በደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው የሕወሓት ጠቅላላ ጉባዔ በተካሄደበት ወቅት

ፖለቲካ

ዮናስ አማረ

September 25, 2024

ከአቶ መለስ ዜናዊ ሕልፈት በኋላ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴና የኢሕአዴግ ምክር ቤት አባል በመሆን ከፅድቁም ሆነ ከኃጢያቱ ተቋዳሽ ሆኛለሁ የሚሉት የኢሕአዴግ የቁልቁለት ጉዞ (ከ2005 እስከ 2010) የስብሰባዎች ወግ መጽሐፍ ደራሲ ብርሃነ ፅጋብ፣ በአንጋፋው ድርጅት ሕወሓት ውስጥ ቀውስ መብቀል የጀመረው ከመለስ ዜናዊ ሞት ጀምሮ እንደሆነ ደጋግመው ይጠቅሳሉ፡፡

በትግራይ ክልል የሚስተዋለው የፓርቲና የመንግሥት ሚና መደበላለቅ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ

‹‹ከአቶ መለስ ዜናዊ ሕልፈተ ሕይወት በኋላ እየተባባሰ የሄደው የሥልጣን ሽኩቻ ድርጅቱ የቁልቁል ጉዞ እንዲጓዝ ያደረገው ቢሆንም፣ በመጋቢት 2009 ዓ.ም. የተካሄደው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ የሚሳይል ተኩስ ግን የቁልቁለት ጉዞውን ወደ ፈጣን ሩጫ ቀይሮታል፡፡ ከመጋቢት 2009 ዓ.ም. ጀምሮ አቶ ዓባይ ወልዱ የክልሉን መንግሥት ለመምራት ሲወስኑ እነ አቶ ዓለም ገብረዋህድ ግን በሕይወት አድን ከባድ የጥድፊያ ሩጫ ውስጥ ገብተው፣ ከአቶ በየነ ምክሩና ሌሎች የተተኩ ነባር አመራሮች ጋር ጊዜያዊ የጥፋት ግንባር መሥርተው ሳይቀድሙን እንቅደማቸው በሚል ፈሊጥ የጥልቅ ተሃድሶ ፍልሚያ እንዲታወጅ አድርገዋል፡፡ ለዚሁ የሚሆን የሴራ ሰነድ ለወራት ያህል ኢመደበኛ በሆነ መንገድ ምክክር አድርገው በኮንትሮባንድ መልክ ለአጀንዳ እንዲበቃ አድርገውታል፤›› በማለት ነበር ጸሐፊው ያስረዱት፡፡

‹‹የጥልቅ ተሃድሶ ሽብር›› በሚለው ምዕራፍ ኢሕአዴግ ክፉኛ ቀውስ በጠናበት የመጨረሻዎቹ ወቅቶች፣ የሕወሓት ሕመም ደግሞ ዘርፈ ብዙ መልክ ያለው ሆኖ እንደነበር ጸሐፊው በሰፊው ተርከዋል፡፡ ኢሕአዴግ በሕዝባዊ ተቃውሞ ተወጥሮና በለውጥ ጥያቄ የፊጥኝ ተይዞ በነበረበት በዚያ የመጨረሻ ሰዓት፣ ሕወሓት ውስጥ ግን የሥልጣን ሽኩቻው ደርቶ እንደነበር ያወሳሉ፡፡

ጥልቅ ተሃድሶ እያለ ሁሉም የኢሕአዴግ ግንባር ድርጅቶች ውስጣዊ ግምገማ ወደ ማድረግ ውስጥ ሲገቡ፣ ሕወሓትም በበኩሉ የአመራር የሥልጣን ግብግብ ጠንቶበት ነበር ይላሉ፡፡ በጊዜው የፍልሚያውን ሜዳ በበላይነት ለመጨበጥ ደግሞ አቶ ዓባይ ወልዱና ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) የቡድን አባቶች ሆነው ቦታውን መያዛቸውን ነው ጸሐፊው የተረኩት፡፡ የኮንትሮባንድ ያሉት ከየት እንደመጣ የማይታወቅ ሰነድ በሕወሓት ጽሕፈት ቤት በኩል ቀርቦ እንገማገም፣ ተሃድሶ እናድርግ፣ ሂስና ግለሂስ እናውርድ ወደሚል የስብሰባ ፍልሚያ መገባቱንም ይዘረዝራሉ፡፡

