የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት ዝላታን ሚሊስክ

ማኅበራዊ በሰብዓዊ ዕርዳታ ዘረፋ ምክንያት ድጋፋቸውን ያቆሙ አካላትን እያግባባ መሆኑን የዓለም የምግብ ፕሮግራም…

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: September 25, 2024

ከአንድ ዓመት በፊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) እና የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ለተቸገሩ ወገኖች የሚያቀርቡት የምግብ ዕርዳታ በመዘረፉ ሳቢያ ድጋፋቸውን ያቋረጡ ለጋስ አካላት፣ ሲያደርጉት የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ እንደገና እንዲጀምሩ የማግባባት ሥራ እያከናወነ መሆኑን የዓለም የምግብ ፕሮግራም አስታወቅ፡፡

በቅርቡ የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት ዝላታን ሚሊስክ፣ ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፣ በሰብዓዊ ዕርዳታ ዘረፋ ሳቢያ የተጀመረው ምርመራ መቀጠሉን ቢገልጹም፣ አሁን ላይ የደረሰበትን ደረጃ በተመለከተ ያሉት ነገር የለም፡፡

ይሁን እንጂ በተፈጸመው ዘረፋ ምክንያት ቀድሞ ድጋፍ ሲያደርጉ ከነበሩ አካላት የተወሰኑት ድጋፋቸውን ባለመጀመራቸው የበጀት እጥረት ማጋጠሙን ተናግረዋል፡፡ ስለዚህም ለለጋሽ አካላቱ ቆሞ የነበረው ዕርዳታ እንደገና ሲጀምር የተወሰዱትን ዕርምጃዎች በማስረዳት፣ ሲያደርጉት የነበረውን ድጋፉ እንዲቀጥሉ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

 በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የፍላጎቱ መጠንና የሚገኘው ፋይናንስ ልዩነቱ ከፍተኛ በመሆኑ ምክንያት፣ ድርጅቱ ሥርጭቱን ቅድሚያ ለሚያስፈጋቸው ሰዎች ብቻ እያቀርበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹የፋይናስ እጥረት በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦቱ ላይ ተፅዕኖ በመፍጠሩ፣ በከፍተኛ ሁኔታ አፋጣኝ የፋይናንስ ድጋፍ ያስፈልገናል፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የነበረው የዕርዳታ ፍላጎት በተፈጥሮ አደጋ በተለይም በጎርፍና በድርቅ ክስተቶች ምክንያት ለሚመጣ አደጋ የሚቀርብ የነበረ ቢሆንም፣ ከሦስት ዓመታት ወዲህ ግን በሰው ሠራሽ አደጋዎች በተለይም በጦርነት ሰላም አጥተው ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ አራት ሚሊዮን ዜጎቸና አንድ ሚሊዮን ስደተኞችን ማስተናገድ የግድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ እያደገ የመጣ ነው ባሉት አስቸኳይ የዕርዳታ ፍላጎት ምክንያቱ ድርጅታቸው እ.ኤ.አ. የካቲት 2025 ድረስ 341 ሚሊዮን ዶላር ካላገኘ፣ ስደተኞችን ጨምሮ በርካታ ሚሊዮን ዜጎች የምግብ አቅርቦት ችግር ይገጥማቸዋል ብለዋል፡፡ ዳይሬክተሩ በአሁኑ ወቅት ከአሥር ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ለከፋ የምግብ እጥረት የተጋለጠ መሆኑን፣ ከዚህ ጋር ተዳምሮ እያንዣበበ ነው ያሉት ድርቅ ቀውሱን እንደሚያባብሰው ገልጸዋል፡፡

በአማራ ክልልና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ለዕርዳታ ፈላጊዎች የሚያስፈልገው በጀት አነስተኛ መሆንና ለሥርጭት አስቻይ የፀጥታ ሁኔታ አለመኖሩ የገዘፈ ችግር እንደሆነባቸው ገልጸው፣ በመጪው መኸር ጥሩ ምርት ሊገኝ እንደሚችል ቢገመትም፣ 4.6 ሚሊዮን ዜጎች እስከ እ.ኤ.አ. 2024 መገባደጃ ድረስ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል። የዓለም የምግብ ድርጅት ባለው የበጀት ውሰንነት ምክንያት ማቅረብ የሚችለው ለ1.3 ሚሊዮን የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ለሚጠብቁ ዜጎች እንደሆን አስረድተዋል።

የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦቱ በተለይም እየተባባሰ ነው ባሉት የፀጥታና የደኅንነት ችግር በተለይ በአማራ ክልል ያለው ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ጠቅሰው፣ እ.ኤ.አ. በ2024 ብቻ ስምንት የዕርዳታ ሠራተኞች መገደላቸውንና 20 ሠራተኞች መታገታቸውን ገልጸዋል፡፡ ሁሉም አካላት የዕርዳታ ሠራተኞችን ደኅንነት መጠበቅ አለባቸው ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለይ በብር የመግዛት አቅም መዳከምና በዋጋ ንረት ለችግር የተጋለጡ ቤተሰቦች የበለጠ የዕለት ምግብ ማግኘት እንደከበዳቸው፣ የፀጥታ ችግሩ ዜጎች ያመረቱትን ወደ ገበያ ይዞ ለመውጣት ፈተና እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡

ከመጪው እ.ኤ.አ. 2025 አጋማሽ ጀምሮ ለመጪዎቹ አምስት ዓመታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም አዲስ አገራዊ ስትራቴጂ ይፋ እንደሚደርግ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ሰብዓዊ ዕርዳታ በከፍተኛ መጠን የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድርቅን መቋቋም እንዲችሉ የሚያደርጉ ሥራዎችን ለማከናወንና የአገሪቱን የምግብ ሥርዓት ማጠናከር ላይ ስትራቴጂው እንደሚያተኩርና በመጪው የአውሮፓውያን አዲስ ዓመት ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል የፀጥታ ችግሩ አሳሳቢ በመሆኑ ዕርዳታ ይዞ ማለፍ የማይቻልበት አጋጣሚ ሲኖር የአቅርቦት መዘግየት ሊኖር እንደሚችል ጠቅሰው፣ በፀጥታ ችግሩ ምክንያት በክልሉ የሚደረገውን የዕርዳታ ሥርጭት የማቆም ዕቅድ እንደሌለ አስረድተዋል፡፡