የሄዝቦላህ ወታደሮች

19 ጥቅምት 2023

ተሻሽሏል ከ 5 ሰአት በፊት

ሐማስ ድንገተኛ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የእስራኤል አንድ ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን ወታደራዊ ዘመቻ ጋዛ ላይ ስትከፍት የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ሐማስን ደግሞ ከእስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ መግባቱን አስታውቋል።

የእስራኤል ጥቃት እየበረታ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ፣ ሄዝቦላ ከሊባኖስ በሚያስወንጭፋቸው ሮኬቶች እና ሚሳኤሎች ሰሜናዊ እስራኤልን በተደጋጋሚ ሲያጠቃ፣ እስራኤልም በጦር አውሮፕላን እና በከባድ መሳሪያዎች ምላሽ ስትሰጥ ቆይታለች።

አሁን ደግሞ ከጋዛ ካለው ሐማስ በተጨማሪ በሊባኖስ ሌላ የጦር ግንባር የከፈተችው እስራኤል ባለፉት ቀናት ፊቷን ወደ ሄዝቦላህ በማዞር የቡድኑ ይዞታዎች ናቸው ያለቻቸውን ይዞታዎችን በአየር እየደበደበችው ነው። በዚህም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሊባኖስ ውስጥ ተገድለዋል።

ይህም ቢሆን ግን ሄዝቦላህ እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም አሁንም ቴል አቪቭን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የእስራኤል ግዛቶች ሚሳኤሎችን እና ሮኬቶችን እየተኮነ ነው።

ለመሆኑ በመካከለኛው ምሥራቅ ኃያል የሚባለው እና ለእስራኤል ዋነኛ የራስ ምታት የሆነው እንዲሁም በዋነኛ ባላንጣዋ ኢራን የሚደገፈው የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ ማነው?

* * *

ለእሰራኤል ራስ ምታት የሆኑ ሁለት ቡድኖች አሉ። አንዱ ሐማስ ነው። ሌላው ሄዝቦላህ ይባላል።

ሐማስ የፍልስጥኤም ነው። ሄዝቦላህ የሊባኖስ።

ሁለቱም በኢራን ይደገፋሉ።

ነገር ግን ሄዝቦላህ የሺኣ ሙስሊም የፖለቲካ ድርጅት ሲሆን፣ ሐማስ በሱኒ ሙስሊሞች የተሞላ ነው።

ሄዝቦላህ መልከ ብዙ ነው። የፖለቲካ ፓርቲ ብቻ አይደለም። ማኅበራዊ አገልግሎት ላይ ይሠራል፣ ፖለቲካ ላይ ይሳተፋል፤ ሚሊሻም ነው። ድንበር ተሻጋሪ ወታደራዊ ክንፍም አለው።

ይህ መልከ ብዙነቱ በሊባኖስም ከሊባኖስ ውጭም አቅም ፈጥሮለታል።

ለመሆኑ ሂዝቦላህ ማን ነው? እንዴትስ ለእስራኤል ፈተና ሊደቅን ቻለ?

ቻርት

ብሶት የወለደው ፓርቲ

ሄዝቦላህ ቃሉ አረብኛ ነው። “የጌታ ፓርቲ” እንደማለት ነው በጥሬው ሲተረጎም።

ዛሬም ድረስ በኢራን ይደገፋል። ያዋለደችውም ኢራን ናት። በትጥቅም፣ በስንቅም ደግፋ ለዚህ ያበቃቸው ኢራን ናት። ይህ የጀመረው ከፈረንጆቹ 1980ዎቹ መባቻ ነው።

ሄዝቦላህ ከደካማ የፖለቲካ መዋቅር ውስጥ የወጣ ጠንካራ የሚባል ድርጅት ነው። ሕዝብ የሚታደገው ሲሻ፣ መንግሥት ባጣ ጊዜ ሄዝቦላህ ደርሶ ነው ‘ሕዝባዊ’ መሆን የቻለው።

