጀምሮ የተለያዩ ዓይነት ያላቸው ከባድ መሳሪያዎች እና በጭነት መኪና ተሸፍነው የሚጓዙ ወታደራዊ ቁሶች በሞቃዲሾ ጎዳናዎች ላይ ሲተላለፉ ታይተዋል።

ቢቢሲ ሶማሊኛ ያነጋገራቸው የሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣን አሁን ከገባው የጦር መሳሪያ ጭነት በተጨማሪ በቀጣይነት ታንኮችን እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

ከሶማሊያ ነጻ አገርነቷን ያወጀችው እና ከኢትዮጵያ ጋር የፈረመችው ስምምነትን ሶማሊያ የተቃወመችባት ሶማሊላንድ ከግብፅ የተሰጡት ከባድ የጦር መሳሪያዎች ውስብስብ የደኅንነት ፈተና ያለበትን ቀጣና ሰላም አደጋ ላይ ይጥላል በማለት ጥልቅ ስጋት እንደተፈጠረባት ገልጻለች።

የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ እንዳለው የሞቃዲሾ አስተዳደር እነዚህን ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ከባድ የጦር መሳሪያዎች በተገቢው ሁኔታ የመያዝ አቅም ስለሌለው አልሻባብን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ አንጃዎች እጅ በመግባት አሳሳቢ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ሲል ስጋቱን ገልጿል።

የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼህ መሀመድ እና የግብፅ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታ አልሲሲ ሲጨባበጡ
የምስሉ መግለጫ,ሶማሊያ እና ግብፅ ነሐሴ 2016 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርመዋል

ይህ የከባድ ጦር መሳሪያ አቅርቦት ዜና የተሰማው ግብፅ ከሶማሊያ ጋር ወታደራዊ ስምምነት ደርሳ ሠራዊቷን በአገሪቱ ውስጥ ለማሰማራት ፍላጎት እንዳላት መግለጿን ተከትሎ ኢትዮጵያ ተቃውሞዋን ካሰማች በኋላ ነው።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ሁለት የግብፅ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ሞቃዲሾ መግባታቸው ሲዘገብ ኢትዮጵያ ድርጊቱን የቀጣናውን ሰላም የሚያናጋ ነው በማለት፤ ሶማሊያ የውጪ ኃይል ወደግዛቷ እንዲገባ መፍቀድ የለባትም ስትል ቅሬታዋን አሰምታ ነበር።

ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ወር ላይ ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት ከሶማሊያ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር ከተፈራረመች በኋላ ከሶማሊያ ጋር ውዝግብ ውስጥ መግባታቸው ይታወሳል።

በሁለቱ አገራት መካከል ከተፈጠረው ቀውስ በኋላ ከኢትዮጵያ ጋር ከአስር ዓመታት በላይ በሕዳሴ ግድብ ምክንያት ስትወዛገብ የቆየችው ግብፅ፣ ሶማሊያን በመደገፍ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አሳውቃለች።

ይህ አሁን በሞቃዲሾ ወደብ በኩል ከግብፅ ገብቷል የተባለው የጦር መሳሪያ የመጀመሪያው አይደለም። ባለፈው ነሐሴ ወርም የጦር መሳሪያ እና ጥይቶችን የጫኑ ሁለት ወታደራዊ አውሮፕላኖች ሞቃዲሾ መግባታቸው ይታወሳል።

በሶማሊያ ላይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለረዥም ጊዜ ተጥሎ የቆየው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ባለፈው ዓመት ከተነሳ በኋላ ወደ አገሪቱ በይፋ የጦር መሳሪያዎች ሲገቡ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

በአካባቢው ያለውን ሁኔታ ወደ በለጠ መካረር ሊከተው ይችላል የተባለውን የግብፅ ተሳትፎ እና የአሁኑን የጦር መሳሪያ አቅርቦት በተመለከተ ኢትዮጵያ እስካሁን ያለችው ነገር የለም።

በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ውስጥ የግብፅ ተሳታፊ መሆን በአካባቢው ውጥረት የፈጠረ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ጋር የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረመችው ሶማሊላንድ በግዛቷ ያለውን የግብፅ የባሕል ማዕከል እና ቤተ መጽሐፍትን ዘግታለች።

ሶማሊያ የኢትዮጵያን አምባሳደር ከአገሯ ከወራት በፊት ያስወጣች ሲሆን፣ ሉዓላዊነቴን የሚጥስ ነው ያለችው ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችውን ስምምነት ውድቅ እንድታደርግ እየጠየቀች ነው።