ፑቲን

ከ 4 ሰአት በፊት

ሩሲያ የኑክሌር ጦር መሳሪያዋን የምትጠቀምበትን ሕግና ቅድመ ሁኔታ ልትቀይር እንደምትችል ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አስታወቁ።

በዚህም ወዳጅ የሆነ የኑክሌር ጦር መሳሪያ የሌለው አገር ኑክሌር በታጣቀ ሌላ አገር ድጋፍ ጥቃት ቢፈጸምበት የሁለቱ ወዳጅ አገራት “የጋራ ጥቃት” ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ገለጹ።

ይህ ንግግር በዩክሬን ጦርነት ኑክሌር ለመጠቀም እንደ ማስፈራሪያ ነው ተብሏል።

ዩክሬን ኑክሌር ባይኖራትም ከአሜሪካና ከሌሎችም ኑክሌር ያላቸው አገራት የመሣሪያ ድጋፍ ታገኛለች።

ዩክሬን ከሩሲያ ጋር እያካሄደችው ባለው ጦርነት የምዕራባውያንን ረዥም ርቀት መሣሪያ ለመጠቀም ፈቃድ እየጠየቀች ነው።

ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በዚህ ሳምንት አሜሪካ ተጉዘዋል። ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር እንደሚገናኙ ይጠበቃል።

በውይይታቸው ዩክሬን የረዥም ርቀት የጦር መሣሪያ ለመጠቀም ፈቃድ እንደምትጠይቅ ይታመናል።

ዩክሬን ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ ወደ ሩሲያ ግዛት ዘልቃ ገብታለች። ወደ ዩክሬን ሚሳዔሎች ይተኮሱባቸዋል ያለቻቸውን የሩሲያ ወታደራዊ ማዕከላትን መምታትም ትፈልጋለች።

ፑቲን ያደረጉትን ንግግር ተከትሎ የዜሌስኪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ አንድሪ ያምራክ፣ “ሩሲያ በኑክሌር ዓለምን ከማስፈራራት ውጪ አማራጭ የላትም” ብለዋል።

ፑቲን ከዚህ ቀደም ኑክሌር ለመጠቀም አስፈራርተዋል።

ዩክሬን ግን የፑቲን ማስፈራሪያ የዩክሬን አጋሮች ድጋፍ እንዳይሰጡ ለማድረግ ያለመ ነው ስትል ተችታለች።

ቻይና ነገሮች እንዲረጋጉ አሳስባለች። ፕሬዝዳንት ዢ ዢፒንግ ፑቲን ኑክሌር እንዳይጠቀሙ አስጠንቅቀዋል።

ፑቲን ከፀጥታ ክፍላቸው ጋር ከተወያዩ በኋላ ውሳኔውን አሳውቀዋል።

“አዲሱ አካሄድ ሩሲያ የኑክሌር መሣሪያ እንድትጠቀም ያስገድዳል” ብለዋል። አዲስ አካሄድ ያሉት ወደ ሞስኮ የሚቃጣ የሚሳዔል ጥቃትን ነው።

ወደ ሩሲያ ግዛት ሚሳዔል ከገባ ወይም ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት ከተሰነዘረ ለአገሪቱ ሉዓላዊነት ስለሚያሰጋ አማራጩን ሩሲያ እንደምትወስድ ገልጸዋል።

“ኑክሌር የሌለው አገር ኑክሌር ባለው አገር ተሳትፎ ጥቃት ከፈጸመ የጋራ ጥቃት ሩሲያ ላይ እንደከፈቱ ይቆጠራል። ኒውክሌር የዜጎቻችን ደኅንነት ማስጠበቂያ ቀዳሚ አማራጭ ነው” ብለዋል።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ኑክሌር ታጣቂ አገራት ኑክሌር በጦርነት ጥቅም ላይ ቢውል በሁለቱም ወገን ያሉ ተዋጊ ኃይሎችን የሚያወድም ስምምነት አድርገዋል።

ነገር ግን አጠቃላይ ውድመትን ሳያስከትሉ ዒላማ የሚመቱ የኑክሌር መሣሪያዎች ግን አሉ።

ባለፈው ሰኔ ፑቲን ዩክሬንን የሚደግፉ የአውሮፓ አገራትን አስጠንቅቀዋል።

ሩሲያ “ብዙ ታክቲካል የኑክሌር መሣሪያዎች አሏት” ብለዋል።