በእሥራኤል በምትገኘው የሃይፋ ከተማ የደረሰ ጥቃት

ዓለም

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

September 25, 2024

እ.ኤ.አ. ሴፕቴምበር 23 ቀን 2024 በዕለተ ሰኞ እስራኤል የሊባኖስ ዋና ከተማ በሆነችው በቤይሩትና ሌሎች አካባቢዎች መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃት በመፈጸም፣ ከ600 በላይ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተፈራው የሂዝቦላህና የእስራኤል ጦር ወደ ለየለት ጦርነት መግባትን ከአፋፍ ያደረሰችው ይመስላል፡፡ ሂዝቦላህ በበኩሉ ወደ ሰሜን እስራኤል የሚያስወነጭፈውን የሮኬትና የሚሳይል ናዳ ቀጥሎ ውሏል፡፡ ይህ ጥቃት ማክሰኞም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሊሞቱ እንደሚችሉ ተሠግቷል፡፡

አስፈሪው የእስራኤል ጥቃትና የሂዝቦላህ የመገዳደር አቅም ማጣት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በሮኬት ጥቃት የደረሰ ውድመት

የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር በሰኞው የእስራኤል ጥቃት ብቻ 600 ሊባኖሳውያን እንደተገደሉ ሲገልጽ፣ የእስራኤል መከላከያ በበኩሉ ጥቃት የደረሰው የሐማስ ተወንጫፊ ሚሳይሎች ተጠምደው ባሉባቸው የጦር ይዞታዎች ላይ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ጥቃቱን ተከትሎ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ውጊያ የሚደረገው ከሊባኖሳውያን ሳይሆን ከሂዝቦላህ ታጣቂዎች ጋር በመሆኑ፣ ሕዝቡ ከጥቃት ዒላማ ቦታዎች ራሱን በአስቸኳይ እንዲያሸሽ ጠይቀዋል፡፡

የእስራኤል መከላከያም በሰኞ ጥቃት ብቻ ከ800 በላይ የሂዝቦላህ ዒላማዎች ጥቃት እንደደረሰባቸው ተናግሯል፡፡ ከጥቃቱ አስቀድሞም በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የስልክ ግንኙነቶች ስለመፃዒው ጥቃት፣ እንዲሁም ሕዝቡ ራሱን ለማዳን መውሰድ ስለሚገባው ጥንቃቄና ዕርምጃ ገለጻ መደረጉን አሳውቋል፡፡

ካለፈው ሳምንት መግቢያ አንስቶ የጀመረው የሁለቱ ኃይሎች መካረር ወደ ጦርነት ትንቅንቅ እየተሸጋገረ ያለ ይመስላል፡፡ ከእስራኤል ጦር ቀጣይ ዕርምጃ እንደሚኖር በማያወላውል ሁኔታ ነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በመከላከያ ሚኒስትራቸውና በአስቸኳይ ጊዜ ካቢኔያቸው አባላት ታጅበው ሲናገሩ የተደመጡት፡፡

አንዳንድ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ከወዲሁ የየአገሮቻቸው አየር መንገዶች ወደ ቤይሩት የሚያደርጉትን በረራዎች ለጊዜው ገታ እንዲያደርጉ ያሳሰቡ ሲሆን፣ ዮርዳኖስ ይህንን ትዕዛዝ በማስተላለፍ የመጀመሪያዋ መሆኗን ዘገባዎች ወጥተዋል፡፡

የአሁኑን መጠነ ሰፊ ጥቃት ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ ኃላፊዎች እንዳሳሰቡት ከሆነ፣ ሁኔታው ለቀጣናው እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ በአፋጣኝ መገታት አለበት፡፡ ኔታንያሁም በበኩላቸው፣ ‹‹ከፊታችን የተወሳሰቡ ቀናት ይጠብቁናል፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

‹‹ለሊባኖስ ሕዝብ መልዕክት አለኝ፡፡ የእስራኤል ጦርነት ከእናንተ ጋር አይደለም፡፡ ጦርነታችን ከሂዝቦላህ ጋር ነው፡፡ ለረዥም ጊዜ ሂዝቦላህ እንደ ሰብዓዊ ጋሻ ሲገለገልባችሁ ቆይቷል፤›› ብለዋል፡፡

ጥቃቱን ተከትሎም በሺዎች የሚቆጠሩ ሊባኖሳውያንን ከደቡብ ቤይሩት ቀዬአቸው በገፍ ሲሰደዱ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ታይተዋል፡፡

