አደጋ የደረሰበት የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ

ከ 49 ደቂቃዎች በፊት

ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን ተነስቶ ወደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ ዞን ሲጓዝ በነበረ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ በደረሰ አደጋ የሁለት ሕጻናትን ጨምሮ 28 ሰዎች ሕይወታቸው አለፈ።

የመኪናውን አሽከርካሪ ጨምሮ 19 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው በህክምና ላይ መሆናቸውን የወላይታ ዞን ፖሊስ መምሪያ ገልጿል።

ትናንት ረቡዕ መስከረም 16/2016 ዓ.ም. ከሶዶ ከተማ የተነሳው “ኤፍ.ኤስ.አር” የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ “በአብዛኛው ለበዓል” ሲጓዙ የነበሩ ከ50 በላይ ሰዎችን ጭኖ እንደነበር የወላይታ ዞን ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ ፍሰት ቁጥጥር እና አደጋ መከላከል ዲቪዥን ኃላፊ ኢንስፔክተር ወልዴ ቢሊሶ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ተሽከርካሪው ከቀኑ ሰባት ሰዓት ገደማ አደጋው የደረሰበት በወላይታ ዞን በሚገኘው ኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ ሲደርስ መሆኑን እንደሆነም ገልጸዋል።

አደጋው የደረሰበት “ግርባ ወንዝ” ተብሎ የሚጠራው አካባቢ የሚገኘው መንገድ “ዳገታማ እና በጣም አስቸጋሪ” መሆኑን የሚያስረዱት ኢንስፔክተር ወልዴ፤ ተሽከርካሪው ዳገቱን በመውጣት ላይ እንዳለ “እንደተንሸራተተ” አብራርተዋል።

“አሁን ያለው መረጃ ተሽከርካሪው ተንሸራርቷል (ስትራፕ) [የሚል] ነው። ተሽከርካሪው ተንሸራትቶ በጣም ረጅም ርቀት ያለውን ቁልቁለት ተገለባብጦ ወንዝ ውስጥ በመግባቱ ነው አደጋው የተከሰተው” ሲሉ ሁኔታውን ገልጸዋል።

እስካሁን ባለው መረጃ መሠረትም በዚህ አደጋ 28 ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ እና 19 ሰዎች ላይ ጉዳት እንደደረሰ ኃላፊው ተናግረዋል።

ሕይወታቸው ካለፈ ሰዎች መካከል ዕድሜያቸው ከስድስት እስከ ስምንት ዓመት የተገመቱ ሁለት ሕጻናት እንደሚገኙበት ኢንስፔክተር ወልዴ አስታውቀዋል።

“ተሽከርካሪው ውስጥ ልጅ እና እናት ነበሩ። ሕጻን ልጅ ሲሞት እናትየው ተርፋ ህክምና ላይ ነች” ሲሉ ሕይወቱ ስላለፈው አንድ ሕጻን ልጅ ጠቅሰዋል።

ሌላኛው ሕጻን ልጅ ደግሞ ሲጓዝ የነበረው ከአክስቱ ጋር እንደነበር አክለዋል።

እንደ ኢንስፔክተር ወልዴ ገለጻ በተሽከርካሪው ውስጥ ተሳፍረው የነበሩት ሰዎች በአብዛኛው የዳውሮ ዞን ነዋሪዎች ሲሆኑ ሕይወታቸው ካለፈው ሰዎች መካከል የአንድ ሰው አስከሬን ወደ ሐዋሳ ተልኳል።

በአደጋው ምክንያት ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎችን ማንነት የመለየት ሥራ ረቡዕ እስከ ሌሊቱ ስምንት ሰዓት ድረስ ሲከናወን እንደነበር የዳውሮ ዞን የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከበደ ሲሳይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች አስከሬን ዛሬ [ሐሙስ] ጠዋት ወደየቤተሰቦቻቸው እንደተሸኘም አቶ ከበደ ገልጸዋል።

ገደለ ውስጥ የተገባው ተሽከርካሪ
የምስሉ መግለጫ,ዳገት ሲወጣ የነበረው የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪው፤ ከተንሸራተተ በኋላ “በጣም ረጅም ርቀት ያለውን ቁልቁለት ተገለባብጦ” ወንዝ ውስጥ መግባቱ ተገልጿል።

ከአደጋው ከተረፉት 19 ሰዎች መካከል አስራ አራቱ የደረሰባቸው ጉዳት ከባድ እንደሆነ የወላይታ ዞን ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ ፍሰት ቁጥጥር እና አደጋ መከላከል ዲቪዥን ኃላፊ ኢንስፔክተር ወልዴ ገልጸዋል።

አምስት ሰዎች ደግሞ ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው የገለጹት ኃላፊው፤ በህክምና ላይ ከሚገኙት ግለሰቦች መካከል የመኪናው አሽከርካሪ እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል።

አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች በወላይታ ዞን በሚገኙት ሶዶ ክርስቲያን እና በሌ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች እንዲሁም በዳውሮ ዞን ታርጫ ጠቅላላ ሆስፒታል እየታከሙ እንደሆነ የዳውሮ ዞን የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከበደ ተናግረዋል።

ሕይወታቸው ካለፈ እና አደጋ ከደረሰባቸው ሰዎች በተጨማሪ “ምንም ጉዳት” ሳይደርስባቸው ከአደጋው የተረፉ “ስድስት” ተሳፋሪዎች መኖራቸውን ኢንስፔክተር ወልዴ ገልጸዋል።

“ስድስት ሰዎችን በአካል አግኝተን አነጋግረናል። እኔ ጋር ባለው መረጃ በአካል ያነጋገርናቸው ስድስት የሚሆኑ ሰዎች በሰላም፣ ምንም ሳይሆኑ ከዚያ ውስጥ ወጥተዋል” ብለዋል።

በወላይታ ዞን የደረሰው ይህ አደጋ፤ በዚህ ሳምንት ወንዝ ውስጥ በገባ ተሽከርካሪ የተነሳ የሰዎች ሕይወት ያለፈበት ብቸኛው ክስተት አይደለም።

ማክሰኞ መስከረም 14/2017 ዓ.ም. ምሽት በጋምቤላ ክልል ጉዞ ላይ የነበረ “አምቡላንስ” ተሽከርካሪ ወንዝ ውስጥ በመግባቱ ሰባት ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ ሌሎች ሰባት ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ከጋምቤላ ከተማ ወደ ኑዌር ዞን ሲጓዝ የነበረው ተሽከርካሪ በጂካዎ ወረዳ አደጋው ደረሰበት “የባሮ ወንዝ ጊዜያዊ ድልድይን ጥሶ በወንዝ ውስጥ በመግባቱ” እንደሆነ የጽህፈት ቤቱ መረጃ ጠቅሷል።

በአደጋው “ወዲያኑ” ሕይወታቸው ካለፈ ሰዎች መካከል የጤና ባለሙያዎች እንደሚገኙበት ተገልጿል።