እስራኤል ሊባኖስን መውረሯን ተከትሎ ደካማ ውክልና የነበራቸው የደቡባዊ ሊባኖስ ሺአ ሙስሊሞችን ለመታደግ የተመሠረተ ቢሆንም፣ አሁን ግን ፖለቲካዊ ፍላጎቱ እና ተጽእኖ ፈጣሪነቱ ቀጠናዊ ለመሆን በቅቷል።

ፓርቲውን ከ1992 ጀምሮ እስከ ዛሬ የሚመሩት ሐሰን ናስራላህ ናቸው። በደጋፊዎቻቸው ዘንድ ተደማጭነታቸው ከፍ ያለ ነው።

ሄዝቦላህ ርዕዮተ ዓለማዊ እሳቤው ከምሥረታው ዘመንም ራቅ ይላል። በሊባኖስ የሺአ ኢስላም ማንሰራራትን ተከትሎ ወደ 60ዎቹ ዘመን ይሳባል።

የሄዝቦላህ ደጋፊዎች በአደባባይ ድጋፋቸውን ሲገልጹ
የምስሉ መግለጫ,ሄዝቦላህ ሊባኖስ ውስጥ ሠፊ የድጋፍ መሠረት አለው

ሄዝቦላህ በሊባኖስ ፖሊቲካ ውስጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታል ብሎ ማለፍ የድርጅቱን ሚና ማሳነስ ይሆናል። በዚያች አገር ፈላጭ ቆራጭ ነው።

የሄዝቦላህ የፖለቲካ ክንፍ ‘ሎያሊቲ ቱ ሬዝስታን ብሎክ’ በተባለ ፓርቲ በሊባኖስ ፓርላማ ውስጥ ይወከላል።

ሄዝቦላህ በሊባኖስ ካቢኔ ውስጥ ድምጽን በድምጽ የመሻር ሥልጣን አለው።

ሄዝቦላህ ባለፉት አሥርታት በርካታ ጥቃቶችን ሲፈጽም እና ግድያዎችን ሲያቀነባብር ቆይቷል። በብዛት ዒላማ የሚያደርገው ደግሞ የአሜሪካ እና የእስራኤል ጥቅሞች ላይ ነው።

ሄዝቦላህ በአሜሪካ፣ በእስራኤል፣ እና በሌሎች የምዕራብ አገራት እንዲሁም በአረብ ሊግ የሽብር ቡድን በሚል ተፈርጇል።

ሄዝቦላህ ድርጅት የሶሪያ ፕሬዝዳንት የባሻር አል አሳድ ቀኝ እጅ እና የማያወላዳ ደጋፊ ነው።

የ2011 (እአአ) የሶሪያን አመጽ ተከትሎ ሄዝቦላህ ከአሳድ ጎን ሆኖ ተፋልሟል። በአማጺዎች የተወሰዱ ቦታዎችን ከመንግሥት ኃይሎች አብሮ እና ተባብሮ አስመልሷል።

በተለይም ከሊባኖስ ኩታ ገጠም የሆኑ ቀበሌዎችን ሄዝቦላህ ለአሳድ አስረክቦ አመኔታን አትርፏል።

እስራኤል በሰላሙ ጊዜ ሳይቀር እጅግ በተደጋጋሚ በሶሪያ የሚገኙ የሄዝቦላህን እና የኢራንን ወታደራዊ ዒላማዎች ታጠቃለች። ሆኖም ግን ጥቃት ፈጸምኩ አትልም።

ጥቃቶቹ ግን ሄዝቦላን አዳክመውት ይሆናል እንጂ አላጠፉጥም።

የሄዝቦላህ በሶሪያ የውስጥ ጉዳይ መግባቱን ተከትሎ በሊባኖስ የሃይማኖት መስመርን የተከተለ የእምነት ግጭት እንዳይቀሰቅስ ስጋት ነበር።

የሄዝቦላህ ወታደሮች
የምስሉ መግለጫ,የሄዝቦላህ ወታደሮች

ሄዝቦላህ አሸባሪ ድርጅት ነው?

