አበበ ፍቅር

September 25, 2024

ምን እየሰሩ ነው?

ትውልድን ከአደንዛዥ ዕፅ ሱስ ለመታደግ በሚል ከሦስት ዓመት በፊት  የተቋቋመው በጎ አድራጎት ድርጅት ‹‹ላግዛት›› ይባላል፡፡ ፕሮጀክቱ መነሻውን የሐረሪ ክልል በማድረግ  የሚተገበር ሲሆን፣ ትኩረቱንም በክልሉ በሚገኙ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች አድርጓል፡፡ በቀጣይም በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች በሱስ የሚጠቁ ወጣቶችንና በሱስ የተጠቁ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ከሱስ የራቁ በማድረግ  አምራች ማኅበረሰብን ለመፍጠር አልሟል፡፡ ላግዛት እያከናወነ ስላለው ተግባር  የድርጅቱን የፕሮጀክት አማካሪ አንዱዓለም አባተን (/አበበ ፍቅር አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ላግዛት በጎ አድራጎት ድርጅት መቼ ተመሠረተ? ዓላማውስ ምንድን ነው? 

አንዱዓለም (/)፡- ላግዛት በ2014 ዓ.ም. የተቋቋመ አገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን፣ ድርጅቱ ከተነሳባቸው ዓላማዎች መካከል አንዱና ዋነኛው በወጣቶች ላይ የሚታየው አደንዛዥ ዕፅ ሱስን ለመከላከል ነው፡፡ ትውልድን ከአደንዛዥ ዕፅ እንከላከል የሚል ዓላማን አንግቦ ተነስቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ፕሮጀክቱ በዋናነት የት አካባቢ ነው የሚተገበረው?

አንዱዓለም (ዶ/ር)፡- ለመጀመሪያ ጊዜ በሐረሪ ክልል የሚጀመር ሲሆን፣ በክልሉ በሚገኙ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ መምህራንና የተማሪ ወላጆች እንዲሁም ከትምህርት ቤቶች ውጪ የሚገኘውን የማኅበረሰብ ክፍል ስለ አደንዛዥ ዕፅ ሱስ አስከፊነት ግንዛቤ ይፈጥራል፡፡ በክልሉ የሚገኙ በሱስ የተጠቁ ወገኖች የሚታከሙበትን ክሊኒክ እንዲሁም የሱስ ማገገሚያ ማዕከላትን ለማቋቋም ይሠራል፡፡

ሪፖርተር፡- በሱስ የተጠቁ ሰዎችን በምን መልኩ ነው የግንዛቤ ማስጨበጫ  የምትሰጡት?

አንዱዓለም (ዶ/ር)፡- ወጣቶችን  ከአደንዛዥ ዕፅ ሱስ ለማስወጣት የተለያዩ መንገዶችን እንከተላለን፡፡ አንዱ ስለ አደንዛዥ ዕፅ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራን የምንሠራ ሲሆን በዋናነት ከ7ኛ ክፍል እስከ 12ኛ ክፍል ባሉ ተማሪዎች ላይ ትኩረት እናደርጋለን፡፡ ከትምህርት ቤት ውጭ ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችም በወጣቶች አደረጃጀትና በሌሎች ዘዴዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአደንዛዥ ዕፅ ሱስ ጋር በተያያዘ በሚከሰተው የአዕምሮ ሕመም ለሚጋለጡ ሰዎች መታከሚያና ማገገሚያ ክሊኒክ ማቋቋም ነው፡፡ ምንም እንኳን በክልሉ የአዕምሮ ሕሙማን መታከሚያ ተቋም ቢኖርም ላግዛት ድርጅት ትኩረት የሚያደርግባቸው ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ ለሚከሰቱ የአዕምሮ ሕሙማን ነው፡፡ ሱስ ራሱን የቻለ በሽታ ሲሆን ሕክምና በአግባቡ ካገኘ የሚድን በመሆኑ ራሱን የቻለ ክሊኒክ እንዲኖር እንፈልጋለን፡፡ ለረጅም ጊዜ በሱስ የተጠቁ ወጣቶች ተኝተው የሚታከሙበት ሥነ ልቦናዊና ማኅበራዊ ክትትል አግኝተው የሚታከሙ፣ አገግመው የተሻሉና አምራች ዜጎች ሆነው የሚወጡበት ይሆናል፡፡ ይሠራል ተብሎ የታሰበው የሱስ ማገገሚያ ማዕከል ለምሥራቅ ኢትዮጵያ አገልግሎት መስጠት የሚችል እንዲሆን ተደርጎ የሚሠራ ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ የአደንዛዥ ዕፅ አስከፊነትን ግንዛቤ በማስጨበጥ ችግሩን ለመከላከል የሕክምና ጣቢያ በመክፈት በሱስ የተጠቁ ሰዎችን በማከም ላይ ያተኮረ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከክልሉ መንግሥታዊ አካላት ያላችሁ ግንኙነት እንዴት ነው?

