ልናገር የተማሪዎች ሥነ ምግባር ነገር ጉዳይ

አንባቢ

ቀን: September 25, 2024

በአንዋር አወል ሞ.

እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በሰማንያዎቹ ማብቂያ ላይ ለዕይታ የበቃ ‘Lean on me’ የተሰኘ አንድ ፊልም ነበር፡፡ እውነተኛ ታሪክ ላይ ተመሥርቶ የተሠራውና መቼቱን በትምህርት ቤት ያደረገው ይኼው ፊልም፣ ጥቂት ደቂቃዎች እንደሄዱ አካባቢ ኢስት ሳይድ የሚባለው ትምህርት ቤት በጠላት ቁጥጥር ሥር የሚገኝ ከተማ ይመስል ቅጥ ባጣ አኳኋን ተተረማምሶ ያሳየናል፡፡ በዚህ የሚያዝ የሚጨበጥ ነገር በታጣበት ሰዓት ጆ ክላርክ የተባለ አንድ መሪ ትምህርት ቤቱን ይረከበዋል፡፡ መሪው ሠራተኞችን ሰብስቦ በሚተዋወቅበት የመጀመሪያው ቀን ላይ ችግር ፈጣሪ ተማሪዎች ከእነ የሚፈጥሯቸው ችግሮች ተዘርዝረው በአስቸኳይ ጠረጴዛው ድረስ እንዲመጡለት ያዛል፡፡ በማስከተልም ተለይተው በመጡለት ተማሪዎች ላይ የማያዳግም ዕርምጃ በመውሰድ ትምህርት ቤቱን በቀናት ውስጥ ‹ያፀዳዋል›፡፡ ይህ ውሳኔው ስሙን በከተማዋ ከንቲባ ጥርስ ሳይቀር እንዲገባ ቢያደርገውም፣ የማታ ማታ ግን ትምህርት ቤቱ በብሔራዊ ፈተና ባስመዘገበው በጎ ውጤት የሰውዬው ስም ታድሶ ታሪኩ ይቋጫል፡፡

በመሠረቱ ከጥንት ከመነሻው ትምህርት ቤትን መቀለስ ካስፈለገባቸው ዓላማዎች መካከል ከፊት ረድፍ ላይ የምናገኘው መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው ዜጎችን የማፍራት ክጃሎት ነው፡፡ እስቲ ለውይይት እንዲመቸን ሥነ ምግባርን ‹የፍልስፍና ቅርንጫፍ ሆኖ ትኩረት የሚያደርግባቸው ዘርፎችም…› የሚለውን የቴክስት ቡክ ሐተታ ወዲያ ብለን ሳናወሳስብ እንፍታው፡፡ ሥነ ምግባር ትክክሉን ከስህተቱ የምናበጥርበት ሚዛናችን ነው (እህሳ?! ያስኬዳል?)፡፡

