September 23, 2024 – Konjit Sitotaw 

በአዲስ አበባ ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት ተከስቷል።

የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን፣ በከተማዋ የነዳጅ እጥረት የተፈጠረበትን ምክንያት በማጣራት ላይ እንደኾነ መናገሩን የመንግሥት ዜና ምንጮች ዘግበዋል።

በርካታ ማደያዎች በረጃጅም ሰልፎች ተጨናንቀው ውለዋል።

ባለሥልጣኑ፣ ለአዲስ አበባ በቀን እስከ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሊትር የሚደርስ ነዳጅ እንደሚያሠራጭና ከጅቡቲ የሚገባው ነዳጅም ከአገሪቱ ፍላጎት ጋር ተቀራራቢ መኾኑን ገልጦ፣ የእጥረቱን ምክንያት እያጣራ ነው ተብሏል።

በከተማዋ የተፈጠረውን የነዳጅ እጥረት ለመቀነስ፣ ባለሥልጣኑ ለጊዜው ከሱሉልታ መጠባበቂያ ዲፖው 20 ቦቲ ቤንዚን እንዳከፋፈለ ተገልጧል።

ከመሃል አገር የሚጓጓዝ ነዳጅ፣ በኮንትሮባንድ ወደ ጎረቤት አገራት እንደሚወጣ ሲነገር ቆይቷል።