ኤንጅላ እና ሟቹ ልጇ ብሬት
የምስሉ መግለጫ,ኤንጅላ ወንድ ልጇ ብሬትን አጥታለች

ከ 5 ሰአት በፊት

በዩናይትድ ኪንግደም ራስን ማጥፋት በሚያበረታታ አንድ ድረ-ገፅ ላይ አብረዋቸው ይህን ድርጊት የሚፈፅሙ ተጣማሪዎችን የፈልጉ ከ700 በላይ እንዳሉ ቢቢሲ ያካሄደው ምርመራ አመለከተ።

ቢቢሲ ስሙን የማይጠቅሰው ይህንን ድረ-ገፅ መጎብኘት የሚችሉት አባላት ብቻ ሲሆኑ፣ አባላቱ እራሳቸውን ለማጥፋት የተነሱ እና በዚህም እንደ እነሱ አብረዋቸው ለመሞት የሚሹ ተጣማሪዎችን የሚያፈላልጉበት የበይነ መረብ መድረክ ነው።

የቢቢሲ የምርመራ ዘገባ እንደሚያሳየው በዚህ ድረ-ገፅ አማካኝነት በርካታ ሰዎች አጣማሪ ከማግኘታቸውም በተጨማሪ አንዳንድ ሰዎች ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን ለማጥመድ እየተጠቀሙበትም ይገኛል።

በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 2019 የ28 ዓመቱ የኤንጅላ ስቲቨንስ ወንድ ልጅ ብሬት አንዲት እራስን የማጥፋት አጣማሪ ለማግኘት በሚል ወደ ስኮትላንድ ይጓዛል።

ሁለቱ ግለሰቦች በኤይርቢኤንድቢ (ሰዎች ቤታቸውን ለእንግዳ የሚያከራዩበት ድረ-ገፅ) ቤት ተከራይተው ራሳቸውን ያጠፋሉ።

“ብሬት ሁሌም ይናፍቀኛል። ፈገግታው ይናፍቀኛል። ሳቁ የሚጋባ ነበር” ትላለች ልጇ በዚሁ የበይነ መረብ ገጽ አማካኝነት ከተዋወቃት ሴት ጋር እራሱን ያጠፋው ብሬት እናት ኤንጅላ።

ከልጇ ሞት በኋላ ለበርካታ ዓመታት ይህ ራስን ማጥፋትን የሚያበረታታውን ድረ-ገፅ በማፈላለግ ብዙ ደክማለች። በተለይ ደግሞ አጣማሪ የሚያፈላልገውን ድረ-ገፅ ለማግኘት ነው ብዙ ሙከራ ያደረገችው።

“በጣም አስፈሪ ቦታ ነው” የምትለው ኤንጅላ ድረ-ገፁ የፍቅር ጓደኛ ማፈላለጊያዎች መተግበሪያዎች ዓይነት ሆኖ ግን ለክፉ ተግባር የሚውል እንደሆነ ታስረዳለች።

“እንዴት ነው አንድ ሰው ራሱን የሚያጠፋ አጣማሪ የሚያፈላልገው? በጣም ጨለማ የሆነ ሥፍራ ነው” ትላለች።

ይህ ድረ-ገፅ ሰዎች አጣማሪ ፈልገው ራሳቸውን እንዲያጠፉ ያበረታታል። ይህን እንዴት ማድረግ እንዳለባቸውም መመሪያ ያስቀምጣል።

የቢቢሲ የምርመራ ዘገባ እንደሚያሳየው ከዓለም ዙሪያ ከ5 ሺህ በላይ ሰዎች በዚህ ድረ-ገፅ ላይ መልዕክታቸውን አስፍረዋል። ቢቢሲ የድረ-ገፁን ስምም ሆነ የሚያስቀምጠውን መመሪያ አያጋራም።

ባለፈው ዓመት መጋቢት በተደረገው ምርመራ ውጤት መሠረት ከ130 በላይ ብሪታኒያውያን በድረ-ገፁ አማካይነት አንድ ኬሚካል ተጠቅመው ራሳቸውን ሳያጠፉ አይቀሩም።