እስራኤል በአንድ ቀን ይህንን ያህል ቁጥር ያለው የአየር ጥቃት መፈጸሟን፣ በጋዛ ስታደርገው በቆየችው ዓመት የተቃረበው ክስተት ዘመቻ ወቅት ያልተስተዋለ ሲሉ ይገልጹታል የጦር ተንታኞች፡፡

የእስራኤል ጥቃት ዒላማ ካደረገችው የሂዝቦላህ ከፍተኛ የጦር አዛዦች መካከል ዓሊ ካራኪ አንዱ ሲሆኑ፣ ሂዝቦላህ ግን ‹‹ዓሊ ካራኪ በደህና ናቸው፤›› ማለቱ ተሰምቷል፡፡

የእስራኤል ጥቃት እ.ኤ.አ. በ2006 በሊባኖስና በእስራኤል ኃይሎች መካከል ተደርጎ የነበረውን ጦርነት የሚያስታውስ መሆኑን ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡

በጥቃቱ 490 ሰዎች እንደተገደሉ (ለኅትመት እስከገባንበት ድረስ) እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች ያመላክታሉ፡፡ ከተገደሉት ውስጥ ከ90 በላይ ሴቶችና ሕፃናት ሲሆኑ፣ ከ1,645 በላይ መቁሰላቸው ተዘግቧል፡፡ ይህ የጉዳት ቁጥር ከዚህም ሊልቅ እንደሚችል ሲገመት፣ እስራኤል በቀጣይ ታደርገዋለች ተብሎ በሚፈራው ጥቃት ከፍተኛ ዕልቂት ሊከሰት እንደሚችል ተንታኞች ይናገራሉ፡፡

የእስራኤል መከላከያ እንዳለው 1,600 ያህል የሂዝቦላህ ዒላማዎች ተመትተዋል፡፡ በ2006 በእስራኤልና በሂዝቦላህ በተደረገው የ33 ቀናት ጦርነት የሟቾች ቁጥር 1,200 ነበር፡፡

የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ መካረሩን የገለጹት፣ ‹‹እጅግ አሳሳቢ›› ሲሉ ነው፡፡ ዓመት ሊሞላው አንድ ወር የቀረው የእስራኤልና የሐማስ ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ቢሆንም፣ እስራኤል የጥቃት ትኩረቷን ከሐማስ ወደ ሊባኖስ የታጣቂዎች ቡድን ሂዝቦላህ ማድረጓን በይፋ አሳውቃለች፡፡

እስራኤል ባለፈው ዓርብ በደቡብ ሊባኖስ በወሰደችው የአየር ጥቃት የሂዝቦላህ ጦር መሪ መገደሉና በጦር ሠፈሩም ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት መድረሱን ተከትሎ፣ ሂዝቦላህ 150 ሮኬቶች ሃይፋ ወደ ተሰኘች የእስራኤል ግዛት መተኮሱን የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር አረጋግጧል፡፡

ይህም ተጨማሪ የዓለም የደኅንነትና የፀጥታ ሥጋት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በጥቃቱ ማግሥት የተመድ ዋና ጸሐፊ ጉቴሬስ ሁለቱም ኃይሎች ግጭቱን ከሚያባብሱ ሁኔታዎችና ድርጊቶች መታቀብ እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ግጭቱ ተባብሶ ከቀጠለ ወይም በአስቸኳይ ካልተገታ ክልላዊ ግጭት ወደ መሆን ሊቀጣጠል እንደሚችል ጉቴሬስ ሥጋታቸውን በአጽንኦት ለሲኤንኤን የፖለቲካ ተንታኞች ኤዲተር ፋሬድ ዘከሪያ አስረድተዋል፡፡

እጅግ አውዳሚና ወደ ለየለት ጦርነት ሊያመራ ይችላል በተባለለት የዓርቡ የእስራኤል ጥቃት 45 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከልም የሂዝቦላህ የጦር መሪ ኢብራሂም አኪልና 95 ታጣቂዎች ይገኙበታል፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት የአሜሪካ መንግሥት በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በኩል ኢብራሂም አኪልን አድራሻ ለጠቆመ ሰባት ሚሊዮን ብር ዶላር ወሮታ እንደሚከፍል አሳውቆ ነበር፡፡

