
ከ 5 ሰአት በፊት
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የምግብ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ሱዳኗ መዲና ካርቱም ገቡ።
በሱዳን ጦር እና በፈጣን ደጋፊ ኃይሎች መካከል እየተደረገ ባለው ደም አፋሳሽ ጦርነት ምክንያት ሱዳን በዓለማችን እጅግ የከፋ የረሃብ ቀውስ ውስጥ እንደምትገኝ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።
እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ሐሙስ፣ ታህሳስ 17/ 2017 ዓ.ም ወደ ደቡባዊ ካርቱም ሲገቡ በርካቶች “በሳቅ እና በደስታ እንባ ታጅበው ነበር” ሲሉ የረድዔት ሰራተኛ የሆኑት ዱኣ ታሪክ ገልጸዋል።
የእርዳታ ኤጀንሲዎች የጸጥታ ስጋቶች እንዲሁም ተፋላሚ ወገኖች በሚያደርጓቸው የመንገድ መዝጋቶች ጋር በተያያዘ ወሳኝ የሆኑ የእርዳታ አቅርቦቶችን እያስተጓጎሉ ነው በማለት ሲወቅሱ ቆይተዋል።
የሐሙሱ እርዳታ እንዲደርስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎች እና የሱዳን ማህበረሰብ ቡድኖች ከሱዳን ጦር እና ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር ድርድር አካሂደዋል።
“በእንባ ታጅበን ነበር፣ የደስታ እንባ፣ ይህንን ለማድረግ የደከምንበት እና የጥረታችን እንባ፤ አስገራሚ ክስተት ነበር” ሲሉ የሱዳን የሰብዓዊ የረድዔት ድርጅት ጋር የሚሰሩት ታሪክ ለቢቢሲ ኒውስ ደይ ፕሮግራም ተናግረዋል።
እርዳታው 28 የጭነት መኪኖች እንዳካተተ ተገልጿል። ከእርዳታው ውስጥ አምስቱን የጭነት መኪና የላከው ዩኒሴፍ “ህይወት አድን” የምግብ እና የጤና አቅርቦቶችን ለአልባሻየር ሆስፒታል እና በካርቱም ለሚገኙ ሌሎች የጤና ማዕከላት ማድረስ መቻሉን ገልጿል።
- ሶማሊያ በቀይ ባህር ዳርቻ የባህር በር ለኢትዮጵያ ሰጥታለች መባሉን አስተባበለች27 ታህሳስ 2024
- በዘውዲቱ ሆስፒታል አንዲት እናት 6 ኪሎግራም የሚመዝን ህጻን ተገላገለች27 ታህሳስ 2024
- ሰሞኑን በዩኒቨርስቲዎች የተፈጠረው “ተቃውሞ” መነሻው ምንድን ነው?27 ታህሳስ 2024
“ካርቱም ውስጥ ይህ እርዳታ በጣም ያስፈልገናል። በከፍተኛ ሁኔታ ስንጠብቀው ነበር። ይህንንም ለማድረግ በርካታ መንገዶችን እና ዘዴዎችን ሞክረናል። በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የረሃብ ተጽእኖ ለመቀነስ ብቸኛው መንገድ እንዲህ ያሉ እርዳታዎች ናቸው” ብለዋል።
ከቀናት በፊት አንድ ገለልተኛ የምግብ ዋስትና ባለሙያዎች ቡድን ሱዳን ወደ “ከፋ የረሃብ ቀውስ” እየገባች ነው ሲል አስጠንቅቆ ነበር።
ረሃብ ወደ አምስት አካባቢዎች የተዛመተ ሲሆን 24.6 ሚሊዮን ወይም ግማሽ ያህሉ ህዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ቡድኑ ገልጿል።
ጦሩ እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከሶስት ዓመታት በፊት በጋራ መፈንቅለ መንግሥት ቢያደርጉም ነገር ግን በመሪዎቹ መካከል በተፈጠረ የስልጣን ሽኩቻ አገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ከገባች 20 ወራትን አስቆጥሯል።
በሱዳን የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ቶም ፔሪየሎ በጦርነቱ እስከ 150 ሺህ ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀሩ በግንቦት ወር ተናግረው ነበር።
በሱዳኑ ጦርነት ምክንያት ከ11 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።
በጦሩ እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል እየተደረገ ያለውን ጦርነት ለማስቆም የተደረጉ የሽምግልና ጥረቶች ፍሬ ሳያፈሩ ቀርተዋል።