ተመስገን ተጋፋው

September 25, 2024

የአውሮፓ ኅብረት ቡናን ጨምሮ ወደ አባል አገሮቹ የሚላኩ ሰባት የምርት ዓይነቶች ከደን ጭፍጨፋና መመናመን ነፃ መሆናቸው ሳይረጋገጥ፣ ለግብይት እንዳይቀርቡ የሚከለክል ሕግ በማውጣቱ ምክንያት፣ በርካታ ቡና ላኪዎች ወደ አውሮፓ ኤክስፖርት ለማድረግ መቸገራቸውን ተናገሩ፡፡

የአርፋሳ ጄኔራል ትሬዲንግ ኤክስፖርት ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ንጉሤ ለገሠ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የአውሮፓ ኅብረት ቡናን ከደን ጭፍጨፋና መመናመን ነፃ መሆኑ ሳይረጋገጥ ለግብይት እንዳይቀርብ የሚከለክል ሕግ ካወጣ ጊዜ ጀምሮ፣ ኤክስፖርተሮች ወደ አውሮፓ ቡናቸውን እየሸጡ አይደለም፡፡

የኢትዮጵያን ቡና ገዥዎች አውሮፓ እስኪደርስ ድረስ የአውሮፓውያን አዲሱ ዓመት እየተቃረበ ነው ብለው በመፍራታቸው፣ ኮንትራት መፈራረም እንዳቆሙ አክለው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ኤክስፖርተሮች ከአቅራቢዎች በዚህን ያህል ዋጋ የኤክስፖርት ቡናን ይቀበሉ ብሎ ያስቀምጥ እንጂ፣ አቅራቢዎች ባለሥልጣኑ ካስቀመጠው ዋጋ እጥፍ ለኤክስፖርተሮች እየሸጡ እንደሆነ አቶ ንጉሤ አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሠረት ኩባንያቸው ኤክስፖርት ማድረግም ሆነ ከአቅራቢዎች ግዥ መፈጸም ማቆሙን የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፣ በአሁኑ ወቅት ኩባንያው ከሁለት ወራት በፊት በተፈራረመው ኮንትራት መሠረት ቡና በመሸጥ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በተለይ የፋይናንስ አቅርቦትና ሌሎች ችግሮች በቡና ላኪዎች ላይ የፈጠሩት ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደሆነና መንግሥትም ጉዳዩን ችላ ማለቱን ተናግረዋል፡፡

ወደ ተለያዩ አገሮች የሚላከው የቡና ዓይነት ዋጋ የተለያየ እንደሆነና ለአብነት  ግሬድ አምስት የተበጠረ የነቀምት ቡና በኪሎ 3.72 ዶላር እየተሸጠ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ዓምና ከተሸጠበት ዋጋ ጋር ሲነፃፀር ተቀራራቢ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ዘንድሮ ከጥር ወር ጀምሮ ወደ አውሮፓ የሚገባ ቡና ከደን ጭፍጨፋና መመናመን ነፃ መሆን እንዳለበት የአውሮፓ ኅብረት ያወጣው ሕግ እንደሚያስገድድ፣ የቡና ላኪዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛት ወርቁ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት ያወጣውን ሕግ በተመለከተ የኢትዮጵያ ሁኔታ ምን ይመስላል የሚለውን ለመፈተሽ በሳተላይት ምሥል ሲታይ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የደን ጭፍጨፋና መመናመን የሚመለከተው የቡና መሬት ሁለት ሔክታር ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት ያወጣው ሕግ እንደማይነካት፣ ይሁን እንጂ ኤክስፖርተሮች ከተለያዩ ቡና አቅራቢዎች የሰበሰበቡትን ቡና ምን ያህል ከደን ጭፍጨፋና መመናመን የፀዳ ነው የሚለውን ማረጋገጫ ለማግኘት እንደሚቸገሩ አስታውቀዋል፡፡

ማረጋገጫ ካላገኙ ደግሞ የአውሮፓ ኅብረት ያወጣውን ሕግ ተፈጻሚ ለማድረግ ኤክስፖርተሮች ችግር ውስጥ እንደሚገቡ፣ ብዙዎቹ ኤክስፖርተሮች ከገበያ ሊወጡ እንደሚችሉ አክለው ገልጸዋል፡፡

አንድ ኤክስፖርተር ለአውሮፓ ገበያ የሚቀርብ ቡና ለመግዛት ከ30 አርሶ አደሮች ሊሰበስብ እንደሚችል፣ ለዚህም የአርሶ አደሮችን ስምና የመገናኛቸውን ጂኦ ሎኬሽን መመዝገብ እንደሚያስፈልገው ጠቁመዋል፡፡

ይህንን ለማድረግ ደግሞ ኤክስፖርተሮች ከባድ ችግር ውስጥ እንደሚወድቁና ወደ አውሮፓም ቡና ለመላክ እንደሚቸገሩ አክለዋል፡፡

በሌላ በኩል በብራዚልና በቬትናም በተፈጠረው የአየር ፀባይ ችግር ምክንያት የዓለም ቡና ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተናግረዋል፡፡

በተለይ የዓረቢካም ሆነ የሮቡስታ የዓለም የቡና ዋጋ በየጊዜው እየጨመረ መሆኑን፣ ዘንድሮ የሮቡስታ ቡና ዋጋ ለ47 ዓመታት ታይቶ ማይታወቅ ሁኔታ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