September 23, 2024 – Konjit Sitotaw 

ኬንያ፣ ባለፈው ዓመት ከጥር እስከ ሰኔ በስድስት ወራት ውስጥ ከኢትዮጵያ የገዛችው ኤሌክትሪክ ኃይል ካለፈው የፈረንጆች ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ88 በመቶ ብልጫ እንዳለው የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል።

ኬንያ፣ በስድስቱ ወራት ውስጥ ከኢትዮጵያ የገዛችው ኃይል፣ 672 ነጥብ 26 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት እንደኾነ ዘገባዎቹ አመልክተዋል። ኬንያ ባሁኑ ወቅት በወር በአማካይ 122 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት ኃይል ከኢትዮጵያ እየገዛች እንደኾነ ተገልጧል።

ኢትዮጵያ ለሽያጭ በምታቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል ዋጋ ርካሽነት የተነሳ፣ የኬንያ ቀዳሚዋ የኃይል አቅራቢ ኾናለች።

ኬንያ አንድ ኪሎ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ የምትገዛው፣ በ8 ነጥብ 6 የአሜሪካ ሳንቲም ነው።

ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ ፍጆታ ላይ ከዚህ ዓመት ጀምሮ በየሦስት ወሩ 10 በመቶ ታሪፍ ለመጨመር የወሰነች ሲኾን፣ ለኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል የምትሸጥበትን ዋጋ እንደገና ለመከለስ ግን እስከ ከሦስት ዓመት በላይ መጠበቅ ይጠበቅባታል።

ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት ለአምስት ዓመታት የሚቆይ የኃይል ሽያጭ ስምምነት ከኬንያ ጋር መፈራረሟ ይታወሳል።