እስራኤል የሂዝቦላህን ሁነኛ የጦር አበጋዝ ስትገድል ኢብራሂም አኪል ሁለተኛው ነው፡፡ ባለፈው ሐምሌ ወር ባደረገችው ጥቃት የሂዝቦላህ የጦር መሪ የነበረውን ፉአድ ሽኩር መግደሏ ይታወሳል፡፡  

እስራኤል ከሁለት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሁለት ከፍተኛ የሂዝቦላህ የጦር አመራሮችን የገደለችው በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ውስጥ በመኖሪያ መንደር ላይ በተደረጉ ጥቃቶች ነው፡፡

ኢብራሂም አኪል በተገደሉበት ዕለት የወጣ የአልጄዚራ እንግሊዝኛ ቋንቋ ዘገባ እንደሚለው ከሆነ፣ ሂዝቦላህ የጦሩ ምክትል አዛዥ መገደሉ የእግር እሳት ሆኖበታል፡፡ በእስራኤል ዒላማ ውስጥ የገባው የሂዝቦላው ኮማንደር ኢብራሂም አኪልን አሜሪካ ታድንና ታሳድነው የነበረችው እ.ኤ.አ. በ1980 ቤይሩት ውስጥ በመቶ የሚቆጠሩ ዜጎቿን ሰለባ ያደረገ ጥቃት በሂዝቦላህ ከተሰነዘረ ጀምሮ ነበር፡፡

በሂዝቦላህና በእስራኤል መካከል በተወሰነ ደረጃ ላለፉት በርካታ ወራት ጥቃቶችና አፀፋ ጥቃቶች ሲደረጉ ቢቆዩም፣ የመንግሥታቱን ድርጅትና አሜሪካን ጨምሮ የኃያላን አገሮችን ትኩረት የሳበው ካለፈው ሳምንት የእስራኤል መጠነ ሰፊ ጥቃቶችና የሂዝቦላህ የመልስ ምቶች ምክንያት ነው፡፡ የኦክቶበር ሰባቱን የሐማስ ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ በጀመረችው መጠነ ሰፊ ዘመቻ ከ41,000 በላይ ንፁኃን ፍልስጤማውያን ሲገደሉ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ መቁሰላቸው ይታወቃል፡፡ ሐማስ በእስራኤል ላይ ለሚያደርጋቸው ጥቃቶች እንደ ምክንያት የሚያነሳው ይህንኑ የፍልስጤማውያንን ፍጅት ነው፡፡ ሂዝቦላህ እስራኤል በፍልስጤም የምታደርገውን የጦር ዘመቻና ግድያ እስካላቆመች ድረስ የሮኬትና የሚሳይል ጥቃቶቹን እንደማያቆም ሲዝት ቆይቷል፡፡

ወደ ለየለት ጦርነት ከመግባት እንዲታቀቡ ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ተማፅኖ ቢደርሳቸውም፣ እስራኤልም ሆነች ሂዝቦላህ ባለፈው ሳምንት የጀመሩትን ድንበር ዘለል ጥቃቶች አጠንክረው እንደሚቀጥሉበት ዝተዋል፡፡

የእስራኤል የጥቃት አቅጣጫ ትኩረት ዒላማ ያደረገው፣ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የእስራኤል ስደተኞችን እስራኤል በሰሜን ሊባኖስ በምትዋሰንባቸው የድንበር አካባቢዎች ለማስፈር መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ለዚህም የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ አካባቢውን ወደ ነበረበት የደኅንነት ሁኔታ ለመመለስና ተፈናቅለው የነበሩ እስራኤላውያንን ወደ ነበሩበት ቀዬአቸው መልሶ ለማስፈር፣ እስራኤል አስፈላጊውን ሁሉ ዕርምጃ ከመውሰድ እንደማትቦዝን ተናግረዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