እንዲሁ በዘልማድ አንድ አዲስ ትውልድ ከሚከሰስባቸው ነጥቦች መካከል ሥነ ምግባር አውራው ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙውን ጊዜ የፊትና የኋላ ትውልዶች ቋንቋቸው አይሰምርም፡፡ አንድ ልሳን እየተነፈሱ ዙሪያ ገባቸውን ባቢሎን ሲያደርጉትም ይስተዋላል፡፡ የቀድሞው ወግ አጥባቂና ተራማጅ የሚልም ሆነ የቅርቡ ፋራና አራዳ የሚለው አመዳደብ በውስጡ የሥነ ምግባርን ንጥረ ነገር ስለመያዙ እንዲሁ ዓይነ ውኃው ያስታውቃል፡፡ የዚህ ጽሑፍ መሻት አንደኛውን ደግፎ ሌላኛውን ነቅፎ የውገና ክርክር ለማድረግ ባለመሆኑ፣ ማጠንጠኛችን ከተማ አቀፉን የተማሪዎች የሥነ ምግባር ሰነድ በትምህርት ቤቶች እየተተገበረ ያለበትን መንገድ መቃኘት ይሆናል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተለመደ አንድ መልካም ተግባር አለ፡፡ መስከረም ላይ ትምህርትን ገና ‹ሀ› ተብሎ ሲጀመር ቀዳሚው ሥራ ልጆቹን በክፍል በክፍል በመደልደል ‹የተማሪዎች የዲሲፕሊን መመርያ› እንዲነበብላቸው እየተደረገ ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ዋና ዋና የሚባሉ የተማሪዎች መብትና ግዴታዎችም በወረቀት ተተይበው በመማሪያ ክፍሎች ይለጠፋሉ፡፡ አሠራሩ የኋላ ኋላ ሊመጡ ከሚችሉ የ‹ሳላውቅ ነው› ሞራዎችን አስቀድሞ ስለሚገፍ ተማሪው አንዳች ጥፋት ሲፈጽም የጥፋቱን ጠንቅም ጭምር ዓይኑ እያየ ይከናነባል፡፡  

የገዘፉና እንደ መንግሥት ዕምነት በ‹ተልዕኮ› ሊከወኑ የሚችሉ ነውጦችን ለጊዜው በውይይት ራዳራችን አናስገባቸው፡፡ ትንንሾቹ የተማሪ የሥነ ምግባር ጉድለቶችን ነጥለን ብናጤን መላ የትምህርት ሥርዓትን የማናጋት አቅማቸው ከምንገምተው በላይ ከፍ ያለ ነው፡፡ አልባሌ የሚመስሉ ግድፈቶች ተማሪውን ተመልካች፣ መምህሩን ገላጋይ፣ ርዕሰ መምህሩን ቅሬታ ሰሚና ውሳኔ ሰጪ በማድረግ በየቀኑ የተለጠጠ ጊዜን ሲሻሙ ይውላሉ፡፡ ይህም የትምህርት ማኅበረሰቡ በጠቅላላ የተሰባሰበበትን እናት ዓላማ አስረስቶ እዚህ ግቡ በማይባሉ ነገሮች ላይ እንዲጠመድና ምርታማ እንዳይሆን ያደርገዋል፡፡

ውሎውን በትምህርት ቤት ያደረገ ማንኛውም ሰው ቢምል እንኳን የማያጣቸው ከጆሮ ጋር ዝምድና የመሠረቱ የሚመስሉ የተወሰኑ የዕለት ተዕለት የመመርያ ጥሰቶች አሉ፡፡

  1. መዘላለፍ ነው፡፡ ተማሪው ሌላ ተማሪን፣ መምህሩ ተማሪውን እንዲሁም ተማሪው መምህሩን (8ኛው ሺሕ ላይም አይደለን?) በመሳደብ ሥነ ልቦናዊ ጥቃት አድርሶ ይገጥመናል፡፡ አልፎ ተርፎም እንዲሁ በቃል አልወጣ ይላቸውና ኮሌታ ለኮሌታ የሚያያዙ አሉ፡፡ የአካላዊ ፀቦቹ ነገር መጨረሻቸው ዕግድ በመሆኑ እሱ እዚህ ላይ ብዙ መስመር ባይሸፍን ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ የመዘላለፉ ምንጭ ግን መመርመር አለበት፡፡

ሀ. ቅስም ልስበር በሚል ተነሳሽነት ሳይሆን እንዲሁ በመልካም ቃላት ያልሠለጠነ አፍ ያላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ብቻ ሲበሳጩ በደመነፍስ የተኮሱትን ያልተገራ ቃል ከተሰዳቢው እኩል አየር ላይ ያገኙትና ክው ብለው ይቀራሉ፡፡ እነዚህ ስህተታቸውን አምነው ያስቀየሙትን ሰው በዚያው ቦታና በዚያው ተመልካች ፊት ይቅርታ ከጠየቁ እንዳይደግሙ አስጠንቅቆ መሸኘቱ ጊዜ መቆጠብ ነው፡፡

