የአውሮፓ ኅብረት ልዑካን ቡድን መሪ ዣቪየር ኒኖ ፔሬዝ (አምባሳደር)

ዜናፖለቲካ

ናርዶስ ዮሴፍ

September 25, 2024

በአውሮፓ ኅብረት ሥር የሚገኘው የአውሮፓውያን የሰላም ፋሲሊቲ ለአጋር የአፍሪካ አገሮች፣ በሁለት መስኮች ከ600 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ድጋፍ ማፅደቁ ተገለጸ። 

ይህ የተነገረው ትናንት ማክሰኞ መስከረም 14 ቀን 2016 ዓ.ም. በአፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረት ልዑካን ቡድን መሪ ዣቪየር ኒኖ ፔሬዝ (አምባሳደር) በሁለቱ ኅብረቶች መካከል ስላሉ የጥምረት ሥራዎችና የጋራ እ.ኤ.አ. በ2030 ድረስ ለማሳካት ዕቅድ ስለተያዘላቸው ራዕይ ውስጥ በዝርዝር የተቀመጡ ጉዳዮችን አስመልክቶ፣ በራዲሰን ብሉ ሆቴል ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሲሰጡ ነው። 

ከማብራሪያው ጋር በቀረቡ ሰነዶች መሠረት በሁለቱ አኅጉሮች ኅብረቶች መካከል የሚገኙ ለትምህርት፣ ለስደተኞች ጉዳዮች፣ ለጤና፣ እንዲሁም ለመከላከያ ሠራዊቶች ድጋፍን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮች ተዘርዝረዋል፡፡  

ከእነዚህ ሰነዶች አንዱ የሆነው የአውሮፓ ኅብረት የዜጎቹንና አብረውት የሚሠሩ የአጋር አፍሪካ አገሮችን በሁለትዮሽ ስምምነት፣ እንዲሁም በአፍሪካ ኅብረት ደረጃ በጋራ የሚሠራባቸውን የውትድርና ተልዕኮ ድጋፍ የሚያቀርበው፣ የአውሮፓ ኅብረት አገሮች በሚሰጡት ድጋፍ የሚንቀሳቀሰው የአውሮፓውያን ሰላም ፋሲሊቲ ድጋፎች ዝርዝር ይገኝበታል። 

ይህንን ጉዳይ የሚመለከተው ሰነድ እንደሚያስረዳው፣ የሰላም ፋሲሊቲው በአፍሪካውያን ለሚመሩ የሰላም ማስከበር ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በአጠቃላይ በአፍሪካ ኅብረት አስፈጻሚነት ለሚከናወኑት የሰላም ማስከበር ሥራዎች እ.ኤ.አ. በ2021፣ 130 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም ከ2022 እስከ 2024 ላለው ጊዜ ደግሞ 600 ሚሊዮን ዩሮ፣ መድቦ እየተሠራ መሆኑን ያስረዳል። 

የእነዚህ ለአፍሪካ ኅብረት የሰላም ማስከበር ወታደራዊ ተልዕኮ የሚደረጉ ድጋፎች ዝርዝር እንደሚገልጸው፣ በአፍሪካ ኅብረት ለሚመራው የሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) የሰላም ማስከበር ሥራዎችን ለማገዝ 340 ሚሊዮን ዩሮ ተመድቧል። 

በተናጠል የሶማሊያ መንግሥትን የፀጥታ ኃይሎች ለማጠናከር፣ የአገሪቱን የውትድርና ሥልጠና ማዕከላትን ለማሻሻል፣ የትዕዛዝ ማስተላለፊያ፣ ቁጥጥርና ግንኙነት መስመሮችም ለማዘመን የመሳሰሉ የመከላከያ መሠረተ ልማቶችን ማሻሻያ ለመደገፍ፣ የሶማሊያ ሠራዊትን መሬት ላይ ያለ እንቅስቃሴ ለማገዝና የመንግሥትን መከላከያ ሠራዊት የሽግግር ዕቅዶችን ማሳካት የሚችልበት አቅም ላይ ለማድረስ ለሚከናወኑ ሥራዎች የሚውል 89 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ከሰላም ፋሲሊቲው እንደሚያገኝ ተገልጿል። 

ሌላው ወታደራዊ ጉዳዮች ነክ የሆነ ድጋፍ ደግሞ ቦኮ ሃራምን ለመዋጋት ለተቋቋመው በአፍሪካ ኅብረት ሥር የሚገኝ የአገሮች የጋራ ግብረ ኃይል የሚውል 100 ሚሊዮን ዩሮ ነው። 

ለጂኤስ ሳህል የጋራ ግብረ ኃይል 35 ሚሊዩን ዩሮ እንደሚውል ሲገለጽ፣ ለዚህ ግብረ ኃይል የሚሰጠው ድጋፍ ቡርኪናፋሶ፣ ማሊንና ኒጀርን እንደማያካትት ተጠቁሟል፡፡  

በአፍሪካ ደቡብ በኩል ባሉ አገሮች ለሚከናወነው የደቡብ አፍሪካ አገሮች የልማት ማኅበረሰብ የሞዛምቢክ ልዑክ፣ ከሰላም ማስከበር ጋር ለተያያዙ ሥራዎቹ 15 ሚሊዮን ዩሮ መመደቡም ታውቋል። 

የአውሮፓውያን የሰላም ተቋም የ17 ቢሊዮን ዩሮ ፈንድ ያለው ለሰባት ዓመታት (እ.ኤ.አ. ከ2021 እስከ 2027) ድረስ የሚቆይና ከኅብረቱ አጋር አካላት ጋር ያለ የሰላም ማስከበር ሒደቶችን ወጥነት ባለው አንድ ሜካኒዝም በኩል የአውሮፓ ኅብረትን የጋራ የውጭና የፀጥታ ፖሊሲዎች ውስጥ ውትድርናና መከላከያን በተመለከቱ ዘርፎች ላይ ፋይናንስ የሚያቀርብ ነው።

የሰላም ፋሲሊቲው ካለው 17 ቢሊዩን ዩሮ ፈንድ ውስጥ አምስት ቢሊዩን ዩሮው ለዩክሬን ድጋፍ ፈንድ የተመደበ ነው።