‹‹እንኳን ሊያስበው ሊልመው የማይችለውን ተከታታይ ጥቃቶች በሂዝቦላህ ላይ አድርሰናል፤›› ሲሉ ኔታንያሁ ቢናገሩም፣ ቢቢሲ አነጋገርኳቸው ያላቸው የሂዝቦላህ ምክትል ኃላፊ ናኢም ቃሴም፣ ‹‹ዛቻዎች አያቆሙንም፣ የትኛውንም የጦር ክስተት ለመጋፈጥ ዝግጁ ነን፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ወደ አዲስ ምዕራፍ አምርተናል፣ በግልጽ ሒሳብ ወደ ማወራረድ እንገባለን፤›› ሲሉም መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በእስራኤልና በሂዝቦላህ መካከል እየተካረረ የመጣው ግጭት ወደ ለየለት ቀጣናዊ ጦርነት ሊያመራ እንደሚችል የፖለቲካና የወታደራዊ ተንታኞች በማስገንዘብ ላይ ቢሆኑም፣ ያለፉት ቀናት ክስተቶች ይህ ሥጋት ዕውን ሊሆን እንደሚችል ያመላክቱ እንደነበርና ሁኔታውም ተባብሶ መቀጠሉን፣ የኖትርዳም ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የሰላም ጥናቶች ፕሮፌሰር አሸር ኮፍማን ይናገራሉ፡፡

ያለፉት ጥቂት ቀናት ሂዝቦላህ ወደ ለየለት ጦርነት ይገባ ዘንድ በእስራኤል ‹እየተገደደ› የነበረበት፣ የዚህ ውጤት ግን በሁሉም ላይ አውዳሚ እንደሚሆን ኮፍማን ያስረዳሉ፡፡

በመጀመሪያ እስራኤል ፔጀርና ዋኪ ቶኪ በመባል በሚታወቁ የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ መገልገያዎች አማካይነት በሂዝቦላህ የሰው ከሰው የግንኙነት መረብ ላይ ጥቃት አደረሰች፡፡ ይህንን ተከትሎ ደግሞ ቁልፍ የሂዝቦላህ መሪ በሆነው ኢብራሂም አኪል ላይ ግድያ ተፈጸመ ይላሉ ኮፍማን፣ ‹‹ዘ ኮንቨርሴሽን›› በተሰኘ የበይነ መረብ ዜና አውታር ላይ በታተመ ጽሑፋቸው፡፡

ኦክቶበር 7 ቀን 2023 ሐማስ እስራኤል ውስጥ ዘልቆ በመግባት ባደረሰው መብረቃዊ ጥቃት 1,200 ሰዎች ሲገደሉ፣ ከ250 በላይ የሚሆኑ ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ቀን በቀን ሲባል በሚችል ሁኔታ ሂዝቦላህ በእስራኤል ላይ ሮኬቶች አስወንጭፏል፡፡ በዚህም ከሰሜናዊ እስራኤል 60,000 እስራኤላውያን ተፈናቅለው እንደነበር መዘገቡ አይዘነጋም፡፡

 ‹‹እንደ አንድ ሊባኖስንና እስራኤልን እንደሚያጠና ምሁር የዚህ አንበርክኮ የማስገበር ጦርነት (War of Attrition) ከኦክቶበር 8 ቀን 2023 ጀምሮ ስከታተል ቆይቻለሁ፡፡ በዚያች ዕለት የሐማስ ታይቶ በማይታወቅ መጠን በእስራኤል ላይ ጥቃት ፈጸመ፡፡ የእስራኤል አፀፋ የጋዛ ሰርጥን በቦምብ መደብደብ ሆነ፡፡ ከዚያም ሂዝቦላህ ወደ ሰሜናዊ እስራኤል ሮኬቶች ማስወንጨፍ ጀመረ፡፡ በዚህም ለሐማስ ያለውን ‹አለኝታነት› ገለጸ፤›› ይላሉ ፕሮፌሰሩ፡፡

ያም ሆኖ ይላሉ ሆፍማን፣ ‹‹እስራኤልም ሆነች ሂዝቦላህ ወይም የሂዝቦላህ ስፖንሰር ኢራን ወደ ለየለት ጦርነት ለመግባት ያሳዩት ምንም ዓይነት ፍላጎት አልነበረም፡፡ ሁሉም ወገኖች እንዲህ ያለውን ግጭት አውዳሚነት ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ጦሱንም በደንብ አድርገው የሚረዱት ጉዳይ ነው፡፡ እስራኤል ልክ ጋዛ ላይ እንዳደረገችው የቤይሩትንና ሌሎች የሊባኖስ አካባቢዎችን ድምጥማጥ ማጥፋት የሚያስችል የወታደራዊ ኃይል ብቃት አላት፡፡ ያም ሆኖ እጅግ በተዳከመ ሁኔታ ውስጥ ቢሆን እንኳን ሂዝቦላህ በሺዎች የሚቆጠሩ ሚሳይሎችን በመተኮስ እንደ በመካከለኛው ቴል አቪቭ ያለን አውሮፕላን ማረፊያ፣ የውኃ አቅርቦት፣ መሠረተ ልማት፣ መስመሮችንና ኤሌክትሪክ ማከፋፈያዎችን ብሎም የባህር ላይ ነዳጅ ማውጫዎችን በመሳሰሉ የእስራኤል ስትራቴጂካዊ ሥፍራዎች ጥቃት ሊያደርስ ብቃቱ ይኖረዋል፤›› ብለዋል፡፡

