በሊባኖስ የደረሰው ጥቃት

ከ 4 ሰአት በፊት

በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል ያለው ጦርነት መባባሱን ተከትሎ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎች አጋሮቻቸው በሊባኖስ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ።

12 አገራት “ለዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ዕድል ለመስጠት” እና በጋዛ የተኩስ አቁም ለማድረግ እንዲያስችል ለ21 ቀናት አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ሃሳብ አቅርቧል።

አገራቱ በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ ጦርነቱ የእስራኤልንም ሆነ የሊባኖስን ሕዝብ የማይጠቅም ከመሆን ባለፈ “ተቀባይነት በሌለው መልኩ በቀጣናው የመስፋፋት አደጋ ይኖረዋል” ብለዋል።

ሃሳቡ የቀረበው ሊባኖስ ውስጥ ሄዝቦላህ ላይ ያነጣጠረው ሰፊ የአየር ድብደባ “ወደ ጠላት ግዛት ለመግባት” መንገድ ሊከፍት ይችላል ሲሉ አንድ የእስራኤል ወታደራዊ አዛዥ ረቡዕ ዕለት ለወታደሮቻቸው ከተናገሩ በኋላ ነው።

የሌተና ጄኔራል ሃሌቪ አስተያየት የእስራኤል ጦር ወደ ሊባኖስ የምድር ጦር ሊገባ እንደሚችል ከአንድ ከፍተኛ ባለስልጣን እስካሁን በግልጽ የተሰጠ ማሳያ ተደርጓል።

የጋራ መግለጫውን የተፈረሙት አሜሪካ፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ አውሮፓ ህብረት፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ፣ እንግሊዝ እና ኳታር ናቸው።

ይህ የተገለጸው በኒው ዮርክ የተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የመሪዎች ስብሰባን ተከትሎ ነው።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሁለቱ ለብቻቸው በጋራ በሰጡት መግለጫ “ሠላማዊ ዜጎች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ሠላም እና ደህንነትን የማረጋግጥ” ጊዜው አሁን ነው ብለዋል።

አሁን ያለው ግጭት “ይበልጥ ሰፋ ያለ ግጭት እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ያስከትላል” ሲሉ ገልጸዋል።

“ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ እንዲሳካ ዕድል ለመስጠት እና በድንበር አካባቢ ተጨማሪ ግጭቶችን ለማስወገድ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ጥሪ ለማድረግ ባለፉት ቀናት በጋራ ሠርተናል።”

ፕሬዝዳንት ባይደን ረቡዕ አመሻሽ ላይ በዋይት ሃውስ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው አጭር ቆይታ “ከአውሮፓ እና ከአረብ ሀገራት ከፍተኛ ድጋፍ አለ። ጦርነቱ እንዳይሰፋፋ ይህ አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ምንም እንኳን አሜሪካ ከሁለቱም መንግስታት ጋር ግንኙነት ብታደርግም እስራኤልም ሆነች ሊባኖስ ሃሳቡን አልተቀበሉም። ኦፊሴላዊ ምላሾች በሰዓታት ውስጥ ይጠበቃሉም ተብሏል።

ኃላፊው አክለውም ለ21 ቀናት ግጭቱን ማቆም “ስምምነት” ላይ ለመድረስ ከማገዝ በተጨማሪ “ሁሉን አቀፍ ስምምነት” ለመድረስ የሚያስችል ይሆናል ብለዋል።

አሜሪካ ከሄዝቦላህ ይልቅ ከሊባኖስ መንግስት ጋር እየተደራደረች ነው ሲሉም አክለዋል። ቀጣዩ እና “መንግስታዊ ካልሆኑ ተዋናዮች” ጋር የመነጋገሩ ኃላፊነት የሊባኖስ መንግስት ይሆናል።

የሊባኖሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ሚካቲ በበኩላቸው አገራቸው "በጠላት እስራኤል አረመኔያዊ ድርጊት ሉዓላዊነታችን እና የሰብአዊ መብቶቻችን ላይ ግልጽ የሆነ ጥሰት እየደረሰባት ነው" ብለዋል

ቀደም ሲል ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ አፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲደረግ አሳስበዋል። ካልሆነ ግን “ሁሉም ነገር ገሃነም ይሆናል” ብለዋል።

የሊባኖሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ሚካቲ በበኩላቸው አገራቸው “በጠላት እስራኤል አረመኔያዊ ድርጊት ሉዓላዊነታችን እና የሰብአዊ መብቶቻችን ላይ ግልጽ የሆነ ጥሰት እየደረሰባት ነው” ብለዋል።

አክለውም ከተባበሩት መንግስታት ስብሰባ ሲወጡ “እስራኤል ላይ በሁሉም ረገድ አፋጣኝ የተኩስ አቁም እንድታመጣ” ጫና የሚያደርግ “ጠንካራ መፍትሔ” እንደሚኖር ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።