ለ. ስድቦቹ አካላዊ ቁመናን፣ ሃይማኖትን፣ ብሔርን፣ የቤተሰብ የኑሮ ሁኔታን፣ የትምህርት አቀባበልን፣ ፆታን ወዘተ… መሠረት ያደረጉ ከሆኑ ከመብት ጥሰትነታቸውም ባሻገር ከበስተጀርባ ቃሉ የሚነካው በዚያ ያለ አካል ስለሚኖር ጉዳዩ መመርያውን በተከተለ መንገድና በዲሲፒሊን ኮሚቴ ታይቶ ዕልባት ሊሰጠው ይገባል፡፡  

ሐ. ተበዳዩ መምህሩስ ከሆነ? እዚህ ላይ የፍትሕ እመቤቷ የዓይኗን ጨርቅ ጥላ ለመምህሩ ‘ማድላት’ ይኖርባታል፡፡ ምክንያቱም ጓድ ሌኒን እንዳሉት በትምህርት ቤቱ ውዱ ሰው መምህሩ ነው፡፡ መምህሩ ሲንጓጠጥ ከተሞዳሞድን በመማር ማስተማሩ ላይ እየተደራደርን መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ስለዚህም የመምህሩን ክብር ከገባበት ገብተን ማስመለስ ይኖርብናል፡፡ ባይሆን ግራና ቀኙን ስናይ መምህሩም ቀስቃሽነቱ ላይ እጁ ካለበት በውስጣዊ አሠራር የእጁን ልንነፍገው አይገባም፡፡

  1. የንብረት አያያዝ ክፍተት ነው፡፡ እዚህ ላይ፣ የወደመ (የተበላሸ) ንብረት ማግኘቱ አንድ ነገር ሆኖ የአውዳሚው ማንነት መለየቱ ግን ሌላ ታሪክ ነው፡፡ በሁለቱ መካከል ያለው ርቀት እንዲሁ ሲታይ የጋት ያህል ቅርብ ቢመስልም፣ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ዕርምጃዎች ሊያስጉዝ ይችላል፡፡ ይህኛው የሥነ ምግባር ግድፈት ከተገቢው በላይ ጊዜን ቀርጥፎ እንዲበላ ከሚያደርጉት ምክንያቶች ዋነኛው ተማሪዎቹ በዕድሜ ከፍ እያሉ ሲሄዱ የግልጽነት ባህላቸው እየሞተ የሚሄድ መሆኑን ነው፡፡ አጥፊን መደበቅ የአሪፍነት መለኪያ አድርጎ ማን እንዳስቀመጠው ባይታወቅም፣ ልጆቹ ችግር ፈጣሪውን አሳልፈን ከምንሰጥ አንገታችንን በካራ ይላሉ፡፡ እንኳን ፊት ለፊት ሊናገሩ ቀርቶ በወረቀት ጻፉና ስጡን ሲባሉ ራሱ ‘ባውቀው ምን አስደበቀኝ?’ በማለት ቀላልደው ያልፉ እንደሆነ እንጂ እቅጩን የመናገር ዕድላቸው የመነመነ ነው፡፡

