የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)

ዜና ለአማራ ተወላጅ እስረኞችና ቤተሰቦቻቸው ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ ቀረበ

ዮናስ አማረ

ቀን: September 25, 2024

ያለ ፍርድ በማረሚያ ቤት ተይዘው የሚገኙ ታዋቂ የአማራ ተወላጅ እስረኞችን ለመደገፍና ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት፣ ታዋቂው ፖለቲከኛ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ጥሪውን ያቀረቡት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲን በመወከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ ‹‹የህሊና እስረኞች›› ያሏቸው የአማራ ተወላጅ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና ምሁራን ቤተሰቦች፣ ችግር ላይ መውደቃቸውን በግል ባደረጉት ክትትል መታዘባቸውን ገልጸዋል፡፡

አቅም አላቸው ብለው ለተማመኑባቸው ለአንዳንድ ሰዎች ይህንኑ የታሳሪ ቤተሰቦችን ሁኔታ በማስረዳት ድጋፍ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት አጥጋቢ ውጤት ባለማግኘቱ፣ ከባድ የሐዘን ስሜት እንደተሰማቸውም ደሳለኝ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ከታሳሪዎቹ ቤተሰቦች መካከል አራት አምስት ልጆች ያላቸው፣ ከፍተኛ የትምህርት ቤት ወጪ የተደራረበባቸው፣ እንዲሁም በቤት ኪራይ የሚኖሩና ብዙ የኑሮ ሸክም የተጫናቸው መኖራቸውን በመጠቆም፣ ቀና ልብ ያላቸው ሁሉ ዕገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ አክለውም የአማራ ተወላጅ የሆኑ ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችንና ምሁራንን ጨምሮ ለሁለት ዓመት ያህል ያለ ፍርድ በእስር ላይ የቆዩ ሰዎች ችግራቸውን ዓለም ሰምቶ መፍትሔ እንዲያገኝ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በእነ ወንድወሰን (ዶ/ር) መዝገብ የተከሰሱ በርካታ ሰዎች ወደ ሁለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በእስር ላይ እንደሚገኙ በይፋዊ የዩቲዩብ ገጻቸው ያስረዱት ደሳለኝ (ዶ/ር)፣ በአማራ ክልል ውስጥ ከሐምሌ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ከተፈጠረው ችግር ጋር በተያያዘ፣ በእነ አቶ ዮሐንስ ቧያለው መዝገብ ሥር የተከሰሱ ሰዎችና ሌሎች ጋዜጠኞችም በእስር መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡ ከእነዚህ የአማራ ተወላጅ እስረኞች መካከል ለከፍተኛ የጤና ዕጦት የተዳረጉ፣ ሌላም እንግልትና ሥቃይ የደረሰባቸው መኖራቸውን እንደሚያውቁ ጠቁመዋል፡፡

የእነዚህን ታሳሪዎች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የቤተሰቦቻቸውን ሁኔታ በቅርበት ሲከታተሉ መቆየታቸውን የገለጹት ፖለቲከኛው፣ ‹‹በርካቶች ለቤተሰቦቻቸው ዋና የገቢ ምንጭ በመሆናቸው እነሱ ከታሰሩ ጀምሮ የቤተሰቦቻቸው ገቢ ተቋርጧል፡፡  የእነሱን ቤተሰቦች ካልረዳናቸው ማንም ሊረዳቸው የሚችል የለም፡፡ የታሰሩ ወንድሞቻችን ወንጀል ሠርተዋል ብዬ አላምንም፡፡ በሚያራምዱት የፖለቲካ አመለካከት ነው የታሰሩት ብዬ አምናለሁ፡፡ ለአማራ ሕዝብ መብት መከበር ባደረጉት የትግል ተሳትፎ ነው የታሰሩት፡፡ ወንጀል ቢኖርባቸው ኖሮ ለአንድ ዓመትና ለስድስት ወራት ጊዜ ክስ መሥርቶ ለማስፈረድ ከበቂ በላይ ነበር፡፡ ነገር ግን እየተደረገ ያለው እነሱን ለረዥም ጊዜ በማሰር ማሰቃየትና ቤተሰቦቻቸውን ለችግር መዳረግ ነው፤›› በማለት በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አቋም አንፀባርቀዋል፡፡

ሁሉንም ማግኘት ባይችሉም የተወሰኑትን ታሳሪ ቤተሰቦች ያሉበትን ሁኔታ መመልከት መቻላቸውንና ሄደው መጠየቃቸውን የጠቀሱት ደሳለኝ (ዶ/ር)፣ በግላቸው ካላቸው ነገር በጥቂቱ ለማገዝ መሞከራቸውን አስረድተዋል፡፡

ኅብረተሰቡ ካለበት የኑሮ ውድነትና የኢኮኖሚ መጎሳቆል አንፃር ብዙ እንደማይጠብቁ ጠቅሰው፣ ነገር ግን እነዚህን የህሊና እስረኞች ቤተሰቦች መደገፍና ማገዝ ከሁሉም ቀና ወገን የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እያንዳንዱ የአማራ ተወላጅ ሰዎቹ የታሰሩለትን ዓላማ በማሰብ ቤተሰቦቻቸውን እንዲደግፍ ጥሪ ያቀረቡት ደሳለኝ፣ የቤተሰቦቻቸውን አድራሻና መገኛ በመስጠት እንደሚተባበሩም ገልጸዋል፡፡

በእነ ወንድወሰን አሰፋ (ዶ/ር) መዝገብ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ፣ ጋዜጠኛ ገነት አስማማው፣ ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው፣ መምህርት መስከረም አበራ፣  ሲሳይ አውግቸው (ዶ/ር) ጨምሮ ወደ 11 እስረኞች ጉዳይ በፍርድ ቤት እየታየ ነው፡፡ በእነ አቶ ዮሐንስ ቧያለው የክስ መዝገብ ሥር ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩትና የአብን ተወካዩ አቶ ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ ካሳ ተሻገር (ዶ/ር) እና ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) ክስም በፍርድ ቤት እየታየ ነው፡፡ በእነ መላክ ምሳሌ መዝገብ ደግሞ ኤርሚያስ መኩሪያ፣ ኮማንደር ጌታዋይ ታደሰና ሌሎች ታሳሪዎች ጉዳይም በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑ ይታወቃል፡፡