ኤንጅላ የልጇ ብሬትን ፎቶ ይዛ

ቢቢሲ በሽፋን ስም በፈጠረው አካውንት አማካኝነት ባጣራው መረጃ ድረ-ገፁ ላይ የሚወጡ መልዕክቶችን መመርመር ችሏል።

የድረ-ገፁ አባላት ዕድሜያቸውን፣ ፆታቸውን፣ አድራሻቸውን እና እንዴት መሞት እንደሚፈልጉ ይጽፋሉ። ይህን የሚያደርጉት አብረዋቸው እራሳቸውን በማጥፋት መሞት የሚፈልጉ ሰው ለማፈላለግ ነው።

የሄለን ካይት እህት ሊንዳ በአውሮፓውያን 2023 ነው እዚህ ድረ-ገፅ ላይ ማስታወቂያ የለቀቀችው።

“በምስኪን ነብሳት ላይ የሚጫወት ገፅ ነው” ትላለች ሄለን። “አጣማሪ የሚያፈላለገው የድረ-ገፁ ክፍል ሰዎችን ወደ ሞት የሚመራ ነው።”

“ዕድሜዬ 54 ነው። ሴት ነኝ። ለንደን አካባቢ ነው የምኖረው” ስትል ነው ሊንዳ የፃፈችው። “ተጉዤ መምጣት ችላለሁ። አስፈላጊ ከሆነ የሆቴል መክፈል እችላለሁ። ነገር ግን መጀመሪያ ብናወራ ደስ ይለኛል” ስትል ታክላለች።

ሊንዳ በድረ-ገፁ አማካይነት አንድ ወንድ ከተዋወቀች በኋላ በምሥራቅ ለንድ ራምፈርድ አካባቢ ካለ አንድ ሆቴል ተገናኙ።

በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 1/2023 በተገናኙበት ሆቴል መርዛማ ኬሚካል ጠጥተው አብረው ሞቱ።

ሄለን እንደምትለው እህቷ ሊንዳ “ከአንድ እንግዳ ግለሰብ አጠገብ ነው አስከሬኗ የተገኘው።”

እሷ እንደምትለው “እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ንፁሃን ሰዎች” ናቸው በየቀኑ በድረ-ገፁ አማካይነት ራሳቸውን እያጠፉ ያሉት። “ባለሥልጣናት ይህን ማስቆም አልቻሉም” በማለት ትወቀሳለች።

የሄለን ሐዘን በዚህ ብቻ አላበቃም።

መስከረም 2023 የሄለን ሌላኛዋ እህቷ ሳራህ በሊንዳ ሞት ምክንያት የከፋ ሐዘን ውስጥ ገባች። እሷም ወደ ድረ-ገፁ ሄዳ መርዛማ ኬሚካል በመጠቀም ራሷን አጠፋች።

ሮቤርታ ባርቦስ
የምስሉ መግለጫ,ሮቤርታ ድረ-ገፁን በሚጠቀሙ አዳኞች ዒላማ ተደርጋለች

አዳኞች

ቢቢሲ ራስን ለማጥፋት አጣማሪ የሚያገናኘውን ድረ-ገፅ በሚመረምርበት ወቅት ነው ሌላ አሰቃቂ ድርጊት ያስተዋለው።

ድረ-ገፁ፤ አጥማጆች ተጋላጭ እና ራሳቸውን ማጥፋት የሚፈልጉ በተለይ ሴቶችን እያሰሱ የሚያገኙበትም መድረክ ሆኗል።

በ2022 በግላስጎው ፍርድ ቤት የክስ መዝገብ ላይ እንደተመለከተው ክሬግ ማክኢናሊ የተባለው የ31 ዓመት ግለሰብ እዚህ ድረ-ገፅ ላይ ገብቶ ለበርካታ ሰዎች መልዕክት ሥር ምላሽ ይሰጣል።