አውጫጭኙ አልሠራ ሲሉ በእንደዚያ ዓይነቱ ቢሉት ቢሠሩት የማይለወጥ ሁኔታ (Deadlock)፣ ብዙ የትምህርት ቤት አመራሮች በስም ጠሪዎች እየተመሩ የሚሠሩት አንድ ለማዳ ስህተት አለ፡፡ ፈጻሚው ላልታወቀው ጥፋት በደህናው ጊዜ ከሰኞ እስከ ዓርብ ተከታታይ ስሞታ ይቀርብበት የነበረው ተማሪ ላይ የዕርምጃ ብትራቸውን ያሳርፋሉ፡፡ እንዲያውም ከዚህ ጋር በተቆራኘ በአንድ የግል ትምህርት ቤት ሳስተምር ምን ገጠመኝ? ወቅቱ የማትሪክ ፈተና ደረስኩ የሚልበት የግንቦት ወር ነበር፡፡ የትምህርት ቤቱ አሥራ ሁለተኛ ክፍሎች ‘ትምህርታችሁ ይብቃን፣ ልቀቁንና በግል እናጥናበት!’ ብለው ፒቲሽን ቢያሰባስቡም ሳይፈቀድላቸው ቀረ፡፡ በተከለከሉ ማግሥት አምስቱም የአሥራ ሁለተኞቹ የመማሪያ ክፍሎች የአልሙንየም በሮች ቁልፋቸው ተከፍቶ በሮቹ ግን አሻፈረን አሉ፡፡ በኋላ ላይ ተዛማጅ ዕውቀት ባለው ሰው ሲታይ በበሮቹ ዳሮች በሚገኙ ጥቃቅን ክፍተቶች ላይ የማጣበቅ ባህሪ ያለው አንዳች ዝልግልግ ፈሳሽ ተንጠባጥቦባቸው ተገኘ፡፡ ቀጣዩ ዕርምጃ ያው አጥፊውን ለመመንጠር መሞከር መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ የተማሪዎቹ ‘ዓይናችንን ግንባር ያድርገው’ የሚለው የሽምጠጣ ምላሽም እንዲሁ ይጠበቃል፡፡ ትምህርት ቤቱ ፍንጭ ፍለጋው አልሳካ ሲለው ምን አደረገ? መስከረም ከጠባ ጀምሮ አስቸጋሪ የነበረውን ልጅ ለይቶ ወላጁን አስጠራው፡፡ ልጁ ጠብታ ፍርኃት ያልፈጠረበትና ሞጥሟጣ ብጤ ስለነበረ አባቱ ፊት ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው?

‹‹እስቲ በሮቹን የምከረችምበት አንድ ነፍስ ያለው ምክንያት ስጡኝ፡፡ ክላስ መቅጣቱን እንደሆነ በሩ ተበርግዶ እያለም ስፈልግ ለቀናት እልም ብዬ እጠፋ ነበር፡፡ ትምህርት ይቁምልን፣ ለማትሪክ እናጥናበት ብለው በተፈራረሙት ውስጥም የሌለሁበት ብቸኛው ተማሪ እኔ ነኝ፡፡ እንዴት እንዴት ብታስቡ ነው እኔ የመጣሁላችሁ?…›› አለ፡፡ ምን ይበሉት? መጨረሻ ላይ ልጆቹ አንድ ወይ ጥንድ ሆነው ባጠፉት ሁሉም ቅጣት ቀመሱ፡፡

በለስ ቀንቶን አሊያም ፖሊሳዊ የሆነ የጥበብ ዛር በእኛ ላይ አድሮ አጥፊውን በትክክል ከደረስንበት ግን፣ የወደመው ንብረት ሆን ተብሎ ይሁን አጋጣሚው እንደሆነ ማጣራት ያስፈልጋል፡፡ ፍትሐዊ ለመሆን ያህልም ንብረቱ ከመጎዳቱ በፊት የነበረበት የጤና ሁኔታ አስመስክሮ መገምገሙ ደግ ነው፡፡ አለበለዚያ ድሮ ድሮ ትምህርት ቤቶች ጥቅምት ላይ አንድ ሐሙስ የቀረውን አሮጌ መጽሐፍ ያድሉና ሰኔ ላይ ያው መጽሐፍ ሲመለስላቸው ‘ቀደድከው’ ብለው እንደሚያስከፍሉት ዓይነት አላስተማሪ ቅጣት ሊሆን ነው፡፡

