ቢሊየነሩ ኢላን መስክ

26 መስከረም 2024, 14:39 EAT

የዓለማችን ቱጃሩ ሰው ኢላን መስክ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በሚያዘጋጀው የኢንቨስትመንት ስብሰባ ላይ ባለመጋበዙ ቁጣውን ገለፀ።

ኢላን መስክ፤ ኢንተርናሽናል ኢንቨስትመንት ሰሚት ለተባለው ስብሰባ ያልተጋበዘው ባለፈው ወር በዩኬ በነበረው አመፅ ምክንያት ማኅበራዊ ሚድያ ላይ በለጠፋቸው መልዕክቶች ምክንያት መሆኑን ቢቢሲ ተገንዝቧል።

“ማንም ሰው ወደዩኬ መሄድ የለበትም። ወሲባዊ ጥቃት ያደረሱ ሰዎችን እየለቀቁ፤ ማኅበራዊ ሚድያ ላይ አስተያየት የሰጡ ሰዎችን እያሰሩ ነው” ብሏል።

ምንም እንኳ የዩኬ መንግሥት እስር ቤቶች ሞልተዋል በሚል ታራሚዎችን ቢለቅም ነፃ ከወጡት መካከል ወሲባዊ ጥቃት ያደረሱ ሰዎች የሉበትም።

ባለፈው ነሐሤ በዩኬ ከነበረው አመፅ ጋር በተያያዘ በማኅበራዊ ሚድያ አመፅ የቀሰቀሱ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል።

በመላው ዩኬ አመፅ የተዛመተው በሳውዝፖርት አየር ማረፊያ በደረሰ አደጋ ሶስት ሕፃናት በጩቤ ተወግተው ከተገደሉ በኋላ ነው።

የቀድሞው ትዊተር የአሁኑ ኤክስ ባለቤት የሆነው ኢላን በገዛ ማኅበራዊ ገፁ የእርስ በርስ ግጭት ይነሳል እያለ ሲተንበይ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩን በተደጋጋሚ ሲተቻቸው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር በሚመጣው ጥቅምት የሚካሄደው ስብሰባ በርካታ ኢንቨስተሮች እንደሚገኙበት እና በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚሰበሰብበት ተስፋ አድርገዋል።

መስክ ባለፈው ዓመት ለተካሄደው ስብሰባ ቢጠራም አለመገኘቱ አይዘነጋም። መንግሥት ኢላን መስክን ለምን እንዳልጋበዘ እስካሁን አስተያየት አልሰጠም።

በነሐሤው አመፅ ወቅት መስክ በኤክስ ማኅበራዊ ሚድያ ገፁ የዩኬ መንግሥት አመፀኞችን “የሚያጉርበት ካምፕ” ፋልክላንድ ደሴት ላይ አዘጋጅቷል የሚል የሤራ ፅንሰ ሐሳብ አሰራጭቶ ነበር። ነገር ግን ከቆይታ በኋላ ይሄን ፅሑፉን አጥፍቶታል።

የዩኬ ሚኒስትሮች ይሄን የመስክ መልዕክቶ ተከትሎ ቁጣቸውን ገልፀው ነበር።

ቢቢሲ ከምንጮቹ እንደተረዳው ኢላን መስክ በመቶዎች የሚቆጠሩ የዓለማችን ጉምቱ ኢንቨስተሮች በሚገኙበት ስብሰባ ላይ ያልተጋበዘው በዚህ ምክንያት ነው።

ኢላን መስክ ማነው?

የዓለማችን ሀብታሙ ሰው ኢላን መስክ በኤክስ ገፁ ሐሳቡን ያለመታከት በመግለፅ ይታወቃል።

ብሉምበርግ እንደሚለው የኢላን የተጣራ ሀብት 228 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ ይችላል። አብዛኛው ገንዘቡ 13 በመቶ ድርሻ ካለው ቴስላ ከተባውለ ድርጅቱ የሚመዘዝ ነው።

ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ወደ ሲሊከን ቫሊ የቴክኖሎጂ ዓለም የመጣው የ53 ዓመቱ ባለሀብት የተወለደው በደቡብ አፍሪካዋ ፕሪቶሪያ ከተማ ነው።

መስክ ገና የ12 ዓመት ታዳጊ ሳለ ነው የኮምፒውተር ጌም የሠራው።

በአውሮፓውያኑ 2002 የአሜሪካ ዜግነት ያገኘው መስክ ራሱን “ግማሽ ዲሞክራት፤ ግማሽ ሪፐብሊካን” እንዲሁም “በተነፃፃሪ ለዘብተኛ” እና “ገለልተኛ” ሲል ይጠራል።

ከዚህ ቀደም ለዲሞክራቶቹ ባራክ ኦባማ፣ ሂላሪ ክሊንተን እና እያመነታም ቢሆን ለጆ ባይደን ድምፁን እንደሰጠ አስታውቋል።

ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወደ ሪፐብሊካን ፓርቲ ያደላው መስክ በ2024 የአሜሪካ ምርጫ ድምፁን ለዶናልድ ትራምፕ እንደሚሰጥ በይፋ ተናግሯል።