September 25, 2024 – Konjit Sitotaw 

የጸጥታ አስከባሪዎች ጨዋነት በተሞላና ክብርን በሚገልጽ አግባብ የፍተሻ ሥርዓቱን እንዲያከናውኑ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አሳሰበች

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባህር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የ2017 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓልን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁና የቅድመ ጥንቃቄ መልዕክት አስተላለፉዋል።

ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በመልዕክታቸው በዓሉ በድምቀት፣ባማረና በሰመረ መልኩ ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ ሕዝበ ክርስቲያኑ በንቃትና በሕብረት በመሆን ከጸጥታ አካላትና ቤተክርስቲያኒቱ ለዚሁ ዓላማ ካቋቋመቻቸው የኮሚቴ አባላት ጭምር በመተባበር እንዲሰራ አደራ ብለዋል።

የመንግሥት የጸጥታ ተቋማት በዓሉ ያለ አንዳች የጸጥታ ችግር ተከብሮ መዋል እንዲችል ከጠቅላይ ቤተክህነት ዐቢይ ኮሚቴ ጋር በጥምረት እየሰራ እንደሚገኝ የጠቀሱት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በበዓሉ ወቅት ለሚደረግ ፍተሻ ፍፁም ክርስቲያናዊ ትብብር እንዲያደርግ አደራ ብለዋል።የጸጥታ አስከባሪዎችም ጨዋነት በተምላና ክብርን በሚገልጽ አግባብ የፍተሻ ሥርዓቱን እንዲያከናውኑ አሳስበዋል።

በመጨረሻም በዓሉን ስናከብር ፍቅር ሰላምንና አንድነትን እንዲሁም መግባባትን መርህ ባደረገ አግባብ መሆን አለበት ያሉት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በዓሉ ሥጋዊ ፈቃዶቻችንን የምንፈጽምበት ሳይሆን ንስሐ ያልገቡ ንስሐ የሚገቡበት የተጣሉ የሚታረቁበት የተለያዩ አንድ የሚሆኑበት የተራራቁ የሚቀራረቡበት ፍፁም የደስታና የሰላም በዓል ሆኖ እንዲከበር ማድረግ ይኖርብናል በማለት መልዕክታቸውን አጠናቀዋል።