በዚህ መሰሉ መንገድ አንዱ ሌላውን ሰልቅጦ ለመብላት ከ2009 ጀምሮ እስከ 2010 ዓ.ም. ጭምር የሕወሓት አመራሮች በየስብሰባ አዳራሹ መተጋተግን አዘወተሩ ይላሉ፡፡ ደፈጣውም ሆነ ኔትወርክ መፍጠሩ የበዛ በነበረባቸው በእነዚያ የስብሰባዎች ጦርነት ሰሞን አቶ ዓባይ ወልዱ ከሁሉም ተሰብሳቢ ጋር ለመገናኘትና እኩል ቀረቤታ ለመፍጠር ሲጥሩ ይታይ እንደነበር ጠቅሰው፣ ነገር ግን ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ከየትኛው ካምፕ እንደሆኑ ለማወቅ ይቸገሩ እንደነበር ያወሳሉ፡፡

አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) ራሳቸውን ነጠል አድርገው ከውስን ሰዎች ጋር ሲንቀሳቀሱ፣ ወ/ሮ አዜብ መስፍን ደግሞ ከአዳዲስ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ጋር ይታዩ በነበረበት በዚያ የስብሰባ ሰሞን ከነባሮቹ ታጋዮች አቶ ስብሀት ነጋ በበኩላቸው፣ በየሻዩ እረፍት ወደ ሁሉም ሰው እየሄዱ የሚፈልጉትን ሐሳብ ለማስተላለፍ ሲጣጣሩ ይታዩ ነበር ብለዋል፡፡

ሌላዎቹ አንጋፋ የሕወሓት ታጋዮች ሟቾቹ አቶ ዓባይ ፀሐዬና ሥዩም መስፍን (አምባሳደር) ‹‹ከማኅበረ ገስገስቲ ብሔረ ትግራይ (ማገብት) ምሥረታ ጀምሮ ያቀኑትን በአፍሪካ አንጋፋ ከሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ የሚባለው ሕወሓትን ከደደቢት ጀምሮ ያለፈበትን ዕድገት፣ እርጅናውንና ሕመሙን በጥንቃቄ እየታዘቡ ያሉ ይመስላሉ፤›› በማለት ጸሐፊው አስፍረዋል፡፡ ሁለቱ አንጋፋ የሕወሓት መሥራቾች በሚያደርጓቸው ጠንቃቃ ንግግሮች ከየትኛውም ቡድን ያልወገኑ መምሰላቸውን በብቃት እየተወኑት የነበረ ቢሆንም፣ በሕወሓት ጽሕፈት ቤት በኩል የቀረቡ የኮንትሮባንድ ሰነዶችን በማዘጋጀት እጃቸው የለበትም ማለት እንደማይቻል ነው የጸሐፊው ትዝብታቸውን ያጋሩት፡፡ ሌላኛው ሟቹ አንጋፋ የሕወሓት ታጋይ አስመላሽ ደምሴ ግን ከእነ ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ክንፍ ጋር አብረው መቆማቸውን የሚጠቁመው የብርሃነ ፅጋብ መጽሐፍ፣ ለረዥም ጊዜ በቀጠለ የስብሰባ ፍልሚያ ተተጋትጎ የእነ ዓባይ ወልዱን አመራር በማስወገድ የሕወሓትን የአመራር የበላይነት ለመጠቅለል የበቃውም ይኸው ቡድን መሆኑን ከትቧል፡፡

በደብረ ጽዮን (ዶ/ር) የሚመራው ከዚያ ወዲህ ማለትም ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ የሕወሓት ድርጅታዊ ሥልጣንን ጠቅልሎ በመያዝ ቆይቷል፡፡ ሕወሓት የኃይል የበላይነት ጨብጦ የቆየበት ከስድስት ሚሊዮን በላይ አባላት ያሉኝና በአፍሪካ እንደ ኤኤንሲ ካሉ ፓርቲዎች የማልተናነስ ነኝ የሚለው ኢሕአዴግ፣ በሕዝባዊ የለውጥ ጥያቄ መጠናከር የተነሳ ሥልጣኑ አጣብቂኝ ውስጥ ሲወድቅና በስተመጨረሻም ድርጅታዊ መበታተን ሲገጥመው የእነ ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) አመራር በሕወሓት ወሳኝ ሥልጣን ላይ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ተፈረካክሶ ብልፅግና ሲመሠረትና ሕወሓት ወደ መቀሌ ሲያፈገፍግም ቢሆን አመራር በድርጅቱ ውስጥ ወሳኙን ቦታ ይዞ ነበር፡፡ በአፍሪካ ከፍተኛ ዕልቂት ማስከተሉ የሚነገርለት የትግራይ በኋላም የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሲፈነዳና ለሁለት ዓመታት ሲካሄድም ይሄው ቡድን ነበር ሕወሓትን የሚመራው፡፡ ሕወሓት ጠፍቶ የተበተነ ዶቄት ነው ሲባልም ይኸው ኃይል ነበር የድርጅቱን የበላይነት ይዞ የዘለቀው፡፡ ከዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ውስጥ ወጥቶ በስተመጨረሻ የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት ሲፈረምም ሕወሓት በእነ ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) እጅ ነበር፡፡