ሄዝቦላህ በብዙ የመካከለኛው ምሥራቅ አረብ አገራት የጎሪጥ እንዲታይ ያደረገው በዋናነት በኢራን መደገፉ ነው።

በሁለተኛነት ደግሞ ድጋፉ እና መታመኑ ለሺአ የአላዋይት ቅርንጫፍ እምነት እንዲሁም ለፕሬዝዳንት አሳድ መሆኑ ነው።

በተለይ ሳዑዲ አረቢያ የኢራን እና የአጋሮቿ ወታደራዊ ጡንቻ መጠናከር ሁሌም በስጋት እና በፍርሃት ነው የምትመለከተው።

ሄዝቦላህ ለአረቡ ዓለም ብቻ ሳይሆን ለእስራኤልም ፈተና ነው።

ከአንድ ሳምንት በፊት ሐማስ በእሰራኤል ላይ የፈጸመውን መብረቃዊ ጥቃት ተከትሎ እስራኤል እና ሄዝቦላህ ሰይፍ ተማዘዋል።

ሄዝቦላህ ለሐማስ እና ለፍልስጥኤም ሕዝብ ድጋፉን ያሳየ ሲሆን፣ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁነቱን አረጋግጧል።

የሄዝቦላህ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ጥንካሬው እንዲሁም ለሚመኩበት በአገር ውስጥ የሰጠው የደኅንነት ከለላ እና ማኅበራዊ አገልግሎት በሊባኖስ ተወዳጅ አድርጎታል።

ሄዝቦላህ በሊባኖስ ያለው ተሰሚነት እና ጥንካሬ መንግሥታዊ ተቋማትን እስከመገዳደር ያደርሰዋል። ወታደራዊ አቅሙ ከሊባኖስ መከላከያ ሠራዊት ቢበልጥ እንጂ አያንስም።

ከፊል ሊባኖሳውያን በፓርቲው ኩራት እና መተማመን ይሰማቸዋል፤ በተለይ የሺአ ማኅበረሰብ የሆኑቱ። ሌሎች ሊባኖሳዊያን ደግሞ ሄዝቦላህ ለሊባኖስ አንድነት ጠንቅም ጭንቅም ነው ይላሉ።

የሊባኖስ ሄዝቦላህ መሪ ሐሰን ናስራላህ
የምስሉ መግለጫ,የሊባኖስ ሄዝቦላህ መሪ ሐሰን ናስራላህ

ሄዝቦላህ እንዴት ተመሠረተ?

ሄዝቦላህ በትክክል እንዴት መጣ? ከየት መጣ? የሚለውን ለማወቅ የሆነ ቀን እና ወርን መጥቀስ እንዲህ ቀላል አይደለም።

ይሁንና በ1982 (እአአ) እስራኤል ደቡባዊ ሊባኖስን ስታጠቃ ያን ለመመከት በሚል እንደተፈጠረ ይታመናል።

በተለይ የሺአ መሪዎች ጥቃቱን በወታደራዊ ምላሽ መመከት እንደሚያሻ አምነው ሲወስኑ፣ ድርጀቱ አማል ከሚባል ፓርቲ ተሰንጥቆ እና አፈንግጦ እንደወጣ ይገመታል።

ያኔ አዲስ የነበረው ‘ኢስላሚክ አማል’ የሚባለው ድርጅት ወታደራዊ ድጋፍ ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ሲጎርፍለት ወሳኝ ድርጅት ሆኖ ብቅ አለ።

ከኢስላሚክ አማል ደግሞ የሺአ ሚሊሻ ሆኖ ሄዝቦላህ ተወለደ።

ድርጅቱ በእስራኤል እና በእስራኤል በሚደገፉ እንደ ሳውዝ ሊባነን አርሚ (SLA) ባሉ ድርጅቶች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት አደረሰ።

በርካታ ጥቃቶችንም አቀነባበረ።

ሄዝቦላህ በ1983 (እአአ) በአሜሪካ ኤምባሲ እና በአሜሪካ ባሕር ኃይል ላይ የፈጸማቸው ጥቃቶችን በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው። በወቅቱ 258 አሜሪካውያን እና 58 ፈረንሳያውያን በሞቱበት ጥቃት እጁ እንዳለበት ይታመናል።