ለዘለቄታው ተማሪዎቹ የእኔነት ስሜታቸው እንዲጎለብት ሰፋፊ ሥራዎች መሠራት አለባቸው፡፡ በኃላፊነት ንብረት ቆጥሮ የማስረከቡን ነገርም እንዲሁ የመደበኛው አሠራር አካል መሆን አለበት፡፡ በሩ ባልተበጀ ክፍል ውስጥ የተሸረከተ ነጭ ሰሌዳ አገኘህና ገቢ ወጪው በበዛበት ክፍል አጥፊውን ውለዱ ብሎ የዚያ ክፍል ልጆችን ማስጨነቅ ምንም ስሜት አይሰጥም፡፡

  1. የፈተና ኩረጃ ነው፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እ.ኤ.አ. በ2004 ባካሄደው ጥናት መሠረት 90 በመቶ ተማሪ እንደሚኮርጅ አጥኚዎቼን አሰማርቼ ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡ ኩረጃን ተከትሎ ሊፈጠር የሚችል የልፈርምብህ አላስፈርምም እሰጣ አገባም ይኖራል (ሌላ የሥነ ምግባር ችግር)፡፡ (የኩረጃን ነገር ራሱን በቻለ ርዕስ በስፋት እመልስበታለሁ እንጂ እንዲህ ነካክቼው አይወጣልኝም)፡፡
  2. ስልክ ይዞ ትምህርት ቤት መምጣት፡፡ በነገራችን ላይ፣ አንዳንዱ የዲሲፒሊን ችግር ዘመን ወለድ ነው፡፡ ለምሳሌ የዛሬ ሩብ ክፍለ ዘመን ገደማ ስልክ ይዞ በትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ መገኘት የተፈቀደ ይሁን የተከለከለ የሚገልጽ አንቀጽ አይኖርም፡፡ ዛሬም ቢሆን በአዲስ አበባው የተማሪዎች የዲሲፕሊን መመርያው ላይ ስልክ መከልከሉን በማያሻማ ቋንቋ አልተቀመጠም፡፡ በአንድ ሰርኩላር ደብዳቤና በየመድረኩ ስልክ በአፅንኦት ሲኮነን መስማቱ ግን የተለመደ ነው፡፡ በተግባር፣ ብዙ ትምህርት ቤቶች ስልክን ይከለክላሉ፣ በር ላይ የዕለቱ አጋፋሪዎቻቸው እየፈተሹ እንዲያስገቡ ያቆማሉ፣ በሉ ሲላቸውም ክፍል ድረስ መጥተው ድንገተኛ ብርበራን ያካሂዳሉ፡፡ ይዞ በተገኘው ላይም ከ500 እስከ 1,000 ብር ቅጣት ይጥላሉ፡፡ አንዳንድ ቦታም ሲም ካርድ ብቻ መልሰው ስልኩን ግን የትምህርት ካሌንደሩ ማብቂያ ላይ ከምስክር ወረቀት ጋር አብረው ያስረክባሉ፡፡

‘ስማርት ሲቲ’ ለመመሥረት እየተጋሁ ነው የሚል አንድ መንግሥት ‘ስማርት ሴል ፎን’ አትያዙ ሲል ላየ ሰው ነገርየው አያዎ ቢመስልም ግን አይደለም፡፡ ከባድ የሆነ የአጠቃቀም ችግር የተጠናወተው ብዙ የትምህርት ቤት ማኅበረሰብ አለ፡፡ በተለይ የማኅበራዊ ሚዲያው አብዮት መፈንዳትን ተከትሎ ተቀርፀው ከሚለቀቁ ቪዲዮዎች መካከል ዓይቶ ለመጨረስ እንኳ የሚዘገንኑ መዓት ናቸው፡፡ የመምህርን ገጸ ባህሪ ይላበሱና ግን ሳቅ ጫርን ባዮች ስለሆኑ አንዳቸውም መምህሩ የዋለበት ላይ አይውሉም፡፡ የተማሪ ዩኒፎርም ይደርቡና አንዳቸውም ‘ጂንዬስ’ የሚያሰኛቸው አካዳሚያዊ ጉዳይ ሲከውኑ አይታዩም፡፡ ከደረቡት ልብስ ጋር አራምባና ቆቦ የሆነ ነገር ለመሥራት የመምህሩን ጋዎን ማራከሱ፣ በተማሪ ዩኒፎርም ሥር መከለሉ ለምን እንደሚያስፈልጋቸው በበኩሌ አይገባኝም፡፡ 

