የሰዳን ዋና ከተማ ካርቱም

26 መስከረም 2024, 18:19 EAT

የእርስ በርስ ጦርነት ላይ ባለችው ሱዳን ጠንካራ አቅም ካለው የፈጥኖ ደራሽ ላይል እየተዋጋ ያለው የሱዳን ጦር በዋና ከተማዋ ካርቱም በሚገኙ የተለያዩ ሥፍራዎች ላይ ጥቃት ከፈተ።

የመንግሥት ኃይሎች ካርቱም እና በሰሜናዊው የከተማዋ ክፍል በምትገኘው ባሕሪ የሚገኙ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (አርኤስኤፍ) ላይ ጥቃት የከፈቱት ሐሙስ ንጋት ነው።

የመንግሥት ኃይል እና የአርኤስኤፍ ተዋጊዎች በሥልጣን ሽኩቻ ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ ሱዳን ከአንድ ዓመት በላይ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ትገኛለች።

የተባበሩት መንግሥት በሱዳን ያለው ሁኔታ እጅግ የከፋ የሰብዓዊ ቀውስ አስከትሏል ብሏል።

በጦርነቱ ምክንያት 150 ሺህ ሰዎች መገደላቸው የተሰማ ሲሆን፣ አንድ አምስተኛ የሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ ማለትም 10 ሚሊዮን ያህል ቤት ንብረቱን ጥሎ ተፈናቅሏል።

የዓይን እማኞች እንደሚሉት ሐሙስ ጥዋት በዋና ከተማዋ ከፍተኛ የአየር ጥቃት እና ውጊያ ተከፍቷል። የመንግሥት ኃይሎች በናይል ወንዝ ላይ የሚገኙ ሁለት ድልድዮችን አልፈው ወደ ከተማዋ ዘልቀው ገብተዋል።

ድልድዮቹ ኦምዱርማን የሚገኙ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ ሥፍራዎችን ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሎ መቀመጫ የሚለዩ ናቸው።

ከወራት በኋላ የተከፈተው የሐሙሱ ጥቃት መንግሥት ከቁጥጥሩ ውጪ የሆኑ ቦታዎችን ለመያዝ ጥረት ያደረገበት ነው ተብሏል።

የጦሩ መሪ ጄኔራል አብድል ፋታህ አል-ቡርሀን ኒው ዮርክ በሚካሄደው የመንግሥታቱ ድርጅት ጉባዔ ላይ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ እየተጠበቀ ባለበት ዕለት ነው ጥቃቱ የተከፈተው።

የተባበሩት መንግሥታት በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ግጭት “በፍጥነት” እንዲቆም እና ሰላማዊ ሰዎች ወደቀያቸው እንዲመለሱ ጠይቋል።

በጣም የከፋ እና የበርካታ ሰዎች ሕይወት ያለቀበት ጦርነት የተካሄደው ሰዎች ሰብሰብ ብለው በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ነው። መንግሥት እና ሚሊሻው ሰላማዊ ሰዎችን ሳይለዩ በቦምብ መትተዋል ሲሉ እርስ በርስ ይወነጃጀላሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ረቡዕ ባወጣው መግለጫው “በአገሪቱ ያለው ግጭት በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ስቃይ አምጥቷል፤ በዓለማችን ፈጣን የሆነው መፈናቀልም የተከሰተው በሱዳን ነው” ብሏል።

መኖሪያቸውን ጥለው ከተፈናቀሉ 10 ሚሊዮን ገደማ ሱዳናውያን መካከል ግማሹ ሕፃናት እንደሆኑ የጠቆመው ድርጀቱ 2 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች በጎረቤት አገራት ጥገኝነት እንደጠየቁ አመልክቷል።

በጦርነቱ ምክንያት ሰዎች ሰብል ማብቀል ባለመቻላቸው የረሃብ አደጋ እየከፋ እንደሚመጣም ተገምቷል።

በምዕራባዊቷ ዳርፉር ግዛት ደግሞ አረብ ያልሆኑ ሱዳናውያን ላይ የዘር ጭፍጨፋ ደርሶባቸዋል የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰምቷል።

የኮሌራ ወረርሽኝ እየተንሰራፋባት ባለችው ሱዳን ባለፈው ወር ብቻ በቀላሉ መዳን በሚችሉ በሽታዎች 430 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።

የተለያዩ የተራድዖ ድርጅቶች እርዳታ ለማድረስ የሚያደርጉት ጥረት ባለው ግጭት ምክንያት እየተሰናከለባቸው ይገኛል።