በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ድጋፍ ሲደረግላቸው ከነበሩ ቤተሰቦች አንዱ

ማኅበራዊ ኮልፌዎች ከወርልድ ቪዥን ምን አተረፉ?

አበበ ፍቅር

ቀን: September 25, 2024

ሕፃናት በሥነ ምግባር ተኮትኩተው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ የወላጅ ሚና የማይተካ ሆኖ ይገኛል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን የመንከባከብ የማስተማርና ሌሎች መሠረታዊ ፍላጎታቸውን የማሟላት ትልቅ ኃላፊነት ቢኖርባቸውም፣ ልጆች በሥነ ምግባር ብቁ ሆነው ተምረው ለአገርና ለወገን ጠቃሚ እንዲሆኑ ደግሞ የማኅበረሰብ ሚና ቀላል አይደለም፡፡ ምንም እንኳን አሁን አሁን በብዛት የቀረ ቢሆንም ቀደም ሲል ወላጆች የጎረቤት ልጆችን ከልጆቻቸው ጋር እኩል ሲያጠፉ ተቆጥተውና ቆንጥጠው ሲርባቸው አብልተው መክረውና ገስፀው ነበር የሚያሳድጉት፡፡

ኮልፌዎች ከወርልድ ቪዥን ምን አተረፉ? | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ወ/ሮ ራሔል ባሻ በኮልፌ አካባቢ ልማት የሕፃናት
እንክብካቤና ተሳትፎ ኦፊሰር

ዛሬ ላይ ይህ ነገር በስፋት አይታይም፡፡ በተለይ በከተሞች አካባቢ ጎረቤት ሆነው እርስ በርስ የማይተዋወቁ ሰዎች በርካታ ናቸው፡፡ በሕፃናት ላይ የጉልበት ብዝበዛም ሆነ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃት ሲደርስባቸው አይተው የሚያልፉ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡  

በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ችግሩ ጎልቶ ይታያል፡፡ ሕፃናትን ለማስተማርና መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት በእጅጉ አስቸጋሪ እየሆነባቸው ስለመምጣቱ ወላጆች ይናገራሉ፡፡

የእናቶችና ሕፃናትን እንዲሁም የአረጋውያንን ችግሮች ተመልክተው ማኅበራዊና ሰብዓዊ ግዴታቸውን ለመወጣት በየአካባቢው የሚሰማሩ አገር በቀልና ከውጭ አገር የሚመጡ በጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ቀላል አይደለም፡፡

ከእነዚህ በጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ አንዱ ነው፡፡ ድርጅቱ ከገጠር እስከ ከተማ በሚያደርጋቸው ሰብዓዊ ድጋፎች በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚታወቅ ነው፡፡ ድርጅቱ በአዲስ አበባ ከተማ በኮልፌ ክፍለ ከተማ ላለፉት 17 ዓመታት በተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ሲሠራ ቆይቶ የሥራ ጊዜውን አጠናቋል፡፡

በቆይታውም በተለይ ሕፃናት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸው እንዳይሸረሸር ከማኅበረሰቡ ጋር በመሆን ዘብ በመቆም፣ በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ለሆኑ ወላጆች የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩና ፍላጎታቸውን እንዲያሟሉ ሲያደርግ መቆየቱን መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. በነበረው የማጠቃለያ ፕሮግራም ላይ ወላጆች ተገኝተው መስክረዋል፡፡

ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በተለይ በክፍለ ከተማው ባሉ አምስት ወረዳዎች ላይ ለሁለት አሠርታት ግድም ሕፃናት ላይ ትኩረት በማድረግ ሲሠራ መቆየቱን የተነገረ ሲሆን በዚህም በርካታ ሰዎችን በንፁህ ውኃና በጤና፣ በትምህርትና በንፅህና አጠባበቅ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ተጠቃሚ ሲያደርግ መቆየቱ ተገልጿል፡፡ ከእነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል 96 ሺሕ የሚደርሱ ሕፃናት በ‹‹ኮልፌ አካባቢ ልማት›› በተሰኘ ፕሮግራም ታቅፈው የተለያዩ አገልግሎቶች ሲያገኙ ቆይተዋል፡፡