ከዚህ ሁሉ ዑደት በኋላ ግን ድርጅቱ አቶ ብርሃነ ፅጋብ ‹‹የኢሕአዴግ የቁልቁለት ጉዞ የስብሰባዎች ወግ›› በሚለው መጽሐፋቸው ሕወሓት ከመለስ ዜናዊ ሞት በኋላ የሥልጣን ሽኩቻ ውስጥ የወደቀ ድርጅት ሆኗል ብለው ደጋግመው እንደከተቡት ሁሉ፣ ተመልሶ ወደ ሥልጣን ሽኩቻ አዙሪት ሲገባ ነበር የታየው፡፡

በአንድ ወቅት ከኤኤንሲ የሚስተካከል የተባለለትን ኢሕአዴግን ያዋለደው ሕወሓት እነሆ አሁን በከባድ ውስጣዊ ሽኩቻ ውስጥ ይገኛል፡፡ የሕወሓት ጽሕፈት ቤትን በሚመራው የእነ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ቡድን፣ በእነ ጌታቸው ረዳ ከሚመራው ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ሕወሓት ጋር ከባድ ፍጥጫ ውስጥ ገብቷል፡፡

 ሕወሓት የሰላም ስምምነቱን መሠረት በማድረግ ሕጋዊ ሰውነቱን በምን መንገድ ማስመለስ አለበት የሚለው ጥያቄ እስከ ፌደራል መንግሥቱ፣ እንዲሁም እስከ ምርጫ ቦርዱ የደረሰ የሁለቱ ሕወሓቶች አንዱ የመወዛገቢያ አጀንዳ ነበር፡፡ በመቀጠልም ሕወሓት በሽኩቻ የተሞሉ ስብሰባዎች በሚካሄዱበት ሰሞን ወይም ከጦርነቱ በፊት ከተካሄደው የጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባው በኋላ 14ኛ ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባዔውን ማድረግ አለበት የለበትም የሚለው ክርክር ደግሞ ሌላኛው የሽኩቻቸው ማዕከል ሆኖ ተከሰተ፡፡

አንዱ ሌላውን ዕውቅና መንፈጉም ቀጠለ፡፡ በጊዜያዊ አስተዳደሩና በፌደራል መንግሥቱ የተወገዘ ጠቅላላ ጉባዔ ያደረገው የእነ ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ቡድን በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ያሉ ሕወሓቶች አይወክሉኝም ከድርጅቴም አሰናብቼያቸዋለሁ ማለቱ ተሰማ፡፡

በሁለቱ የሕወሓት ቡድኖች መካከል 60 ቀናት የፈጀ ጉባዔና ድርጅታዊ ስብሰባዎች መካሄድ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በየስብሰባ አዳራሾቹ ተገድቦ የቆየው ሽኩቻና ልዩነት፣ ቀስ በቀስ እየጋለ ገንፍሎ ወጥቶ የሚዲያ መተጋተግን ወልዷል፡፡ በየአጋጣሚው አንዱ ሌላውን የሚያወግዝ መግለጫ ከማውጣት ጀምሮ፣ በየሚዲያው የሁለቱ ቡድን አመራሮች እየቀረቡ ነጥብ ማስቆጠሪያ ያሏቸውን ሚስጥራዊ መረጃዎች ማሠራጨት ቀጥለዋል፡፡

