ታጣቂዎች
የምስሉ መግለጫ,የመንግስት የጸጥታ ኃይሎቹ አብዛኛዎቹን ግድያዎች የፈጸሙት “ሰዎችን ከቤታቸው አስወጥተው” መሆኑን ኢሰመኮ አስታውቋል።

ከ 48 ደቂቃዎች በፊት

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በግጭት አውድ ውስጥ በሚገኙ አካባቢዎች ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ ብቻ ከ200 በላይ ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን ይፋ አደረገ።

ኮሚሽኑ አሃዙን ይፋ ያደረገው ረቡዕ መስከረም 15/2017 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው በግጭት ዐውድ ውስጥ ያሉ አካባቢዎች የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ የሩብ ዓመት ሪፖርት ነው።

የኢሰመኮ ሪፖርት ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር እስከ መስከረም 2017 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ የሚመለከት ነው።

ሪፖርቱ በግጭት ዐውድ ውስጥ ባሉ አካባቢዎች “አሳሳቢ ሆነው የቀጠሉ” ባላቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ከእነዚህ አሳሳቢ ጉዳዮች፤ “ከሕግ ውጭ የሚፈጸም ግድያ፣ በግጭት ዐውድ እና አካባቢ የሚደርስ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመት እና ዘረፋ፣ የዘፈቀደ፣ የጅምላ እና የተራዘመ እስራት እና የተፋጠነ ፍትሕ እጦት፣ አስገድዶ መሰወር፣ እገታ፣ በመዘዋወር መብት እና በመጓጓዣ መንገዶች ላይ የሚፈጸም ሕገ-ወጥ ገደብ እና የአገር ውስጥ መፈናቀል” ናቸው።

ኮሚሽኑ ከሕግ ውጭ ግድያ፣ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመት እና ዘረፋ ተፈጽሞባቸዋል በሚል በሪፖርቱ የጠቀሳቸው አምስት ክልሎች ናቸው። ከእነዚህ ክልሎች መካከል በርካታ ሲቪል ሰዎች የተገደሉት በአማራ ክልል ነው።

በአማራ ክልል ካለፈው ሰኔ ወር ወዲህ ከግጭቱ ጋር ግንኙነት የለሌላቸው ከ130 በላይ ሲቪል ሰዎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች “በክልሉ የሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት” መገዳላቸውን አመልክቷል።

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር መጀመሪያ በክልሉ ምዕራብ ጎንደር ዞን የአገው ብሔረሰብ ተወላጆች ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች የፋኖ አባላት 23 ሲቪል ሰዎችን አፍነው የተወሰኑትን መግደላቸውን ተቋሙ ሪፖርት አድርጓል።

ከዚህ በተጨማሪ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች፤ “ፋኖን ትደግፋላች፤ ትቀልባላችሁ” በሚል እና “በበቀል ስሜት” በድምሩ “በግጭት ተሳትፎ የሌላቸው” 100 ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል።

የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎቹ አብዛኛዎቹን ግድያዎች የፈጸሙት “ሰዎችን ከቤታቸው አስወጥተው” መሆኑን ኮሚሽኑ አክሏል።

መንግሥታዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም በመንገድ እና በቤታቸው ውስጥ እንዲሁም ከቤታቸው እንዲወጡ ተደርገው የተገደሉት ሰዎች፤ “በግጭት ተሳትፎ ያልነበራቸው” እና “ሲቪል ሰዎች” መሆናቸውን ጠቁሟል።

ኢሰመኮ በሪፖርቱ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ሰኔ 2/2016 ዓ.ም. በክልሎ አዊ ብሔረሰብ ዞን፤ ቤት ለቤት በመፈተሽ “ፋኖን ትደግፋላችሁ፤ ትቀልባላችሁ፤ ቤት ታከራያላችሁ” እንዲሁም “የፋኖ አባላት ናችሁ ብለው የጠረጠሯቸውን 10 ሲቪል ሰዎች በጥይት መግደላቸው ታውቋል” ብሏል።

ከአምስት ቀናት በኋላ ሰኔ 7 የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ደግሞ ፋኖ ኃይሎች “በፋኖ አባላት የደረሰባቸውን የደፈጣ ጥቃት ተከትሎ” በቀራኒዮ ከተማ ቀራኒዮ መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ “የቀብር ቦታ በመቆፈር ነበሩ 6 ነዋሪዎችን እና አንድ የአብነት ተማሪን መገደላቸውን” የዓይን ምስክሮችን ጠቅሶ ኢሰመኮ አስታውቋል።

በኢሰመኮ ሪፖርት መሠረት ከአማራ ክልል በመቀጠል ከፍተኛ ሲቪል ሰዎች የተገደሉት በኦሮሚያ ክልል ነው። ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ በክልሉ 43 ሲቪል ሰዎች መገዳለቸውን ተቋሙ በሪፖርቱ አስታውቋል።

ባለፈው ነሐሴ ወር መጀመሪያ “የአማራ ታጣቂዎች ቡድን አባላት” በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ በከፈቱት ተኩስ 22 ሰዎች መገደላቸውን እና አራት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን ኢሰመኮ አመልክቷል።

በክልሉ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ደግሞ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በነሐሴ ወር ብቻ “ከ14 ያላነሱ ሰላማዊ የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ግድያ ስለመፈጸሙ ከተለያዩ አካላት ከተሰበሰቡ መረጃዎች ለመገንዘብ ተችሏል” ሲል ኢሰመኮ ገልጿል።

በጋምቤላ ክልልም በተመሳሳይ ካለፈው ሰኔ ወር ወዲህ ሦስት የደቡብ ሱዳን ስደተኞችን ጨምሮ አምስት ሰዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ በረቡዕ ሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጉማይዴ ከተማ ነሐሴ አጋማሽ ላይ “የጉማይዴ ልዩ ወረዳ አስመላሽ” ተብሎ በሚጠራው ቡድን በተፈጸ ጥቃት፤ “ብዛታቸው ለጊዜው በትክክል ያልታወቀ የፖሊስ አባላት እና ነዋሪዎች መገደላቸውን” በኢሰመኮ ሪፖርት ላይ ተመላክቷል።

ኢሰመኮ በ14 ገጾች ባወጣው ሪፖርት ላይ ከሕግ ውጪ ግድያ በተጨማሪ የዘፈቀደ፣ ሕገ ወጥ፣ የጅምላ እና የተራዘመ እስር፣ የቦምብ ጥቃቶች፣ እገታ፣ የአገር ውስጥ መፈናቀል እና የመዘዋወር ነጻነት ገደቦች መኖራቸውን አስታውቋል።

ተቋሙ በዚሁ ሪፖርቱ “በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በግጭት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም [እንዲያደርጉ]” ጥሪ አቅርቧል።