አናዱዓለም (ዶ/ር)፡- ፕሮጀክቱ ከሐረሪ ክልል መንግሥትና ከሴቶችና ሕፃናት ቢሮ፣ ከትምህርት ቢሮና ከፖሊስ ኮሚሽን ጋር በጋራ ለመሥራት ተፈራርመናል፡፡ በሌላ በኩል የድርጅቱ ተልዕኮ ማኅበረሰቡን በማስተባበር አደንዛዥ ዕፅ በግለሰቦችና በቤተሰብ እንዲሁም በአገር ላይ የሚያደርሰውን አስከፊ ውጤት መቀነስና ማጥፋት በመሆኑ የክልሉ መንግሥትም ሆነ ሌሎች አካላት ለፕሮጀክቱ ትግበራ የሚያስፈልገውን ድጋፍ እንደሚያደርጉልን ትልቅ ተስፋ አለን፡፡

ሪፖርተር፡- ለአደንዛዥ ዕፅ ሱስ መስፋፋት ተጠያቂው ማን ነው ይላሉ?  

አንዱዓለም (ዶ/ር)፡- የአደንዛዥ ዕፅ ሱስ በርካታ አምራች ወጣቶችን ከዓላማቸው ከማጨናገፍ ባሻገር፣ ሰብዕናቸውን በማበላሸትና የጤና እክል በመሆን ለአገር ሥጋት ሆኗል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁላችንም ተጠያቂ ነን፡፡ ትውልዱ ተበላሸ፣ በሱስ ተጠምዶ  አምራች ዜጋ ጠፋ ከማለት ወጥተን፣ ቆም ብለን በማሰብ ተጠያቂው ማነው ብለን ሳንጠይቅ ትውልዱ እንዲሻገር ሁላችንም ምን አደረግን ምንስ ሠራን የሚል ጥያቄን ራስን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ፕሮጀክቱ ሲነሳ ትውልዱን ከሱስ ለማዳን የበኩሉን ድርሻ ምን ላድርግ የሚል ሐሳብን ፀንሶ ሲሆን በተመሳሳይ ሁሉም ሰው ሊያስብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ፕሮጀክቱ መነሻውን ሐረር ከተማ ላይ ያደረገበት ምክንያት ይኖረው ይሆን?

