ኢዋኦ ሃካማዳ እና እህታቸው
የምስሉ መግለጫ,በተፈበረከ ማስረጃ ከ50 ዓመት በላይ የታሰሩት ኢዋኦ ሃካማዳ እና እህታቸው

ከ 1 ሰአት በፊት

ሞት ተፈርዶባቸው ከ50 ዓመታት በላይ በእስር ቤት የቆዩት የ88 ዓመቱ ጃፓናዊ አዛውንት ለተፈረደባቸው ወንጀል የቀረበባቸው ማስረጃ የተቀነባበረ ነው በሚል በነጻ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት ወሰነ።

ኢዋኦ ሃካማዳ በአውሮፓውያኑ በ1968 አለቃቸውን፣ ሚስቱን እና ሁለት ልጆቹን ገድለዋል ተብለው በፍርድ ቤት ሞት ተፈርዶባቸው ከአምስት አስርት ዓመታት በላይ እስር ቤት ቆይተዋል።

ለግለሰቡ ነጻ መውጣት እንደምክንያት የቀረበው የአራቱ ሰዎችን ግድያ በተመለከተ መርማሪዎች ሆን ብለው ማስረጃዎችን በማስቀመጥ ሃካማዳን ወንጀለኛ እንዲባሉ ሳያደርጉ አይቀርም በሚል የፍርድ ሂደቱ እንደገና እንዲታይ በመደረጉ ነው።

ይህ ኢዋኦ ሃካማዳ ነጻ የወጡበት ውሳኔ በጃፓን ውስጥ ለረጅም ጊዜ አወዛጋቢ ሆኖ የቆየውን ታዋቂ የሕግ ጉዳይ መቋጫ እንዲያገኝ አድርጓል።

ጉዳዩ ከፍተኛ የሕዝብ ትኩረትን የሳበ ሲሆን ዛሬ ሐሙስ አዛውንቱ ነጻ የወጡበት ውሳኔ ሲተላለፍ በችሎቱ ውስጥ መቀመጫ አግኝተው ለመታደም በርካታ ሰዎች ተሰልፈው እንደነበር ተዘግቧል።

የአዛውንቱ ሐካማዳ የፍርድ ሂደት በድጋሚ ሲታይ በነበረበት ጊዜ ከእርጅና የተነሳ ባለባቸው የአእምሮ ጤና ሁኔታ ምክንያት ችሎቱ እንዳይገኙ ስለፈቀደላቸው በስፍራው አልተገኙም ነበር። ነገር ግን ነጻ መውጣታቸው ሲወሰን ደጋፊዎቻቸው ደስታቸውን ገልጸዋል።

የጃፓን ፍርድ ቤት የግለሰቡ ጉዳይ በድጋሚ እንዲታይ የወሰነው ከ10 ዓታት በፊት ሲሆን፣ ከዚያ ጊዜ አንስቶ ከእስር ቤት ወጥተው በእህታቸው አማካይነት እንክብካቤ እየተደረገላቸው ነው።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚለው ከሃምሳ ዓመታት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት ኢዋኦ፣ በዓለም ላይ ሞት ተፈርዶባቸው ለረጅም ጊዜ በእስር ላይ የቆዩ ግለሰብ ናቸው።

የቀድሞው ቦክሰኛ ግድያውን ፈጸመዋል ከተባለ በኋላ በየቀኑ ለ12 ሰዓታት በተደረገባቸው ምርመራ ወቅት ተፈጽሞብኛል ባሉት ድብደባ ወንጀሉን መፈጸማቸውን እንዳመኑ በመግለጽ ለፍርድ ቤት ተናግረው ነበር።

በፍርድ ሂደቱ ወቅት ዳኞች ተጨማሪ የዲኤንኤ ማስረጃ ጠይቀው ከገዳይ ጋር ተመሳሳይ መሆናቸው የተገለጸ ቢሆንም፣ ጠበቆች ግን ማስረጃው የተፈበረከ ነው በማለት ተከራክረው ነበር።

ኢዋኦ ሃካማዳ ቀጣሪያቸውን እና ቤተሰባቸውን ቶኪዮ ውስጥ በስለት ወግቶ በመግደል፣ 200 ሺህ የን (የጃፓን ገንዘብ) በመዝረፍ እና ንብረት በማቃጠል ወንጀል ተከሰው ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ ነበር ሞት የተፈረደባቸው።

ተከሳሹን ጥፋተኛ የሚያስብል ማስረጃዎች በመርማሪዎች የተዘጋጁ ሊሆኑ ይችላሉ በማለት በ2014 (እአአ) ከእስር ተለቀው ጉዳያቸው እንደገና በፍርድ ቤት እንዲታይ ተወስኖ ነበር። ነገር ግን ውሳኔው በቶኪዮ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውድቅ ተደርጓል።

ነገር ግን ለይግባኝ ሰሚ ችሎት አቤቱታ ከቀረበ በኋላ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከፍተኛው ፍርድ ቤት ጉዳዩን መልሶ እንዲመለከተው ካዘዘ በኋላ የቀደመው ውሳኔ መልሶ እንዲታይ ተወስኗል።

ለአስርት ዓመታት በቆየው አወዛጋቢ የፍርድ ውሳኔ ዙሪያ አሁን የተሰጠው አንድ ደም የነካው ልብስ ከተገኘ በኋላ ሲሆን፣ ጠበቆች ማስረጃው በፖሊስ የተፈበረከ ነው በሚል የዘረ መል ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀው ነበር።

ከብዙ ክርክር በኋላ በ2024 (እአአ) ልብሶቹ የሃካማዳ እንዳልሆኑ በመረጋገጣቸው ጉዳዩ በድጋሚ እንዲታይ ወሰኑት ዳኛ እስረኛው ከወህኒ ቤት ውጪ ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ በመወሰናቸው ነው አሁን በመጨረሳ ሃካማዳ ከግማሽ ክፍለ ዘመን እስር በኋላ ነጻ የተባሉት።

ለወንድማቸው ነጻ መውጣት ሲከናከሩ የቆዩት የ91 ዓመቷ እህታቸው ሂዴኮ “ይህችን ቀን ለማየት ለ57 ዓመታት ስጠብቅ ነበር፤ አሁን ደረሰች” በማለት “በመጨረሻም ትከሻዬ ላይ ወድቆ የነበረው ሸክም ተነስቶልኛል” በማለት የፍርድ ሂደቱ እንደገና እንዲታይ በተወሰነ ጊዜ ደስታቸውን ገልጸው ነበር።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከሃምሳ ዓመታት በላይ በእስር ላይ የቆዩት ሃካማዳ፣ በዓለም ላይ ሞት ተፈርዶባቸው ለረጅም ጊዜ በእስር ላይ የቆዩ ግለሰብ ናቸው ብሏል።