ይህ ደግሞ ሄዶ ሄዶ አንዱ ሌላውን ከኤርትራ ጋር በማሴር እስከ መወንጀል ሲደርስ ነው የታየው፡፡ የእነ ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ቡድንም ሆነ የእነ አቶ ጌታቸው ቡድን በእስካሁን ሒደት ከቃላት ውርወራ ባለፈ ወይም ዕርምጃ እወስዳለሁ ብሎ ከማስጠንቀቅ ባለፈ በተግባር ወደ ዕርምጃ አልገቡም፡፡

ይሁን እንጂ ሁለቱ ቡድኖች በተከታታይ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን በክልሉ ለማድረግ በሚንቀሳቀሱባቸው አጋጣሚዎች፣ በሕዝባዊ ተቃውሞዎች እንዲቋረጡና መድረኮቻቸው እንዲስተጓጎሉ የማድረግ ሴራዎችን አንዱ በሌላው ላይ እየፈጠሩ ነው ይባላል፡፡ ይህ ቢባልም ነገር ግን የእነ አቶ ጌታቸው ሕወሓት በሕዝብ ተቃውሞ የተነሳ ስብሰባ ለማድረግ በተቸገረባቸው እንደ ሽሬ ባሉ ከተሞች ሳይቀር የእነ ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ሕወሓት ያለ ኮሽታ ስብሰባ ሲያካሂድ መታየቱ፣ የትኛው ቡድን ስብሰባዎችን የማወክ አቅም እንዳለው ጠቋሚ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡

የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት ሕጋዊ ባለቤት እኔ ነኝ የሚለው ክርክር በሁለቱ ወገኖች መካከል ብዙ ሲያነታርክ የቆየውን ያህል፣ በሒደት ግን ፕሪቶሪያ ሄዶ የሰላም ስምምነቱን የተፈራረመው የእነ አቶ ጌታቸው ቡድን ከተሰጠው ኃላፊነት ውጪ በመውጣት የትግራይን ጥቅም አሳልፎ የሰጠ የስምምነት ሰነድ ተፈራርሞ ነው የተመለሰው የሚል ውንጀላ ሲሰማበት ነው የቆየው፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ግን ከዚህ በተቃራኒ እንዲያውም ስምምነቱን በቶሎ ፈርማችሁ ተመለሱ ይል የነበረው የእነ ደብረ ጽዮኑ (ዶ/ር) ሕወሓት ነው በማለት ነበር ለዚህ አጸፋ ሲሰጥ የቆየው፡፡

በትግራይ ክልል በአሁኑ ሰዓት በሁሉም ጉዳይና በሁሉም አጀንዳ ላይ በሁለቱ የሕወሓት ክንፎች መካከል መናቆሩና መቆራቆዙ የበዛ ይመስላል፡፡ ይህ ሁኔታ የበለጠ ከተካረረ ደግሞ አንዱ ወገን የፀጥታ ኃይል የሚባለውን ወይም በጦርነቱ ወቅት የትግራይ ሠራዊት (ቲዲኤፍ) ሲባል የቆየውንና እስካሁንም ጠብመንጃ ያልፈታውን ኃይል ጣልቃ ወደሚያስገባ ግጭት ጉዳዩ ሊያመራ እንደሚችል እየተሠጋ ይገኛል፡፡

ከዚህ በመለስ የሁለቱ ሕወሓት ክንፎች ፍጥጫ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ባህል ለረዥም ዛሬም መቀጠሉ የሚነገረው የመንግሥትና የፓርቲ ሚና መደበላለቅ ጉዳይን እንዲነሳ እያደረገ ይገኛል፡፡ በቅርቡ መንግሥትና የፖለቲካ ፓርቲ ሚና መደበላለቅ ጉዳይ ያሳሰበው የሚመስለው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ ችግሩ በአገሪቱ ውስብስብ ደረጃ ላይ ይገኛል ሲል መግለጫ ማውጣቱ አይዘነጋም፡፡

በትግራይም ያለው ሁኔታ ከዚህ የተለየ አለመሆኑን የሚጠቅሱ አንዳንድ ወገኖች በበኩላቸው፣ በክልሉ በሁለቱ ሕወሓቶች መካከል የተፈጠረው መሻኮትና የፖለቲካ መቃቃር የዚሁ የፖለቲካ ፓርቲና የመንግሥት መዋቅር ድንበር በጠራ ሁኔታ ታውቆ ባለመሰመር የመጣ ችግር እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

