September 25, 2024 – EthiopianReporter.com 

ሰሞነኛው የዓለም መገናኛ ብዙኃን ትኩረት በአዲሱ የእስራኤልና የሂዝቦላህ አውዳሚ ጦርነት ላይ ቢሆንም፣ የግብፅ የጦር መርከብ ለሶማሊያ ሁለተኛውን ዙር የጦር መሣሪያ ጭነት ማድረሱ ሰፊ ሽፋን ያገኘ ዜና ነበር፡፡ ግብፅ ከሶማሊያ ጋር ባደረገችው ወታደራዊ ስምምነት መሠረት በይፋ የጦር መሣሪያዎችን ስታጓጉዝ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባዔ ለመታደም የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ታዬ አጽቀ ሥላሴ (አምባሳደር) መሣሪያዎቹ አሸባሪዎች እጅ ወድቀው ችግር እንዳይፈጠር ማሳሰባቸው ተሰምቷል፡፡ የአፍሪካ ቀንድ ከወትሮ በባሰ ሁኔታ ወደ ለየለት ቀውስ ውስጥ የሚከተው አደገኛ ክስተት እየተፈጠረ ሲሆን፣ ውስጣዊ ሰላሟ የታወከው ኢትዮጵያ ህልውናዋን ሊፈታተን የሚችል ከባድ ጊዜ እየተጋረጠባት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በበርካታ አውሮፕላኖች የጦር መሣሪያዎችን ለሶማሊያ ያቀረበችው ግብፅ ድርጊቷን አጠናክራ ስትገፋበት፣ የኢትዮጵያን ህልውና ከፈተና ለመከላከል የላላውን አገራዊ አንድነት ለማጠናከር የሚረዱ ዕርምጃዎች ላይ ማተኮር የግድ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በይፋ የመሠረት ድንጋዩ ከተጣለ ከመጋቢት 2003 ዓ.ም. ጀምሮ ከግብፅ ጋር የገባችበት እሰጥ አገባ፣ ከተደጋጋሚ አሰልቺ ንግግሮችና ድርድሮች አልፎ ለህልውናዋ አደገኛ የሆኑ ግጭቶችና አውዳሚ ጦርነቶች ውስጥ ገብታለች፡፡ ኢሕአዴግን ከ27 ዓመታት መንበረ ሥልጣኑ ላይ ገፍትሮ በጣለው ሕዝባዊ ተቃውሞ አማካይነት አዲስ የለውጥ መንግሥት ቢመጣም፣ ለውጡን በተጀመረበት ፍጥነትና ግለት በአንድነት በሥርዓት ለማስኬድ መደረግ የነበረበት ጥረት ተቀልብሶ በየቦታው ግጭቶች ተበራክተው ነው የቀጠሉት፡፡ በአራቱም ማዕዘናት አንዴ ሞቅ አንዴ በረድ ያሉ አጋጣሚዎች ቢፈጠሩም፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደው አውዳሚ ጦርነት ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ያደረሰ ነበር፡፡ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሠረት ጦርነቱ ቢገታም፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ተጠናክሮ በመቀጠሉ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡

የውስጥ ሰላም ተቃውሶ መፍትሔው በእጅጉ በራቀበት በዚህ ጊዜ አገር ዙሪያዋን በታሪካዊ ባላንጣ እየተከበበች ነው፡፡ ግብፅ የኢትዮጵያን የሰላም አስከባሪነት ሚና በመንጠቅ በሶማሊያ ለመስፈር ከምታደርገው እንቅስቃሴ በተጨማሪ፣ በሁለትዮሽ ስምምነት ግዙፍ ሠራዊት ለማስገባት ከፍተኛ ጥረት እያደረገችም ነው፡፡ ይህ አልበቃ ብሏት ከኤርትራ ጋር ወዳጅነቷን ለማጠናከር ገባ ወጣ እያለች ስትሆን፣ ሰሞኑን ደግሞ በደቡብ ሱዳን ሰላም አስከባሪ ሆና የመግባት ውጥኗ ተሰምቷል፡፡ ይህ የግብፅ ድርጊት ከዲፕሎማሲው ግብግብ ባሻገር ከፍተኛ የሆነ ውስጣዊ ዝግጅት እንደሚያስፈልገው ማንም አይስተውም፡፡ ለዚህ ደግሞ በአገር ውስጥ የሚካሄዱ ሁሉም ግጭቶችና ውጊያዎች በፍጥነት እንዲቆሙ ማድረግ ተቀዳሚ ዓላማ መሆን ይኖርበታል፡፡ ለሁሉም አለመግባባቶችና ግጭቶች ምክንያት ለሆኑ ጉዳዮች በጋራ መፍትሔ የሚፈለግበት መደላድል እንዲመቻች በቅን ልቦና ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ መቀጠል የሚጠቅመው ታሪካዊ ጠላትን ብቻ ነው፡፡