በ1985 (እአአ) ሄዝቦላህ በይፋ አሜሪካ እና ሶቭየት ኅብረት ቀንደኛ የኢስላም ጠላት ናቸው ብሎ ካወጀ በኋላ፣ እስራኤል ከምድረ ገጽ መጥፋት አለባት ሲል ዛተ።

ይህን ካለ በኋላ እስራኤል በጉልበት ከያዘቻቸው የፍልስጤም መሬቶች ትውጣ በሚል ፕሮግራሙን ይፋ አድርጎ በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ እንደ አንድ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ኃይል ተመሥርቷል።

የጦር መሳሪያ እና የወታደሮች ትርኢት
የምስሉ መግለጫ,የሄዝቦላህ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ተጽእኖ ከሊባኖስ ባሻገርም ይሰማል

ሊባኖስ ረዥም ዓመታትን በእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ቆይታለች።

በ1989 (እአአ) ‘ጣይፍ አኮርድ’ የተባለው ስምምነት ሲፈረም የሊባኖስ የእስር በእስር ጦርነት ቆመ።

በዚህ ስምምነት መሠረት ደግሞ ሁሉም ነፍጥ ያነሱ ጠመንጃቸውን እንዲያስቀምጡ ተባለ።

ሄዝቦላህ ግን ነፍጥ ይዞ ቆየ። ወታደራዊ ክንፉ ‘ኢስላሚክ ሬዚስታንስ’ በሚል ራሱን ቀይሮ ብቅ አለ። ዓላማውን የእስራኤልን ወረራ ለማስቆም በሚል መሣሪያውን እንደያዘ ቆየ። ዛሬም ድረስ ጠመንጃውን እንደታጠቀ አለ።

ሄዝቦላህ በ1992 (እአአ) ለመጀመሪያ ጊዜ በሊባኖስ ምርጫ ተሳትፏል።

የእስራኤል ኃይል በ2000 (እአአ) ከሊባኖስ ለቆ ሲወጣ ሄዝቦላህ ለእስራኤል መውጣት ትልቁን ዕውቅና አገኘ።

ይህን ተከትሎ ነፍጡን እንዲያስቀምጥ በውስጥም በውጭም ቢጎተጎትም ይህን ሳያደርግ ቀረ።

ለዚህም የሰጠው ምክንያት እስራኤል አሁንም በሼባአ እና ሌሎች ደቡባዊ ግዛቶች እንዲሁም በድንበር አካባቢዎች መኖሯ እና ስጋት መሆኗን ነው።

ሄዝቦላህ እና እስራኤል

በአውሮፓውያኑ በ2006 ሄዝቦላህ ድንበር ተሻጋሪ ጥቃት በመፈጸም 8 የእሰራኤል ወታደሮችን ገድሎ ሁለቱን አግቶ ወሰደ። ይህ እስራኤልን በማስቆጣቱ ከፍተኛ ወታደራዊ ጥቃት ፈጽማበታለች።

በምላሹ የእሰራኤል የጦር አውሮፕላኖች በደቡባዊ ቤይሩት እና በሄዝቦላህ ጠንካራ ይዞታዎች ላይ ድብደባ በመፈጸም 1 ሺህ 125 ሊባኖሳውያንን ገድላለች። ከሟቾቹ ብዙዎቹ ንጹሐን ነበሩ።

34 ቀናት በወሰደው በዚህ ግጭት ሄዝቦላህ 4ሺህ ሮኬቶችን በመተኮስ 45 ሲቪሎችን ጨምሮ በድምሩ 119 የእስራኤል ወታደሮችን ገድሏል።

ከዚያ ጦርነት በኋላ ሄዝቦላህ ይበልጥ እንደተጠናከረ ይገመታል። በዚህ ወቅት አወዛጋቢው የድንበር አካባቢ በሊባኖስ መከላከያ እና በተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ የሚጠበቅ ሆኗል።