ከተጠቃሚዎቹ መካከል አንዲት ተጋላጭ የ25 ዓመት ሴት አጥምዶ ወደ ቤቱ መጥታ

“ራስን ማጥፋት እንድትለማመድ” ይጋብዛታል።

ሰውዬው ይህችን ሴት ወደ ቤቱ ከጠራት በኋላ ራሷን እስክትስት ድረስ በተደጋጋሚ እንዳነቃት ችሎቱ ተመልክቷል።

ማክኢናሊ ሌሎችንም ሴቶች አጥምዶ ተመሳሳይ “ምክር እና እርዳታ” ለመስጠት በሚጠራበት ቤቱ ነው በቁጥጥር ሥር የዋለው።

ሁሉንም ያጠመዳቸውን ሴቶች ያገኛቸው በዚህ ድረ-ገፅ ላይ ነው።

ከእነዚህ መካከል አንዷ ሮማኒያዊቷ የ22 ዓመት ተማሪ ሮቤርታ ባርቦስ ናት።

ቢቢሲ በተመለከተው የመልዕክት ልውውጥ ላይ ማክኢናሊ የተባለው ግለሰብ ለሮቤርታ በላከው ፅሑፍ “አይታ የማታወቀውን ነገር እንደሚያሳያት” እና “ይህ ሁሉ ሲሆን አብሯት ለመሆን” ቃል ገብቶላታል።

ሮቤርታ ይህን ግለሰብ አንድ ጊዜ ካገኘችው በኋላ ድጋሚ ልታገኘው እንደማትፈልግ አሳወቀችው። ነገር ግን የካቲት 2020 ብቻዋን ባለችበት ራሷን አጠፋች።

“ከአንድ አሰቃቂ ፊልም የተወሰደ ዓይነት ነው። ታይቶ የማይታወቅ ነገር ነው” ትላለች የሮቤርታ እናት ማሪያ ባርቦስ። “እንዲህ ዓይነት ድረ-ገፅ መኖሩን ራሱን ማመን አልችልም። በሽተኛ አእምሮ ያላቸው ሰዎች ናቸው ይህን ያዘጋጁት።”

ማክኢናሊ ስኮትላንድ ውስጥ ፍርድ የተሰጠው ሲሆን፣ ከሞት ብይን ዝቅ ብሎ ወሲባዊ እና አሰቃቂ ወንጀል ለሚፈፅሙ የሚሰጠው “ኦርደር ኦፍ ላይፍሎንግ ሪስትሪክሽን” ተፈርዶበታል።

በዚህ መሠረት ቢያንስ ለሁለት ዓመታት እስር ቤት የሚቆይ ሲሆን፣ ከወጣ በኋላ ደግሞ እስኪሞት ድረስ ቁጥጥር ይደርግበታል።

የሮቤርታ እናት ማሪያ
የምስሉ መግለጫ,የሮቤርታ እናት ማሪያ ድረ-ገፁ መኖሩን ማመን አቅቷታል

የቢቢሲ ዘገባ እንደሚያሳየው ባለፉት ሁለት ዓመታት የድረ-ገፁ ተጠቃሚ የሆኑ አንዳንድ ሰዎች አጣማሪ ፍለጋ አገራቸውን ለቀው ሄደዋል።

ለምሳሌ ሁለት ጊዜ የድረ-ገፁ ተጠቃሚ የሆኑ ወንዶች ተጋላጭ እና ወጣት የሆኑ ሴቶች ራሳቸውን እንዲያጠፉ “ለማገዝ” ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም መጥተዋል።

ከእነዚህ መካከል አንዱ ከአሜሪካዋ ሚኒሶታ ግዛት የመጣ ሲሆን፣ ሆቴል ተቀምጦ ድረ-ገፁ ላይ የተዋወቃትን አንዲት የ21 ዓመት ወጣት ሴትን አግኝቷታል።

