የአየር ጥቃት

23 መስከረም 2024, 15:11 EAT

እስራኤል ዛሬ በሊባኖስ ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 100 ሰዎች መገደላቸውን የሊባኖስ የጤና ሚኒስትር አስታወቀ።

በጥቃቱ ከ400 በላይ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸውም ተገልጿል።

የሊባኖስ የሕብረተሰብ ጤና ሚኒስትር ባወጣው መግለጫ በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል ያሉ ሆስፒታሎች ከአጣዳፊ ቀዶ ሕክምና ውጪ ያሉ አገልግሎቶችን እንዲሰርዙ አሳስቧል።

የሕክምና ባለሙያዎች ወደ ድንገተኛ ክፍል የሚወሰዱ ተጎጂዎችን ለማከም እንዲጠባበቁ ማሳሰቢያም ተሰጥቷል።

በሊባኖስ ደቡባዊ ክፍል እና በመዲናዋ ቤይሩት ደቡባዊ ክፍል ትምህር ቤቶች መዘጋታቸውን የአገሪቱ የትምህርት ሚኒስቴር ገልጿል።

በሊባኖስ መንገዶች ተጨናንቀው ይታያሉ። ሰዎች ወዴት እንደሚሄዱ ቢጨንቃቸውም ጉዞ ላይ መሆናቸው ተስተውሏል።

የእስራኤል የአየር ጥቃትም እንደቀጠለ ነው።

ሀማራ የተባለውን አካባቢ ጨምሮ በቤሩት የተለያዩ አካባቢዎችና ደቡባዊ ሊባኖስ የሚኖሩ ሰዎች ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።

አካባቢው የመረጃ ሚኒስትር፣ ባንኮች እና ዩኒቨርስቲዎች የሚገኙበት ሲሆን፣ የሄዝቦላህ ጠንካራ ይዞታ ከሚባሉ አካባቢዎች መካከል አይደለም።

ሄዝቦላህ በርካታ ሮኬቶችን ወደ ሰሜናዊ እስራኤል መተኮሱን አስታውቋል።

የእስራኤል ወታደራዊ መቀመጫን ጨምሮ ሌሎችም መሰል ወታደራዊ ስፍራዎች የሚሳዔል ዒላማ መሆናቸውን ሄዝቦላህ ገልጿል።

ይህም እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ ለከፈተችው ጥቃት ምላሽ ነው።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቢያንስ 35 ሮኬቶችን ወደ እስራኤል መተኮሳቸውን ገልጿል።

በአየር መቃወሚያ አማካይነት በርካታ ሮኬቶች መመታታቸውንም አክሏል። የተቀሩት ሮኬቶች አሚአድ የተባለ አካባቢ ጉዳት ማድረሳቸውን አስታውቋል።

በደቡባዊ ሊባኖስ ሄዝቦላህ ከሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች እንዲወጡ ለነዋሪዎችና ለመንግሥት ሠራተኞች ሳይቀር የድምጽና የጽሑፍ መልዕክት መተላለፉ ተገልጿል።

ሄዝቦላህ ዒላማ የሚሆንባቸውን አካባቢዎች ለቀው እንዲወጡ እስራኤል ማስጠንቀቋ ተነግሯል።

እስራኤል በመቶዎች የሚቆጠሩ የአየር ጥቃቶች ማድረሷ የተገለጸ ሲሆን፣ ከ300 በላይ የሄዝቦላህ ይዞታ የሆኑ ዒላማዎች መምታቷን አስታውቃለች።

የሊባኖስ የመረጃ ሚኒስትር ዛይድ ማካሪ በቤሩት “ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ለቀው እንዲወጡ የሚያሳስቡ የጽሑፍ መልዕክቶች” መላካቸውን ገልጸዋል።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት የአየር ጥቃቱ “እስራኤል ግቧን እስከምትመታ ድረስ እየተባባሰ ይሄዳል” ብለዋል።