ሕዝብና መንግሥት በአገር ልማት፣ የወደፊት ተስፋና ህልውና ላይ የጋራ መግባባት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ገዥው ፓርቲና ተፎካካሪዎቹ ከባላንጣነት በላይ በሠለጠነ መንገድ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማሳመር የጋራ ግብና ራዕይ ሊኖራቸው የግድ ይላል፡፡ የወጣቶች፣ የሴቶች፣ የሲቪክ ማኅበረሰቦች፣ የሙያና የጥቅም ማኅበራትና የተለያዩ ፍላጎቶችን የሚወክሉ አደረጃጀቶች በነፃነት ሥራቸውን የሚያከናውኑበት ምኅዳር ሲኖር ለአገር ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል፡፡ የፍትሕ አካላትና የፀጥታ ኃይሎች ተግባራቸውን በነፃነትና በገለልተኝነት ሲያከናውኑ፣ ለቅሬታ ምክንያት የሚሆኑ ችግሮች የሚፈጠሩበት ዕድል አይኖርም፡፡ በአጠቃላይ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲከበሩ ዜጎች በነፃነትና በኃላፊነት ሐሳባቸውን ለመግለጽና የሚፈለግባቸውን ለማበርከት አያዳግታቸውም፡፡ በአገር ውስጥ ለፀብና ለግጭት መንስዔ ሊሆኑ የሚችሉ ችግሮች በጋራ ጥረት ሲወገዱ፣ አገር በቀላሉ የማንም የጥቃት ዒላማ አትሆንም፡፡ እንደ ብረት ጠንካራ መሆን ሲቻል ማንም አይደፍርም፡፡

በአሁኗ ኢትዮጵያ ሕዝቡን ለጋራ ዓላማ አስተሳስሮ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በቋንቋና በፖለቲካ አመለካከት ልዩነትን እያሰፉ ከመገፋፋት ይልቅ እንደ ቀድሞዎቹ ጀግኖች አባቶችና እናቶች፣ የጋራ የሆነች አገርን ጥቅም የማስቀደም አስፈላጊነት ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ለተወሰነ ቡድን ጥቅምና ፍላጎት ሲባል ብቻ በሚደረግ ሽኩቻ የአገርና የሕዝብ ህልውና አደጋ ውስጥ ይገባል፡፡ ለዘመናት በመከባበርና በመፈቃቀድ ልዩነቶቹን አቻችሎ ለአገሩ ዳር ድንበር መከበር ሕይወቱን በፈቃደኝነት ሲገብር ለኖረው ለዚህ ጀግና ሕዝብ፣ ሰላሙንና አንድነቱን የሚገዘግዙ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች መገታት አለባቸው፡፡ የዓለም ጥቁር ሕዝቦችን በተጋድሎው በአንድነት ያስተሳሰረ ይኼ ጀግና ሕዝብ፣ በስሜታዊነትና በደም ፍላት በሚቅበዘበዙ ወገኖች ምክንያት ሊፈታ አይገባውም፡፡ ከአገሩ አንድነትና ህልውና በላይ ምንም የሚበልጥበት ነገር እንደሌለ ታሪክ ምስክር ነው፡፡

ነገር ግን ታሪካዊ ጠላት የእርስ በርስ ግጭቱ እሳት ላይ ነዳጅ እያርከፈከፈ ሲያጋግመው፣ ገመናችንን ለዓለም እያሳየ ኢትዮጵያን የግጭት ተምሳሌት መሆኗን ያጋልጣል፡፡ የውጭ ኢንቨስተሮች ተረጋግተው እንዳይሠሩ ውስጣዊ ግጭቶችን ያባብሳል፡፡ የልማት አበዳሪ ተቋማት ብድርና ድጋፍ እንዳይሰጡ መሰናክል ይፈጥራል፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያን በጥርጣሬ እንዲያዩ ሴራ ይሸርባል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የአፍሪካ ኅብረት ሰላም የለም በማለት መቀመጫቸውን እንዲቀይሩ ይገፋፋል፡፡ በገዛ ራሳችን በፈጠርነው ችግር ምክንያት ጠላት መሀላችን እየገባ ክፍፍሉን የበለጠ ያጧጡፈዋል፡፡ የጎረቤት አገሮችን ሳይቀር በኢትዮጵያ የደኅንነት ሥጋት እየተፈጠረባቸው እንደሆነ በማስመሰል የጥፋቱ ተባባሪ ያደርጋቸዋል፡፡ እንኳንስ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን የአገሪቱ ህልውና ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አጣብቂኝ ውስጥ ይገባል፡፡ ዙሪያውን ከበባ መሰል እንቅስቃሴ እየተጠናከረ ስለሆነ፣ የአገር ህልውና እንዲከበር ውስጣዊ የሰላም ዕጦት ይታሰብበት!