ትራምፕ

25 መስከረም 2024

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን የግድያ ሙከራ ሊደረግባቸው እንደሚችል የአሜሪካ ደኅንነት እንዳስጠነቀቃቸው ተገለጸ።

እጩው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከኢራን “እውነተኛና ግልጽ የግድያ ሙከራ ሊደረግባቸውና በዚህም አሜሪካን ቀውስ ውስጥ የመክተት ፍላጎት እንዳለ” በአገሪቱ ደኅንነቶች እንደተነገራቸው የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን አስታውቋል።

ይህ የግድያ ሙከራ ስጋት የቆየ ይሁን አዲስ በግልጽ አልተቀመጠም።

የኢራን መንግሥት እስካሁን በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን አልሰጠም።

ከዚህ ቀደም ግን በአሜሪካ ጉዳይ ጣልቃ ገብቷል መባሉን የኢራን መንግሥት አስተባብሏል።

ትራምፕ በኤክስ ገጻቸው “ከኢራን በሕይወቴ ላይ ትልቅ አደጋ ተቃጥቷል” ሲሉ ጽፈዋል።

“ኢራን ከዚህ ቀደምም ሙከራ አድርጋለች ግን አልተሳካም። በድጋሚም ይሞክራሉ” በማለትም አክለዋል።

ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ ማድረግ “ሙከራ አድራጊው በራሱ ላይ ሞት መጋበዝ ይሆንበታል” ሲሉ ተናግረዋል።

ለደኅንነት አባላት ተጨማሪ ክፍያ እንዲመደብ በኮንግረስ ውሳኔ መተላለፉን ትራምፕ አመስግነዋል።

የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ስቲቨን ቸንግ፣ “እነዚህ የተቀነባበሩ ተከታታይ ጥቃቶች ባለፉት ወራት መጨመራቸውን የደኅንነት ባለሥልጣናት አስታውቀዋል” ብለዋል።

“በሁሉም ክፍል ያሉ ሕግ አስከባሪዎች የትራምፕን ደኅንነት ለመጠበቅና ምርጫው ከጣልቃ ገብነት ነጻ እንዲሆን እየሠሩ ነው” በማለትም አክለዋል።

ቢቢሲ ከአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ዳይሬክተር አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

ትራምፕ ሁለት ጊዜ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸው መትረፋቸው ይታወሳል።

ለምን ሙከራዎቹ እንደተደረጉ በመጣራት ላይ ይገኛል።

የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ትራምፕ ከኢራን የግድያ ሙከራ ሊደረግባቸው እንደሚችል እንደተነገራቸው ከዘገቡ በኋላ የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ እንደዘገበው የኢራን ባለሥልጣኖች ክሱን “በተንኮል የተሞላ” ሲሉ አጣጥለውታል።

ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያቸው “ዕድሉ ስላለ ‘ትራምፕን መግደል’ ከቻሉ አሜሪካውያን ኢራንን ያመሰቃቅሏታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። አለበለዚያ ግን የአሜሪካ መሪዎች ወኔ ቢስ ይባላሉ” ብለው ጽፈዋል።

ትራምፕ ላይ ሁለተኛውን የግድያ ሙከራ ያደረገው ዌስሊ ሮውት በግድያ ሙከራ ተከሷል።

ያለፈው ወር የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን እንዳለው፣ የመጀመሪያ ደረጃ የመረጃ ልውውጥ የሚጠይቀው ትራምፕ ዒላማ የተደረጉት በኢራን አማካይነት ነው።

እአአ በ2022 የኢራን እስላማዊ ዘብ አባል ሻሀርም ፖርሳፊ የትራምፕን የቀድሞ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጆን ቦልተን ለመግደል በማሴር ተከሷል።

ግለሰቡ ግድያውን ለማስፈጸም 300,000 ዶላር ለመክፈል መሞከሩ የተገለጸ ሲሆን፣ አሜሪካ በምላሹ የኢራን ወታደራዊ ኮማንደር ቃሲም ሱሌማኒን ገድላለች።