ፕሮፌሰር ሆፍ ማን እንደሚሉት ከሆነ፣ ያለፉት ቀናት ክስተቶች ከላይ የተዘረዘሩ ሥጋቶችን ዕውን ለማድረግ የሚያቃርቡ ናቸው፡፡ ይህንንም ‹አዲሱ አደገኛ ምዕራፍ›› ይሉታል፡፡

ይህ ሁሉ የሚያሳየው የግጭት ስበቱ ከደቡብ ወደ ሰሜን መሄዱን ነው፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከአምስት ቀናት በፊት ባወጡት መግለጫ፣ ሁለቱ ወገኖች ግጭት ከሚያባብሱ ሁኔታዎችና ድርጊቶች አጥብቀው እንዲቆጠቡ ጥሪ ማስተላለፋቸው ይታወሳል፡፡ ከጥሪው በኋላ በተከታታይ ቀናት የተስተዋለው እውነታ ግን ተፋላሚ ወገኖች የብሊንከንን ተማፅኖ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለውታል፡፡ ብሊንከን ጥሪውን ያስተላለፉት በቤይሩት የተከሰቱትን የፔጀርና የዎኪ ቶኪ ፍንዳታ ጥቃቶች ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የተካረረ ሁኔታ ለማስቆም ባለመ የዲፕሎማሲ ጥረታቸው ወደ ካይሮ ባቀኑበት ጊዜ ነበር፡፡

እንደ ብሊንከን ከሆነ በሁለቱ ወገኖች የሚደረግ ማንኛውም የግጭት መባባስ መካከለኛው ምሥራቅን የጦር ቀጣና የማድረግ የሥጋት ሁኔታ የሚፈጥር ነው፡፡

የሂዝቦላ ዋና ጸሐፊ ሐሳን ናስራላህ እንደሚሉት ሰሞነኛው የእስራኤል ጥቃቶች፣ ‹‹ሁሉንም ቀይ መስመሮች የጣሱ›› በመሆናቸው እስራኤል ውሎ አድሮ የበቀል ዕርምጃ አይቀርላትም፡፡ እስራኤል በበኩሏ ካለፉት ቀናት ጀምሮ እያደረሰችው ባለችው ጥቃት ሂዝቦላህ በበቃኝ እጅ ይሰጥ ዘንድ ጥቃቷን አጠናክራ እንደምትገፋበት ከበቂ በላይ ማሳያዎች አሉ፡፡ ኮፍማን አክለው በአሁኑ ወቅት ናስራላህ ሂዝቦላህን ከእስራኤል ጦር ጋር ወደ ለየለት ጦርነት ይዞ የመግባት ፍላጎቱ እንደሌላቸው፣ የሒሳብ ማወራረጃው ማስጀመሪያ ቀን በግልጽ ባለመናገር ተናግረውታል፡፡

በኢራን ስትራቴጂካዊ ጥቅም ሳቢያ ይሽከረከራል የሚባለው የኢራን፣ የሐማስና የሂዝቦላህ ጥምረት የወቅቱን የእስራኤል ትንኮሳዎችን በትዕግሥት ተቋቁሞ የለየለት ጦርነት እንዳይኖር አስተዋጽኦ ያደርጋል? ወይስ አንዳንድ ተንታኞች እንደሚሉት ሂዝቦላህ ከእስራኤል ጋር ጦርነት ለመግጠም ይገደዳል?

ይህ አደገኛ የተባለ ግጭት ያለ ሃይ ባይ በቀጠለበት ሁኔታ ተመድ ጠቅላላ ጉባዔውን ጀምሯል፡፡ ጉዳዩ ከዩክሬንና ከሩሲያ ጦርነት ያልተናነሰ ወይም በበለጠ ትኩረት ተሰጥቶ ለውይይትና ለውሳኔ እንደሚቀርብ ይጠበቃል፡፡