ወ/ሮ ራሔል ባሻ በ‹‹ኮልፌ አካባቢ ልማት›› የሕፃናት እንክብካቤ ተሳትፎ ኦፊሰር ናቸው፡፡ ወርልድ ቪዥን ላለፉት 17 ዓመታት በኮልፌ ክፍለ ከተማ በተመረጡ አምስት ወረዳዎች በወረዳ 1፣ 9፣ 10፣ 11 እና ወረዳ 12 ላይ በተለይ የሕፃናት ጥቃት መከላከል ላይ ትኩረቱን አድርጎ ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ብዙ ሕፃናት ሴቶች መደፈርን ጨምሮ ሌሎች ጥቃቶች ሲደርስባቸውም ሆነ ጥቃቱ ከደረሰባቸው በኋላ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት አይደረግላቸውም ያሉት ወ/ሮ ራሔል፣ ችግሩን ወደ ማኅበረሰቡ ጠለቅ ብሎ በመመርመር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ለማኅበረሰቡ በመስጠት ለችግሩ መፍትሔ ሰጪ እንዲሆን በማድረግ በርካታ ሕፃናት ከሚደርስባቸው ጥቃት እንዲጠበቁ ሆነዋል፡፡

ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላም ቢሆን ጥቃት አድራሾች ተገቢውን ቅጣት በሕግ እንዲያገኙ ለሕግ አሳልፎ ከመስጠት ባሻገር ተጎጂ ሕፃናት ለደረሰባቸው አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ እንዲያገግሙ ሲሠሩ መቆየታቸውን  ወ/ሮ ራሔል ተናግረዋል፡፡ ሕፃናት ጥቃት ሳይደርስባቸው በፊት ቀድሞ ለመከላከል እንዲችሉ ሴቶችን እናቶችን ጨምሮ በማሠልጠን እንዲሁም በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ የከተማ ግብርና ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ ሲሠሩ መቆየታቸውንም አስረድተዋል፡፡

‹‹ወላጆች በልጆቻቸው ላይ እንዴት በጎ ተፅዕኖን ያሳድራሉ የሚለውን እናስተምራለን፤›› ያሉት ወ/ሮ ራሔል፣ ትምህርት ቤት ውስጥም ቢሆን መምህራን በልጆች ላይ ተገቢ ያልሆነ ቅጣት እንዳይቀጡ እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች በሕፃናት አስተዳደግ ላይ ለማኅበረሰቡ ምክር እንዲሰጡ ሲሠሩ መቆየታቸውን አክለዋል፡፡

በኮልፌ አካባቢ የልማት ፕሮግራም ተጠቃሚ ከሆኑ ሰዎች መካከል ወ/ሮ ሙሪሺዳ ሙሐመድ አንዷ ናቸው፡፡ ወ/ሮ ሙሪሺዳ ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡ ልጃቸው የአዕምሮ ታማሚ በመሆኗ የሚያደርጉት ነገር ጠፍቶባቸው እንደነበር በማስታወስ በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በተደረገላቸው ተከታታይ ድጋፍ ዛሬ ላይ የተሻለ ኑሮን ለመኖር መብቃታቸውን ተናግረዋል፡፡

ልጃቸው ከ35 እስከ 50 ሺሕ ብር የሚደርስ መድኃኒት በፕሮጀክቱ እየተገዛላት ሕክምናዋን በመከታተል ላይ ሆና የተሻለ የጤና ለውጥ በማምጣት በአሁኑ ወቅት የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤት በመግባት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ እንደሆነች ገልጸዋል፡፡

እዚህ ለመድረስ ብዙ ፈተናዎችን ማለፋቸውን የተናገሩት እናት፣ ልጃቸው የአዕምሮ ታማሚ በነበረችበት ወቅት ተደፍራ ጥቃት አድራሹም ፖሊስ ይዞት ሲያበቃ በምስክር ከተረጋገጠ በኋላ እንዲሁ ያለ ምንም ፍርድ መለቀቁን ነው የተናገሩት፡፡

ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያም ጉዳዩን ሲከታተለው እንደነበርና እንዲሁ ያለምንም ፍርድ ከሰባት ዓመት በላይ ማስቆጠሩን ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የቆይታ ጊዜውን አጠናቆ በመውጣቱ ሐሳብ እንደገባቸው የተናገሩት ወ/ሮ ሙርሺዳ እስካሁን ስለተደረገላቸው ድጋፍና ክትትል አመስግነዋል፡፡