  1. ሱስ ነው፡፡ ይኼኛው በሁለት መንገድ መመልከት እንችላለን፡፡

ሀ. ልጆቹ እየፎረፉ በትምህርት ቤቱ ዙሪያ ባሉ ሱስ ቤቶች የሚጠቀሙት ነው፡፡ አንዳንድ ሰሞን ደንቦችና ትምህርት ቤቶች ተቀናጅተው በብርቱ ይሠሩበታል፡፡ አብዛኛው የዓመቱ ሰሞን ግን እነሱም እንደ ማንም መንገደኛ ‘አዋኪ ጉዳዮች’ በማለት ሲያወግዙ ነው የሚታዩት፡፡ ይኼ ሁሉም ነገራችን ላይ የሚንፀባረቀው አንድን ነገር በዘመቻ ለመለወጥ የመሞከር አባዜያችን አካል ተደርጎ ሊታይ ይችላል፡፡  

ለ. ሱስዬው በቦርሳ ውስጥ ተወሽቆ ቅጥር ግቢው ድረስ የሚመጣበት አጋጣሚም አለ፡፡ ተማሪዎቹ ተበጥብጦ በሚጠጣው ዱቄት አስመስለው ሐሺሽ ያስገባሉ ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ ውኃ አስመስሎ አረቄ አስገባ የተባለ ልጅም ገጥሞኛል፡፡ ‘ወየው ጉዴ!’ ያልኩት ግን ልጁ ወላጅ ጥራ ተብሎ ወላጅየው ‘እኛ ቤት ውኃም አረቄም ጠረጴዛ ላይ ስለምናኖር ልጃችን የተሳሳተው ውኃ አነሳሁ ብሎ ነው’ በማለት ለልጃችን ቤዛ እንሁን ያሉበት መንገድ ሰምቼ ነው፡፡

ከዚያ ውጪ ሲጋራ በጣም የተለመደ ነገር ነው፡፡ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ሃምሳ ዓመት ወደኋላም ሄደን የአስኳላ መፀዳጃ ቤቶች ብንፈትሽ የሲጋራ ቁሩዎች እንደምናገኝ አውቃለሁ፡፡ የቁማር ነገርም እንዲሁ አሳሳቢ ነው፡፡ 

ሰብሰብ ሳደርገው፣ ‘የላቀ ውጤት’ የሚባለው ነገር በመልካም ሥነ ምግባር ካልታጀበ ጎበዙ ተማሪ ማለት በየጊዜው ቀይ ካርድ የሚበላ ጎበዝ ተጫዋች እንደ ማለት ነው፡፡ ያ ዓይነቱ ተጫዋች ደግሞ ከሚሞላው ይልቅ የሚያጎድለው ይበዛል፡፡ በሌላ በኩል፣ የትም ዓለም ላይ ትምህርት ቤት የቻለው አመል ማንም አልቻለውም፡፡ ትምህርት ቤቶች በሚዘጉባቸው ወቅቶች ወላጅ ልጆቹን ሃይ! ብሎ ሰሚ ሲያጣ ተማሮ፣ ‘አረ ያ ገመና ከታች ትምህርት ቤትህ በተከፈተልህና ወደዚያ በተገላገልኩህ!’ የሚል ቤተሰብ ቁጥሩ ቀላል አይደለም፡፡ ትምህርት ቤቶች የፕሮፌሽናሎች መናኸሪያዎች እንደ መሆናቸው መጠን ሆድ አስፍተው ልጆችን ይታገሱ ዘንድም ይጠበቃል፡፡ የተያዘው ሥራ ዜጋን ማሳመርም አይደል? ማሳመር ደግሞ ሞልቶ የሚፈስ ትዕግሥት የሚጠይቅ ትልቅ ሥራ ነው፡፡ ማይክል አንጄሎ የሲስቲን ቻፕል ጣሪያ ለማሳመር ለድፍን አራት ዓመታት በጀርባው ተኝቶ ሥዕሎቹን ሠርቷቸዋል ይባላል፡፡ በእኔ እምነት፣ የመምህር ሥራ ከማይክል አንጄሎ የጥበብ ሥራ አይተናነስም፡፡ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው የአርቲስቱ የኪነት ሥራዎቹም መምህሩ በየጉራንጉሩ ከሚቀርፃቸው ዜጎች አይበልጡም (ማነፃፀር ካልቀረ እንዲህ ነው)፡፡

