የቻይና አህጉር አቋራጭ ተወንጫፊ ሚሳኤሎች
የምስሉ መግለጫ,አሜሪካ እንደምተለው እነዚህን አህጉር አቋራጭ ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን ጨምሮ ቻይና ከ500 በላይ ኑክሌር ተሸካሚ የሚሳዔል አረሮች አሏት።

ከ 4 ሰአት በፊት

ቻይና ከበርካታ አስርት ዓመታት በኋላ የመጀመሪያ ነው የተባለውን ያልተለመደ አህጉር አቋራጭ ሚሳዔኤልን በዓለም አቀፍ የውሃ አካል ላይ የማስወንጨፍ ሙከራ ማድረጓን አሳወቀች።

አጎራባች አገራት ደግሞ ሙከራውን በመቃወም ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

ለ40 ዓመታት ከበለጠ ጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ረቡዕ ዕለት የተደረገው ሙከራ “የተለመደ እና በየትኛውም አገርም ሆነ ዒላማ ላይ የተነጣጠረ” እንዳልሆነ እንዲሁም “ለሚመለከታቸው አገራት” የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ባለሥልጣናት መናገራቸውን የቻይና መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ነገር ግን ጃፓን ምንም ዓይነት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ እንዳልደረሳት በመጥቀስ ከአውስትራሊያ እና ከኒውዚላንድ ጋር በሙከራው ላይ ቅሬታዋን አሰምታለች።

ቻይና ባላት ረጅም ርቀት የሚጓዙ ኑክሌር ተሸካሚ ሚሳዔሎች ኢንዶ-ፓሲፊክ በተባለው ቀጣና ባለው ውጥረት ላይ አሁን ያደረገችው ሙከራ ተጨማሪ ስጋትን የሚፈጥር መሆኑን ተንታኞች ይናገራሉ።

ባለፈው ዓመት አሜሪካ ቻይና የመከላከያ አቅሟን ለማጠናከር በሚል የኑክሌር ጦር መሳሪያ ግንባታዋን እያስፋፋች ነው ስትል አስጠንቅቃ ነበር።

አህጉር አቋራጭ ተወንጫፊ ሚሳኤል አስከ 5,500 ኪሎ ሜትሮችን በመጓዝ ጥቃት የሚፈጽም ሲሆን፣ ይህም ሃዋይን ጨምሮ ዋነኛውን የአሜሪካ ክፍል በቻይና የሚሳኤል ዒላማ ክልል ውስጥ የሚያስገባ ነው።

ቻይና ያላት የኑክሌር ጦር መሳሪያ አቅም ከአሜሪካ እና በሩሲያ ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ሲሆን፣ ከየትኛውም ወገን ሊሰነዘር የሚችልን ጥቃት ለማስቀረት ብቻ ያለመ መሆኑን በተደጋጋሚ ትገልጻለች።

አሜሪካ እንደምትለው ቻይና አህጉር አቋራጭ ተወንጫፊ ሚሳዔሎችን ጨምሮ ከ500 በላይ የኑክሌር አረሮች በጦር መሳሪያ ክምችቷ ውስጥ ይገኛሉ።

ወደ ደቡባዊ የፓሲፊክ ውቅያኖስ ረቡዕ ዕለት የተደረገውን የአህጉር አቋራጭ ሚሳዔል ሙከራን በተመለከተ የቻይና መከላከያ ሚኒስቴር “የተለመደ ዓመታዊ ልምምድ” ሲል ገልጾታል።

ነገር ግን ተንታኞች እንደሚሉት ቻይና ከዚህ በፊት አህጉር አቋራጭ የዓለም አቀፍ ሚሳኤል ሙከራን ያደረገችው ከ40 ዓመታት በፊት በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ ነበር። በወቅቱም ሙከራው የተደረገው በዓለም አቀፍ የውሃ አካል ላይ ሳይሆን ዢንጂያንግ ግዛት ውስጥ በሚገኝ በረሃ ላይ ነበር።

የኑክሌር ሚሳዔሎች ተንታኝ የሆኑት አንኪት ፓንዳ “እንዲህ ዓይነቱ የሚሳዔል ሙከራ በአሜሪካ እና በሌሎች አገራት በተደጋጋሚ የሚካሄዱ ሲሆን፣ ለቻይና ግን የተለመደ አይደለም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጨምረውም ቻይና በአሁኑ ወቅት “የኑክሌር ጦር ማሳሪያ ትጥቋን ማዘመን” እያካሄደች ሲሆን፣ ይህም ጉልህ ለውጥ ማምጣቱን ይገልጻሉ።

አውስትራሊያ ቻይና ያደረገችውን ሙከራ በተመለከተ ድርጊቱ “በቀጠናው አለመረጋጋት የሚፈጥር እና የተዛባ ስሌት እንዲወሰድ የሚያደርግ ነው” ብላለች። ከቻይና ማብሪያ እንዲሰጣትም ጠይቃለች።

ኒው ዚላንድ “ያልተጠበቀ እና አስጊ ለውጥ” ብላ ሙከራውን ጠርታዋለች።

ፓንዳ ግን የቻይና ለውጥ ፖለቲካዊ መልዕክት ለማስተላለፍ ያለመ ነው ብለዋል።

“ቀጠናውን እና አሜሪካን ስለ ኑክሌር መሣሪያ አሰላለፍ የሚያስታውስ እና እስያ ቀስ በቀስ እየተለመወጠ መሆኑን የሚያሳይ ነው” ብለዋል።

አሜሪካ እና አጋሮቿ በቀጠናው ያላቸውን አሰላለፍ እንዲከልሱ የሚያደርግ ነው ብለው የሚያምኑ ተንታኞችም አሉ።

በደቡብ ኮሪያ ኢውሀ የሴቶች ዩኒቨርስቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያ ሌይፍ ኤሪክ ኤስሊ “ለአሜሪካ የሚተላለፈው መልዕክት በታይዋን ቀጠና ግጭት ቀጥታ የምታደርገው ጣልቃ ገብነት አገሪቱን ለጥቃት እንደሚያጋልጣን ነው” ብለዋል።

በእስያ ላሉ የአሜሪካ አጋሮች “ተንኳሽ ድርጊት እና የቻይናን በአንድ ጊዜ በተለያየ አቅጣጫ የመዋጋት አቅም የሚያሳይ” ነው ሲሉም ያክላሉ።

በሲንጋፖር በኤስ ራጃርታንም የዓለም አቀፍ ጥናት ዩኒቨርስቲ መምህር ድሩ ቶምሰን “ለምን አሁን የሚለው ዋና ነገር ነው። ቻይና ማንኛውንም አገር ዒላማ እንደማታደርግ አስታውቃለች። ግን ቻይና ከጃፓን፣ ከፊሊፒንስ እና ከታይዋን ጋር ፍጥጫ ውስጥ ናት” ብለዋል።

በቻይና እና በአሜሪካ መካከል ያለው ግንኙነት እየተሻሻለ ቢሆንም፣ ቻይና በቀጣናው ጫና ለመፍጠር የምታደርገው ጥረት ግንኙነታቸውን የሚወስን ይሆናል።

ቻይና እና ፊሊፒንስ በይገባኛል በሚወዛገቡበት የውሃ ክፍል ላይ መርከቦቻቸው ግጭት ውስጥ እየገቡ ግንኙነታቸውም እየሻከረ መጥቷል።

የቻይና የስለላ አውሮፕላን የአየር ክልሌን ጥሷል በማለት ይህም “ተቀባይነት የለውም” ስትል የከሰሰችው ጃፓን ተዋጊ ጀቶች ማዘጋጀቷ ይታወሳል።