የወጣቶች የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም

ከ 5 ሰአት በፊት

ከኮቪድ ወረርሽኝ ወዲህ በወጣቶች ዘንድ “አደገኛ” የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ወሳን የተባለ አንድ ዓለም አቀፍ ጥናት አመለከተ።

ተመራማሪዎች በ44 አገራት ውስጥ የሚገኙ 11፣ 13 እና 15 ዓመት የሆናቸው ወደ 280 ሺህ የሚጠጉ ሕጻናት ላይ ጥናት ካደረጉ በኋላ መደምደሚያ ላይ መድረሳቸው ታውቋል።

እአአ በ2022 በአማካይ 11 በመቶ ታዳጊዎች ከማኅበራዊ ሚዲያ ጋር በተያያዘ ችግር በሚፈጥር መልኩ ተጠምደዋል ሲል ለትምህርት በደረሱ ልጆች ላይ በማተኮር የተሰራው (ዘ ሄልዝ ቢሄቪየር ኢን ስኩል-ኤጅድ ቺልድረን – ኤችቢኤስሲ) ጥናት አመልክቷል።

ይህ እየጨመረ መሆኑን ጥናቱ ደረሰበት የልጆች እና የማኅበራኢ ሚዲያ ቁርኝት ቁጥር እአአ በ2018 ሰባት በመቶ ነበር።

በጥናቱ ላይ እንደታየው እንግሊዝ፣ ስኮትላንድ እና ዌልስ ከአማካይ በላይ የሆነ ቁጥር አስመዝግበዋል።

“የዲጂታል ቴክኖሎጂ በአውሮፓ ወጣቶች አዕምሯዊ ጤንነት እና ደኅንነት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ስጋትን ይፈጥራል” ሲሉ የሪፖርቱ አዘጋጆች ገልጸዋል።

በጥናቱ ከተገኘው ውጤት በመነሳት “ጤናማ የበይነ መረብ አጠቃቀምን ለማስተዋወቅ” ተጨማሪ እርምጃ ያስፈልጋል ብለዋል።

“ችግር ያለበት አጠቃቀም በ13 ዓመት ታዳጊዎች ላይ በጣም የተለመደ ነው። ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ችግር ያለበትን የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሁኔታን ሪፖርት የማድረግ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው” ሲሉ የጥናቱ ዓለም አቀፍ አስተባባሪ እና የግላስጎው ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ጆ ኢንችሌይ ገልጸዋል።

ወጣቶች በበይ መረብ ላይ ምን ያህል ጊዜ እንደሚያጠፉ በጥናቱ መገለጹንም ተናግረዋል።

“በጥናቱ ውስጥ በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙት ወጣቶች መካከል ከአንድ ሦስተኛ የሚበልጡት ከጓደኞቻቸው እና ከሌሎች ጋር ተከታታይነት ያለው የበይነ መረብ ግንኙነት ማድረጋቸውን ሪፖርት አድርገዋል” ብለዋል።

“ይህ ማለትም ቀኑን ሙሉ ከጓደኞቻቸው እና ከሌሎች ሰዎች ጋር በበይነ መረብ ይገናኛሉ ማለት ይቻላል።”

በተጨማሪም ታዳጊዎች በበይነ መረብ ላይ የሚያሳልፉት ጊዜ በሙሉ ጎጂ ነው ብሎ መደምደም አይቻልም ሲልም ሪፖርቱ ገልጿል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከፍተኛ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ኖሯቸው ችግር የሌለባቸው ታዳጊዎች፤ ከእኩዮቻቸው ከሚያገኙት ድጋፍ በተጨማሪ ማኅበራዊ ግንኙነታቸውን ማጠናከሩን ገልጸዋል።

እየጨመረ የመጣው ስጋት

እንደጥናቱ ከሆነ “ችግር ላለባቸው” ጥቂት የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ሱስ ከሚመስሉ ምልክቶች ጋር የተቆራኘ ተጽዕኖ እንዳለባቸው ታይቷል። እነዚህም፡

“ችግር ያለበት የጌም አጨዋወትን” በተመለከተ ደግሞ ከሴቶች ይልቅ ወንዶችን ይመለከታል በሚል ስጋቱን አስቀምጧል።

ከእነዚህ ውስጥ 15 በመቶ ያህሉ በእንግሊዝ የሚገኙ ናቸው። ይህም ጥናቱ ከተደረገባቸው አገራት በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ አድርጓታል።

በየቀኑ ጌም የሚጫወቱት ወንዶች አማካይ 46 በመቶ ሲሆኑ፣ ይህ አሃዝ በእንግሊዝ 52 በመቶ እና በስኮትላንድ 57 በመቶ ደርሷል።

በእንግሊዝ ያሉ የ13 ዓመት ወንዶች ለረዥም ሰዓታት ጌም በመጫወት ትልቁን ቁጥር ይዘዋል። ከእነዚህ ወንዶች መካከል 45 በመቶ ያህሉ ጌም በሚጫወቱበት ቀን ቢያንስ ለአራት ሰዓታት እንደተጫወቱ ታውቋል።

አዎንታዊ እና አሉታዊ ውጤቶች

ጥናቱ በዓለም ጤና ድርጅት የአውሮፓ ክንፍ የታተመ ነው።

በዓለም ጤና ድርጅት የአውሮፓ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ሃንስ ሄንሪ ፒ ክሉዥ እንደተናገሩት ማኅበራዊ ሚዲያ በወጣቶች ላይ አዎንታዊ እና አሉታዊ ውጤቶችን እንደሚያስከትል ግኝቱ ግልጽ አድርጓል ብለዋል።

ወጣቶች በበይነ መረብ አጠቃቀማቸው ላይ ጤናማ አካሄድ እንዲኖራቸው ለማድረግ ከፍተኛ “የዲጂታል አጠቃቀም ትምህርት” ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ መንግሥታት፣ ጤና ባለሙያዎች፣ መምህራን እና ወላጆች የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባልም ብለዋል።

“ወደ ድብርት፣ ጭንቀት እና ደካማ የትምህርት ውጤት እንዳያመራ ታዳጊዎች የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማቸው ሊጎዳ የሚችልበትን አቅጣጫ እንዲቀይሩ ለመርዳት አፋጣኝ እና ቀጣይነት ያለው እርምጃ እንደሚያስፈልገን ግልጽ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

በሳይካትሪ፣ ሳይኮሎጂ እና ኒውሮሳይንስ ተቋም የሕክምና ስታትስቲክስ ፕሮፌሰር የሆኑት ቤን ካርተር በበኩላቸው ሪፖርቱ “ጠቃሚ ማስረጃ” ሲሉ ገልጸውታል።

መረጃ አሰባሰብ ፈታኝ መሆኑን በማንሳት “ችግር ያለበት ማኅበራዊ ሚዲያ” ምንድነው በሚለው ትርጓሜ ላይ ለመስማማት አስቸጋሪ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሆኖም ጥናቱ “በማስረጃነት ትክክለኛ አስተዋጽኦ” ይኖረዋል ብለዋል።