የእኛ አገር ትምህርት ቤቶች መግቢያዬ ላይ ከጠቀስኩት ሙቪ አንፃር ካየናቸው ቅዱሳን ሥፍራዎች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ያም ሆኖ ብልሹ ሥነ ምግባር ራስ ምታታችን አይደለም እያልኩ አለመሆኑ ይታወቅልኝ (ያ ሁሉ አውርቼ እንዴትስ እላለሁ?)፡፡ ከፊልሙ መወሰድ ያለበት ብዬ የማምነው፣ ርዕሰ መምህሩ ያዋጣል ብሎ ባመነበት መንገድ ሲሄድ መዳቢዎቹ ‘አበጀህ!’ ባይሉትም ጣልቃ ግን አልገቡበትም፡፡ ያው ጉዳይ እኛ ጋር ተከስቶ ቢሆን ኖሮ እርሙን ለአንድ ቀን ዞር ብሎ አይቶህ የማያውቀው የአካባቢ ሹመኛ ወይም የቦርድ የሆነ ነገር፣ ደርሶ ‘የነገ አገር ተረካቢዎች ላይ የተፈጸመው በፍትሕ ላይ ያለው አመኔታን የሚሸረሽር በደል…’ በማለት አማርኛውን ያሰማምርብሃል፡፡ በእርግጥ አቶ ክላርክ ያደረጉት ለተማሪው ሁለተኛ ዕድልን ያልሰጠ ጥድፊያም አድናቂው አይደለሁም፡፡ ሁሌም ቢሆን ሥነ ምግባር በዕድሜ ሞረድ እየተሳለ ከመሄዱ በፊት ድፍድፍ ነው፡፡ ድፍድፉ የሚጠራው እርምት እየሰጡ ሁለተኛ ዕድልን ባለመከልከል ነው፡፡ ካልሆነ በአፉ ‘እንዳይለመድህ!’ እያለ በሽጉጥ ደፋው እንደተባለው ዓይነት ቀልድ ነው ይሆናል፡፡

ሌላው ሊታሰብበት የሚገባው ነገር እነዚህን የግሎባይላይዝድ ዓለም ውልዶች በ‘እጅ በደረቱ’ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ደንብ ቢስተናገዱ ብዙ ነገሮች ልክ አይመጡም፡፡ መመርያው አንቀጾቹ ተፈትሸው መዘመን ያለባቸው ይከለሱ፡፡ ዜጋን ሰብስቦ ‘ፀጥ አርጋቸው’ መሆን ቁምነገር አይደለም፡፡ ተፈጥሯዊውን የ‘ረብሻ’ ጅረት ባገድነው ቁጥር ተጠራቅሞ የራሱ ሽንቁር ያበጅና የማይገታ ጎርፍ በመሆን መድረስ ያልነበረበትን ብዙ ጉዳት ያደርሳል፡፡

ሰላም!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በመምህርነት የሚያገለግሉ የትምህርት ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