የቻይና ኤምባሲ የአፍሪካ አገሮች ዲፕሎማቶች በተገኙበት ውይይት ሲደረግ

ዜና ኢትዮጵያ አባል የሆነችበት ዓለም አቀፍ አሸማጋይ ድርጅት በቅርቡ በቻይና ይፋ እንደሚደረግ ተገለጸ

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: September 25, 2024

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካና ከእስያ 19 አባል አገሮችን በመሥራችነት የያዘው ዓለም አቀፍ አሸማጋይ ድርጅት፣ በመጪው የአውሮፓውያን አዲስ ዓመት በቻይና ሆንግ ኮንግ ይፋ እንደሚደረግ ተገለጸ፡፡

በዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ወይም በአገሮች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት በቻይና መንግሥት አነሳሽነት እ.ኤ.አ. በ2022 ለጉዳዩ የጋራ ስምምነት የፈጠሩ አገሮች የፈጠሩት መሆኑን፣ በአዲስ አበባ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ አስታውቋል፡፡

ኤምባሲው ትናንት ማክሰኞ መስከረም 14 ቀን 2017 ዓ.ም. በድርጅቱ አመሠራረትና ቁመና ላይ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካዮችና የአፍሪካ አገሮች ዲፕሎማቶች በተገኙበት ውይይት አካሂዷል፡፡

ኢትዮጵያ መሥራች አባል እንደሆነች የተገለጸው ይህ የአገሮች ስብስብ፣ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ አለመግባባቶችን ለመፍታት ያለመ አሸማጋይ ተቋም መሆኑን የድርጅቱ ዝግጅት ቢሮ ኃላፊ ሰን ጂን (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ከመሥራች አገሮች መካካል አሥሩ ከአፍሪካ ሲሆኑ፣ ቻይናን ጨምሮ ሁለት ቢሊዮን ሕዝቦች የሚገኙበትን የአፍሪካ እስያ በዋነኝነት የሚያካትት ስብስብ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

በዓለም ላይ እየተተገበረ ያለው የአሸማጋይነት ሚናና አሠራር በአደጉት አገሮች የበላይነት የተያዘ በመሆኑ፣ አፍሪካውያንና ሌሎች አዳጊ አገሮች አለመግባባትና ግጭትን በራሳቸው አቅም እንዲፈቱ የሚያስችላቸውን ዕድል የሚፈጥር ዓለም አቀፍ ተቋም እንደሆነ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

ለምሥረታው የተስማሙ አባል አገሮች በጋራ ለሚመሠርቱት የአሸማጋይ ተቋም የራሳቸውን ተወካይ ለመላክ የሚያስችላቸው የኮታ ሥርዓት እንዲሚኖር የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህ ተቋም ውስጥ አገሮች መወከላቸው አዳጊ አገሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሰላም የሚኖራቸው ሚናና ተሳትፎን ያሳድጋል ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምሥራቅ፣ እስያና ፓስፊክ አገሮች ጉዳዮች ዳይሬክተር ንጉሥ ከበደ (አምባሳደር) በበኩላቸው፣ ይህ ስብስብ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ አዲስ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከቻይና ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ለመሥራት የተመሠረተ ትልም ነው ብለዋል፡፡ ስብሰቡ ከትንንሽ እስከ ትልልቅ ሉዓላዊ አገሮች የጋራ ተቋም እንዲያደራጁ የሚያስችልና አቅም የሚፈጥር እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ሕግ ጉዳዮች ዳይሬክተር ረታ ዓለሙ (አምባሳደር)፣ ይህ ከተለመደው የአሸማጋይነት ሚና ለየት ብሎ ዲፕሎማሲያዊና የሕግ ጉዳዮችን በአንድ አድርጎ ለመሥራት የተነሳ የአገሮች ስብስብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሐሳቡ ጥንስስ ጀምሮ ተሳታፊ እንደነበረች የጠቀሱት ረታ (አምባሳደር) በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊደመጥ የሚችል፣ በአባል አገሮች ብዛትም ሆነ በመሥራች አባላቱ ሲታይ አሁን በዚህ ደረጃ የተቋቋመ ዓለም አቀፍ አሸማጋይ ተቋም ባለመኖሩ ስብስቡ ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን ለመፍታት የራሱ የሆነ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአሸማጋይነት ሥራ በተሰማሩ አካላት ላይ የሚሰጡ አስተያየቶችን በማረም፣ አፍሪካውያን የመሪነትና ለዓለም ሰላም ከፍተኛ የአሸማጋይነት ሚና እንዲኖራቸው ያደርጋል ብለዋል፡፡

አገሮች ስምምነት በፍላጎት የሚገቡበት የጋራ ተቋም መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ ዓመታዊ የአባልነት ክፍያ መፈጸም አንዱ የአባልነት መለኪያ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ድርጅቱ ወደ ሥራ ሲገባ ለሕግ ባለሙያዎችና በአባል አገሮቹ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ለሚያስፈልጋቸው የመንግሥት አካላት ሥልጠና መስጠትና ማመቻቸትን ጨምሮ፣ በርካታ ተግባራት እንደሚኖሩት በመድረኩ በነበረ ገለጻ ተብራርቷል፡፡

በቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስምምነቶችና የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክተር ማ ሽንሚን (አምባሳደር) በሰጡት አስተያየት፣ ሰላማዊ የአሸማጋይነት ሚና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሠረታዊ መርሆች ውስጥ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የአሸማጋይነትን ሚና የሚፈልጉ አካላት መበራከትና ፍላጎቱም እያደገ መምጣቱን በማየት፣ ቻይና ይህን የአነሳሽነት ሚና በመውሰድ ለድርጅቱ መመሥረት ግፊት ስታደርግ መቆየቷን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት በአመሠራረቱ ላይ በርካታ ውይይቶች ሲደረጉ መየቆታቸውን አስታውሰው፣ ከጅምሩ 11 የነበሩ መሥራች አገሮች ወደ 19 አድገው ዋና መሥሪያ ቤቱን በሆንግ ሆንግ ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡

ኃያላኑ አገሮች የከበዱ አጀንዳዎችን በደካማ አገሮች ላይ በማራመድና እነሱን ያላማከሉ የዜሮ ድምር ውጤት ብቻ በያዙ ውሳኔዎች እየጎዷቸው ነው ብለዋል፡፡

ዳይሬክተሩ በሆንግ ኮንግ ይፋ ይደረጋል የተባለው ዓለም አቀፍ አሸማጋይ ድርጅቱ ዓለም አቀፍ ሕጎች እንዲከበሩ፣ ፍትሐዊነት እንዲሰፍንና የአንድ ወገን የበላይነትን በመቃወም የጋራ ውሳኔዎች እንዲተላለፉ የራሱ የሆነ ትርጉም ያለው ሚና ይጫወታል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ያላደጉ አገሮች በዓለም አቀፍ ተቋማት የዕለት ተዕለት ሥራዎች  ውክልና የሌላቸው ስለሆነ፣ የሚኖራቸው ተፅዕኖ ዝቅተኛ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ይህ ስብስብ አገሮቹ የሚገባቸውን ድምፅና ውክልና እንዲያገኙ ይሠራል ብለዋል፡፡