የሄዝቦላህ ወታደሮች

ሄዝቦላህ፡ ከመንግሥት በታች መንግሥት

ሄዝቦላህ እጁ ረዥም ነው። በሊባኖስ ፖለቲካ ላይ ያለውን ጠንካራ ተጽእኖ አለው። ለዚህም አንድ ጉልህ ምሳሌን እንቅጥቀስ።

በ2008 (እአአ) በምዕራባውያን የሚደገፈው የሊባኖስ መንግሥት አንድ እርምጃ ወሰደ።

በዚህም የሄዝቦላህን የግል ቴሌኮሚዩኒኬሽን መስመርን ቆረጠ። የቤይሩት አውሮፕላን ማረፊያ ደኅንነት ክፍል ዋና አዛዡን ከኃላፊነቱ አነሳ። ለምን ሲባል ዋና አዛዡ ከሄዝቦላህ ጋር ግንኙነት ስለነበረው ነው ተባለ።

በዚህን ጊዜ በሊባኖስ ማዕከላዊ መንግሥት እና በሄዝቦላህ መካከል ትልቅ ፍጥጫ ተፈጠረ።

ይህን የሊባኖስ መንግሥትን እርምጃ ተከትሎ ታዲያ ሄዝቦላህ ተቆጣ። ቁጣውን የገለጸው አቅሙን በማሳየት ነበር። ዋና ከተማዋን ቤይሩትን በከፊል እስከመቆጣጠር ደርሶ ነበር።

ይህ ብቻም ሳይሆን በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የሱኒ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ ገብቶ 81 ሰዎች ተገድለዋል።

ብቻ በአጭሩ ሊባኖስ ሌላ ዙር የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ለመግባት ጫፍ ደርሳ ነው ነገሩ የበረደው።

ከዚህ ክስተት በኋላ ነበር ማዕከላዊ መንግሥቱ ሸብረክ ብሎ በካቢኔ ውስጥ ለሄዝቦላህ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት የሰጠው።

በ2009 (እአአ) በተደረገው ምርጫ ሄዝቦላህ በፓርላማው 10 መቀመጫዎችን አሸንፎ በጥምር መንግሥቱ ውስጥ ቦታ ያዘ።

በዚያው ዓመት የሄዝቦላህ ዋና ፀሐፊ ሼክ ሐሰን ነስረላህ አዲስ የፖለቲካ ማኒፌስቶ ይፋ አደረጉ።

በ2011 (እአአ) በሳዑዲ አረቢያ ይደገፈው የነበረው ሳአድ ሐሪሪ ይመሩት የነበረው የሊባኖስ ማዕከላዊ መንግሥት ሲፈርስ ሄዝቦላህ ራሱን አገለለ።

ምክንያቱም አራት አባላቱ በፕሬዝዳንት ሐሪሪ አባት ፕሬዝዳንት ራፊቅ ሐሪሪ ግድያ ክስ ተመሥርቶባቸው ስለነበረ ነው።

በ2020 (እአአ) የሄዝቦላህ አንድ አባል በራፊቅ ሐሪሪ ግድያ ጥፋተኛ ተብሎ በሌለበት ዕድሜ ይፍታህ ተፈረደበት።

ይህን ፍርድ የሰጠው ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት የሚታገዘው ልዩ የፍርድ ሸንጎ ነበር።

ሄዝቦላህ በስደት የሚኖሩ እና ከፍተኛ ሃብት ያካበቱ አባላቱ በአሜሪካ፣ በአውስትራሊያ እና በአውሮፓ እንዳሉት ይጠረጠራል። ከዳያስፖራ የሚያገኘው እርዳታ ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ፈጥሮለታል።

ከሰሞኑ በመካከለኛው ምሥራቅ እየሆነ ባለው ነገር ሄዝቦላህ ጠቅልሎ ተሳትፎ ካደረገ እና እስራኤል ከፍተኛ ወታደራዊ እርምጃ ከከፈተችበት ምናልባት ይህ ነገር ኢራንን ጎትቶ ወደ ግጭቱ እንዳያስገባት ስጋት አለ።