በቅርቡ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ ይቻል እንደሆነ ከሮይተርስ ለቀረበላቸው ጥያቄም “አዎ ተስፋ እናደርጋለን” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእስራኤል ልዑክ ዳኒ ዳነን ቀደም ብለው እንደተናገሩት ግጭቱ እንዳይስፋፋ የሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን አመስግነው ዓላማችንን ለማሳካት ግን “በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ሁሉንም መንገዶች እንጠቀማለን” ብለዋል።

እስራኤል “ሁሉን አቀፍ ጦርነትን እንደማትፈልግ” እና የሠላም ፍላጎቷን “ግልጽ” አድርጋለች ሲሉ ተናግረዋል።

ዳነን አክለውም የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሐሙስ ኒው ዮርክ እንደሚገቡ እና በዚያኑ ቀንም የሁለትዮሽ ስብሰባ እንደሚያደርጉ ገልጸው፤ በማግስቱ ጠዋት በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ንግግር እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

እአአ በ2006 ለመጨረሻ ጊዜ ጦርነት ካካሄዱ ወዲህ እስራኤል በሄዝቦላህ የተገነቡ መሠረተ ልማቶችን ለማጥፋት ከፍተኛ የአየር ዘመቻ የጀመረች ሲሆን ሊባኖስ ውስጥ ከ600 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።

ሊባኖስ ውስጥ አዲስ ተፈናቀሉትን 90 ሺህ ሰዎች ጨምሮ ከግጭቱ መባባስ በፊት ቤታቸውን ለቀው የወጡ 110 ሺህ በላይ ሰዎች እንደነበሩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል። ወደ 40 ሺህ የሚጠጉት በመላ አገሪቱ በሚገኙ መጠለያዎች ውስጥ ይኖራሉ።

በጋዛ ጦርነት ምክንያት በተቀሰቀሰው የድንበር ዘለል ጥቃት ለአንድ ዓመት ገደማ የቀጠለ ሲሆን በሰሜን እስራኤል 70 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን አፈናቅሏል። የእስራኤል መንግስት እና ጦር ነዋሪዎቹን በሠላም ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ እንፈልጋለን ብለዋል።

ሄዝቦላህ የፍልስጤም አጋሩ የሆነውን ሃሐማስን በመደገፍ እስራኤል ላይ የሚፈጽመው ጥቃት የሚያበቃው በጋዛ የተኩስ አቁም ሲደረስ ብቻ ነው ብሏል። ሁለቱም ቡድኖች በኢራን የሚደገፉ ሲሆን በእስራኤል፣ በእንግሊዝ እና በሌሎች አገራት በአሸባሪነት ተፈርጀዋል።

ረቡዕ ዕለትም በቀጠለው ድንበር ዘለል ውጊያ ሄዝቦላህ የእስራኤሉን ስልላ ተቋም የሞሳድ ዋና መስሪያ ቤት በሚሳኤል ዒላማ ማደረጉን ገልጿል። ሄዝቦላህ ብዙ ህዝብ የሚኖርበትን ቴል አቪቭን ዒላማው ሲያደርግ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜው ነው።

ጥቃቱ በአየር መከላከያዎች የተቋረጠ ሲሆን ምንም ያደረሰው ጉዳት የለም ተብሏል።

ሄዝቦላህ በደርዘን የሚቆጠሩ ተጨማሪ ሮኬቶችን ወደ ሰሜን እስራኤል መተኮስ ሁለት ሰዎችን አቁስሏል።

የሊባኖስ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ፍራስ አቢያድ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት በጥቃቱ ቢያንስ 51 ሰዎች ሲገደሉ 223 ቆስለዋል ቢሉም ምን ያህሉ ሲቪሎች እና ተዋጊዎች እንደሆኑ አልገለጹም።

ባለፈው ሳምንት ሊባኖስ ውስጥ በሁለት አጋጣሚዎች የሄዝቦላህ አባላት ለመግባባት የሚጠቀሙባቸው ፔጀሮች እና ዎኪ ቶኪዎች ፈንድተው 39 ሰዎች ሲሞቱ በሺህዎች የሚቆጠሩት ቆስለዋል። ከጥቃቱ ጀርባ የእስራኤል እጅ እንዳለበት በሰፊው ይታመናል።

በደቡባዊ ቤይሩት በሚገኘው የቡድኑ ጠንካራ ይዞታ በሆነው በዳሂህ ላይ እስራኤል አርብ ዕለት በፈጸመችው የአየር ጥቃት ሄዝቦላህ የሚተማመንበት ራድዋን ፎርስ የተሰኘው ዋና ተዋጊ ቡድን የእዝ ሰንሰለት ተበጣጥሷል።

ከተገደሉት 55 ሰዎች መካከል አንዱ ኢብራሂም አቂል የተባሉት ከፍተኛ ወታደራዊ መሪው መሆናቸውን ቡድኑ አረጋግጧል።