ሁለቱ ግለሰቦች ለ11 ቀናት ያህል ሆቴል ውስጥ ከከረሙ በኋላ ወጣቷ ሴት መርዛማ የሆኑ ኬሚካል በመጠቀም ራሷን አጥፍታለች።

ግለሰቡ ወጣቷ ሴት ራሷን ስታጠፋ እሱ ተኝቶ እንደነበር እና ነቅቶ የሆነውን ሲመለከት እርዳታ እንደጠራ ይናገራል። ሰውዬው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ ቢደርግበትም በኋላ ላይ በነፃ ተለቆ ከአገር እንዲወጣ ተፈቅዶለታል።

በሁለተኛው ክስተት ደግሞ አንድ የፍሎሪዳ ነዋሪ የሆነ ሰው ድረ-ገፁ ላይ ያገኛቸውን አራት ሰዎች በአካል ለማግኘት ያመቻቻል። ከእነዚህ መካከል አንዷ ዩናይትድ ኪንግደም ነው የምትገኘው።

ቢቢሲ በምርመራው ባጣራው መሠረት ግለሰቡ አሜሪካ ውስጥ ላገኛት ሴት ራሷን እንድታጠፋ ሽጉጥ ቢሰጣትም ይህን ከማድረጓ በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውላለች።

ግለሰቡ ወደ ለንደን መጥቶ አንዲት ወጣት ብሪታኒያዊትን ሆቴል ውስጥ እንዳገኛትም አምኗል። እህች ሴት ማን እንደሆነች እና ምን እንዳጋጠማት የሚታወቅ ነገር የለም።

ግለሰቡ ምንም ዓይነት ክስ አልቀረበበትም።

ምን ማድረግ ይሻላል?

የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ወግ አጥባቂ መንግሥት በ2023 የበይነ መረብ ደኅንነትን የተመለከተ ሕግ ማውጣቱ ይታወሳል። አዲሱ የሌበር ፓርቲ መንግሥት ይህን ሕግ ተከትሎ “በበይነ መረብ አደጋ የሚያደርሱ ድሮች ላይ እርምጃ ለመውሰድ” ቃል ገብቷል።

‘ሳማሪታንስ’ የተሰኘው ድርጅት ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ጁሊ ቤንትሊ “ሕጉ ሰዎችን ከጉዳት ሊታደግ የሚችለው ጥርስ ሲኖረው ነው” ይላሉ።

ኦፍኮም የተሰኘው እና በበይነ-መረብ እና በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ መልዕክቶችን የሚከታተለው አካል ከአገሪቱ መንግሥት ተቋማት ጋር በመሆን ሕጉን ተፈፃሚ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

ኦፍኮም የቢቢሲን ምርመራ ተከትሎ የድረ-ገፁን ባለቤቶች ለማግኘት ቢሞክርም የበይነ መረብ መድረኩ ትንሽ ስለሆነ እና መቀመጫውን አሜሪካ ስላደረገ እርምጃ ለመውሰድ “ከባድ እንደሆነ” ይናገራል።

ነገር ግን ቢቢሲ ባደረገው ምርመራ ድረ-ገፁን ከሚያስተዳድሩ ሰዎች መካከል አንዷ ምዕራብ ለንድ የምትገኝ ሴት መሆኗን ደርሶበታል።

የአፎኮም ሥራ አስኪያጅ ሜላኒ ዶውስ “ድረ-ገፁን አግኝተን ይህ ሕጋዊ አይደለም፤ ራስን ማጥፋት ማበረታት በሕግ ያስቀጣል ስንላቸው ለሆነ ጊዜ ያክል ዩኬ ውስጥ መሥራት አቁመው ነበር። ነገር ግን አሁን ተመልሰው መጥተዋል” ይላሉ።

ሐዘን ላይ ያሉ ቤተሰቦች ድረ-ገፁ ራስን ማጥፋት እያበረታታ ነው፤ ይህ ድርጊት ደግሞ በበይነ-መረብም ይሁን አይሁን ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ውስጥ የሚያስቀጣ ነው ይላሉ።