አንጋፋው የቀድሞ የሕወሓት አመራር ገብሩ አሥራት በቅርብ ጊዜ ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ ጊዜያዊ አስተዳደሩን የሕወሓት ፓርቲ አላሠራ እንዳለው ተናግረው ነበር፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከላይ ተንሳፎ ታች ሕዝቡ ጋር ሳይገናኝ እንዲቀር መደረጉን አመልክተው በክልሉ አሁንም ድረስ ታች ቀበሌ ድረስ መዋቅር ዘርግቶ ሕዝቡን እንደፈለገ የሚያደርገው ሕወሓት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የድርጅት መዋጮዎችን ሁሉ ከሕዝቡ እንደሚሰበስብ ነው አቶ ገብሩ የተናገሩት፡፡ 

ይህንን ሐሳብ የሚደግፍ አስተያየት የሚሰጡ አንዳንድ ወገኖች በቅርቡ የጊዜያዊ አስተዳደሩ የሕወሓት አመራር በየአካባቢው በመዘዋወር ከሕዝቡ ጋር ምክክር ለማድረግ የጠራቸው ስብሰባዎች፣ በረብሻ የተበተኑበትን አጋጣሚ የዚህ ውጤት እንደሆኑ ያወሳሉ፡፡

ሕወሓት ኢሕአዴግ በነበረበትም ጊዜ ይሁን ብቻውን በቆየባቸው ጊዜያት የሚቀናቀኑት ኃይሎችን ከታች ከቀበሌ ጀምሮ ጠርንፎ በሚፈጥራቸው የአደረጃጀት ህዋሶች ተቃውሞ እንዲነሳባቸው ማሴሩ የተለመደና የቆየ የፖለቲካ ሥልት መሆኑን በመጠቆም፣ አንዳንድ የትግራይ ፖለቲካ ምሁራን ሲተቹ ታይተዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ከየአቅጣጫው ከሚሰነዘረው አስተያየት በተጨማሪ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ውዝግቡ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ገና ሲጀምር አንስቶ ይህን ወቀሳ ያቀርብ እንደነበር አንዳንዶች ያስታውሳሉ፡፡

በጥቅምት መጀመሪያ 2016 ዓ.ም. ውዝግቡ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአደባባይ የበቃው፣ በፓርቲውና በጊዜያዊ አስተዳደሩ መካከል የጣልቃ ገባህብኝ ጭቅጭቅ በመፈጠሩ እንደነበር መለስ ብለው ያወሱታል፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ አልታዘዝም አሉኝ ያላቸውን ሦስት ካድሬዎች ከወረዳ የሥራ ኃላፊነቶች በማንሳቱ፣ ከፓርቲው ጽሕፈት ቤት ባለሥልጣናት ጋር እንዳወዛገበው በወቅቱ ይደረጉ ከነበሩ የመግለጫ ልውውጦች መታዘብ ይቻል ነበር፡፡

በሌላ በኩል ሕወሓት በመቀሌ ጠራሁት ያለውን የካድሬዎች ስብሰባ ማድረግ እንደሌለበት ጠቅሶ፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ያለው ሕወሓት ያሰማው ቅሬታም የፓርቲና የመንግሥት ሚና ልዩነት ድንበር ተጥሷል የሚል ክርክር አስነስቶ ነበር፡፡

የበለጠ ጉዳዩን ያወሳሰበው ደግሞ ወደ ተፈናቀሉባቸው አካባቢዎች ተመልሰው ይስፈሩ ተብሎ ተፈናቃዮችን ማስፈር በተጀመረበት ወቅት፣ በሕወሓትና በጊዜያዊ አስተዳደሩ መካከል ሰፊ ልዩነት ተፈጠረ መባሉ እንደነበር ይታወሳል፡፡

የፌዴራል መንግትና የአማራ ክልል አስተዳደር የትግራይ ተፈናቃዮችን መልስ ለማስፈር እንቅፋት ሆነዋል በሚል በመጀመሪያ ሲወቀሱ ቆዩ፡፡ ይሁን እንጂ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ዘግይቶ ይፋ ባደረገው መረጃ ጉዳዩ የተደናቀፈው የሕወሓት ጽሕፈት ቤት ተፈናቃዮች ወደ የሚመለሱባቸው አካባቢዎች፣ የቀደመው የአስተዳደር አብሮ ካልተመለሰ የሚል አቋም በመያዙ እንደሆነ ነው ያረጋገጠው፡፡