አንዱዓለም (ዶ/ር)፡- ላግዛት አደንዛዥ ዕፅና ሱስን ለመከላከል ፕሮጀክቱ የጀመረው  ሐረር ላይ ነው፡፡ ሐረር ስሟ የገነነ የብዙ ጥንታዊ ቅርስና የመቻቻል ከተማ ስትሆን  ከሐረር በመነሳት ወደ ሌሎች የአገሪቱ ከተሞች የሚሄድ ይሆናል፡፡ በርካታ ወጣቶች በሱስ ሲያዙ የጤና ችግር ስለሚገጥማቸው የማኅበራዊ ችግር ያሰቡበት ለመድረስ የሚደናቀፉበት ስለሚሆን ነው፡፡ የትውልድ ሰብዕና ላይ ባልተሠራ ቁጥር ቆይተው አቶሚክ ቦንብ ነው የሚሆኑት፡፡ ችግሩ ከቤተሰባዊና ከማኅበራዊ ቀውስ አልፎ አገራዊ ቀውስ ስለሚያመጣ ሁላችንም ደግሞ ወጣቶችን የመታደግ ኃላፊነት ስላለብን፣ በሐረር ከተማ ከሱስ ጋር የሚኖሩ ወጣቶች ከችግር ተላቀው አምራችና የሐረርን ታሪክ የሚያስቀጥሉ፣ ለሌላው መፍትሔ እንጂ ችግር የማይሆኑ ትውልድን  ለማፍራት ሥራው በሐረር ላይ ተጀምሯል፡፡ ሐረር ላይ የተጀመረው እንቅስቃሴ በሁሉም አካባቢ የሚቀጣጠል ሲሆን፣ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር ወጣቶችና ሕፃናት ጎልማሶችና በአጠቃላይ በሁሉም ኅብረተሰብ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ቢያንስ በጥናት እንደተመለከተው ለአምስት ተከታታይ ዓመታት የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ከተሠራ በኋላ ቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ደግሞ ወደ ተግባር የሚቀየርበት ነው፡፡ ቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ደግሞ ውጤቱ የሚታይበት ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ሁሉንም አካባቢ በአንድ ጊዜ ማስጀመር ከኢኮኖሚ አንፃር ስለማይቻልና ያሉ ክፍተቶችን ለማየት የሚያግዝ በመሆኑ በቀጣይ በመላው ኢትዮጵያ  እንዲደርስ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ፕሮጀክቱ ከሌሎች በጎ አድራጎት ድርጅቶች ለየት የሚያደርገው ጉዳይ ይኖራል?

አንዱዓለም (ዶ/ር)፡- ስለ አደንዛዥ ዕፅ ከዚህ በፊት ብዙ ነገር ተብሏል፡፡ የዚህ ፕሮጀክት ለየት ከሚያደርገው አንደኛውና ዋነኛው ነገር ሰዎች ለምን ወደ ሱስ ይገባሉ? ከገቡ በኋላስ እንዴት ይወጣሉ? የሚሉ ጉዳዮችን ጠንከር አድርጎ የሚዳስስ ሞጁል የማሳተም ዕቅድ በመያዙ ነው፡፡ ሞጁሉ በአብዛኛው ትኩረቱን የሚያደርገው ደግሞ ተማሪዎች ላይ ነው፡፡ ችግሩ ሥር ከመስደዱ የተነሳ ሱስ ወደ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወርዷል፡፡ ፕሮጀክቱን ለመቅረፅ ወደ ሐረር በሄድንበት ወቅት ብዙ ጊዜ እያጨሱ የነበሩት ሕፃናት ናቸው፡፡ እየቃሙና እየጠጡ የነበሩት ሕፃናት ነበሩ፡፡ ብዙ ነገሮችን ሲያደርጉ የታዩት ሕፃናት ነበሩ፡፡ ለምን? ስንል አንዱና ዋነኛው ነገር የዕውቀት ማነስ ነበር፡፡ ይህንን የዕውቀት ወይም የግንዛቤ እጥረት ደግሞ እንዴት ነው የምናጠበው ስንል ባህልና ወጉን የማይለቅ ኢትዮጵያዊ ይዘት ያለው ሞጁል በማሳተምና በማስተማር ነው፡፡ በዚህ የማስተማሪያ ሞጁል ላይ በጉዳዩ ዙሪያ ዕውቀቱ ያላቸው በርካታ ባለሙያዎች ይሳተፉበታል፡፡