ሕወሓት ተፈናቃዮቹን መልሶ የማስፈሩ ሥራ ከካድሬዎች መልሶ ማስፈር ጋር አብሮ ካልተከወነ ማለቱ የችግሩ ምንጭ ነው መባሉ ከባድ የፖለቲካ ውዝግብ አስነስቶ ነበር፡፡ ተፈናቃዮቹን መልሶ በማስፈሩ ሥራ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ነው የሚያገባው ወይስ ሕወሓት የሚለው በትግራይ የፓርቲና የመንግሥታዊ ድንበር መዋቅር አይታወቅም የሚል አስተያየት ያሰጠ ነበር፡፡ 

ይህን በሚመለከት አስተያየት የተጠየቁ የትግራይ ፖለቲካን በቅርበት የሚከታተሉ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ ግን፣ የመንግሥትና የፖለቲካ ፓርቲ ሚና በትግራይ መጣረስ ጀምሯል የሚለውን መላምት ፈጽሞ እንደማይቀበሉት ነው የሚገልጹት፡፡ ‹‹ሲጀመር የትግራይ ክልል ሁኔታ ገና ወደ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ አልተመለሰም፡፡ ልክ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ በአፋር፣ ወዘተ እያልን የሌሎች ክልሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮችን እንደምንመዝነው ሁሉ የትግራይንም ሁኔታ በተመሳሳይ መነጽር ማየት አንችልም፡፡

‹‹ትግራይ ክልል እንደ አንድ ሉዓላዊ ክልል ሆኖ በእግሩ ገና አልቆመም፡፡ በተወካዮች ምክር ቤትም ሆነ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ተወካዮች የሉትም፡፡ መደበኛ የምርጫ ሥርዓት አድርጎ መሪዎቹን ገና መርጦ መደበኛ ክልላዊ መንግሥት አልመሠረተም፡፡ በትግራይ ክልልና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ያለው ግንኙነት ራሱ በአንዲት የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት ሰነድ ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የዚህ ሰላም ስምምነት ውጤት ነው፡፡ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ሹመት የፀደቀውም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ ስለዚህ ልክ መደበኛ መንግሥታዊ መዋቅር በክልሉ እንደተዘረጋ ሁሉ፣ የጊዜያዊ አስተዳድሩ ድንበርና ሥልጣን ተጣሰ/አልተጣሰ ብሎ ለመፍረድ ያስቸግራል፤›› ብለዋል፡፡

በትግራይ መደበኛ የካቢኔ ስብሰባዎችን ማካሄድ ራሱ ብርቅ በሆነበት፣ ወደ 250 ሺሕ ትጥቅ ያልፈታ ኃይልን ትጥቅ አስፈትቶ ሥልጠና ሰጥቶ ወደ መደበኛ ሕይወት ማስገባት ገና ሳይቻል፣ የትግራይ ክልል አስተዳደርና ሙሉ መሬት ሳይመለስ፣ እንዲሁም የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀዬአቸው ሳይመለሱና የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት አንቀጾች በተጨባጭ ወደ መሬት ሳይወርዱ የሁለቱ የሕወሓት ኃይሎች ፀብ የፓርቲና የመንግሥት ሚና መደበላለቅ ነው ብሎ ለመግለጽ እንደሚቸገሩ አስረድተዋል፡፡

‹‹ትግራይና የፌዴራል መንግሥቱ በሰላም ስምምነቱ እንጂ በሕገ መንግሥቱ አይደለም ግንኙነታቸው፡፡ ስምምነቱ ተሟልቶ ሲፈጸም፣ ወደ መደበኛ ሥርዓት ትሸጋገራለች፡፡ አሁን ሁሉም ሥልጣኑን ስለሚፈልጉ የሰላም ስምምነቱን ተፈጻሚ የማድረጉን ሥራ ትተው እርስ በእርስ ወደ መሻኮቱ ገብተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ድንገት በዚህ መካከል አንፃራዊ መረጋጋት የፈጠረው የፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነት ቢቀደድ ያ ክልል ወዴት እንደሚሄድ አይታወቅም፤›› በማለትም አክለዋል፡፡

‹‹ጌታቸው ረዳ የተቀመጡበት ወንበር እሳት ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ጤነኛ ሰው ትግራይ ውስጥ ፕሬዚዳንት ካልሆንኩ ብሎ አይጣላም፤›› ሲሉ ያስረዱት የፖለቲካ ተንታኙ፣ የፕሪቶሪያውን ስምምነት ማስፈጸም ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዘበዋል፡፡ የጊዜያዊ አስተዳደሩ የሕወሓት ፓርቲ ጽሕፈት ቤት አላሠራ አለኝ ቢልም ሆነ ወይም ፓርቲው ጊዜያዊ አስተዳደሩን እንቅፋት ሆነብኝ ብሎ ቢወነጅል፣ ተጨባጭ የፓርቲና የመንግሥት ሚና መጣረስ ኖሮ ሳይሆን የፖለቲካ ሥልጣንን ማዕከል ያደረገ ሽኩቻ እንደሆነ እንደሚያዩት አክለዋል፡፡    

በቅርቡ የጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚያወጣቸው መግለጫዎች የእነ ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ቡድን ሕጋዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ባለመሆኑ፣ የፀጥታ ኃይሉ ሥርዓት ማስከበር እንደሚገባው የሚጠይቅ ይዘት አላቸው፡፡

በተቃራኒው ሕወሓት በሚሰጣቸው መግለጫዎች የጊዜያዊ አስተዳደሩ ቡድን ከሕገወጥ እንቅስቃሴው ካልተቆጠበ እንደማይታገስ የሚያሳስቡ ሐረጎች ሲይዙ ይታያል፡፡ አንዱ ሌላውን እንቅፋት እንደሆነበትና ዕርምጃ ለመውሰድ ትዕግሥቱ እንዳለቀ ሲገልጽ መሰማቱ እየተለመደ ነው፡፡

የሁለቱ የሕወሓት ቡድን አመራሮች በፓርቲው የሕጋዊ ሰውነት ማስመለስ ጥያቄ፣ በጠቅላላ ጉባዔ ማድረግ ጉዳይ፣ በፕሪቶሪያ ስምምነት ባለቤትነትና በሌሎችም ዘርፈ ብዙ የክልሉ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ የጀመሩት መወነጃጀልና የቃላት ውርወራ አሁን ገለልተኛ ሆኖ ለረዥም ጊዜ የቆየ የሚመስለውን የፀጥታ ኃይሉን ወደ መጋበዝ እያመራ ያለ ይመስላል፡፡ የፀጥታ ኃይሉ በዚህ መጓተት ወደ የትኛው ቡድን ያመራል የሚለው ወሳኝ ጥያቄ እየሆነ የመጣ ይመስላል፡፡

በትግራይ ክልል መደበኛ መንግሥት እስኪመሠረትና ሁኔታዎች እስኪስተካከሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ተመሠረተ ተብሎ ብዙ በጎ ተስፋዎች ቢፈነጥቅም፣ በሒደት ግን የሕወሓትና የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሽኩቻ በክልሉ ሰላም ላይ ጥላውን ያጠላ ይመስላል፡፡ ይህ ቀውስ የአንዱ ቡድን አመራር የሌላውን ቡድን አመራር ሚስጥር በየዩቲዩቡ እየዘረገፈ በየምሽቱ ነጥብ ለማስቆጠር በሚጥርበት ሁኔታ ብቻ ተገድቦ የሚቆምም አይመስልም፡፡ አንዱ ሌላውን እንቅፋት ሆነብኝ ብሎ ወደ ተግባር ዕርምጃ መውሰድ ከገባ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ከባድ አይደለም፡፡

ሁኔታው መልሶ ወደ ጦርነት ሊከት ይችላል በሚል የትግራይ ክልልን ብቻ ሳይሆን መላው አገሪቱን ሥጋት ላይ ጥሏል በሚባልበት በዚህ ወቅት ግን፣ ጉዳዩን በማሸማገልም ሆነ በማረጋጋት ዋናውን ሚና ሊወጣ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው የፌደራል መንግሥት ትንፍሽ ሲል አለመታየቱ የበለጠ ችግር እንዳይወሳሰብ እየተፈራ ነው፡፡

አሜሪካን የመሳሰሉ አገሮች ችግሩን ለማርገብ ሲንቀሳቀሱ ታይተዋል፡፡  በተለይ አሜሪካ በቅርቡ ልዩ የአፍሪካ ቀንድ ልዑኳ ማይክ ሀመር ትግራይ መሄዳቸው ይታወሳል፡፡