ልናገር የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አውጪዎች ችግር የት ጋ ነው ያለው?

አንባቢ

ቀን: February 12, 2025

በጌታነህ አማረ

የአንድን አገር ኢኮኖሚ ችግር ለመፍታት መጀመሪያ ቁልፍ የሆነውን ነገር መረዳት በጣም ጠቃሚ  ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ቁልፍ ነገር ተብሎ የሚጠራው ‹‹ተርኒንግ ፖይንት›› ነው፡፡ ‹‹ተርኒንግ ፖይንት›› የአንድን አገር ኢኮኖሚ በመሠረታዊነት ለመለወጥ ብሎም ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ችግሮችን ለማስወገድ ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ትንሳዔም ለማብሰርና ለመከወን  ቁልፍ መሣሪያ ነው፡፡ ይህ ቁልፍ ነገር ጥቅም ላይ ካልዋለና ችግሮች ካልተፈቱ ግን የሰው ልጅ በከንቱ ሲዳክርና ሲለፋ ይኖራል እንጂ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም፡፡ ለውጥ ማለት ደግሞ አንድ ሰው በጥሩ አካላዊ፣ አዕምሮዓዊና መንፈሳዊ የተገነባ ሰው መፍጠር ማለት ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ጥሩ ኢኮኖሚ ያስፈልጋል፡፡ ጥሩ ኢኮኖሚ ለማምጣት ጥሩ የኢኮኖሚ ሥርዓት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ጥሩ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመፍጠር ደግሞ መነሻችን የኢኮኖሚ ተርኒንግ ፖይንትን ማወቅ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህንንም በቀላሉ ለመረዳት ይጠቅመን ዘንድ ምሳሌ ወስደን ለማየት እንሞክር፡፡

ይህን ለማየት ደግሞ በአንድ አገር ኢኮኖሚ የምትመሰለውን ብስክሌት ምሳሌ አድርገን እንውሰድ፡፡ አንድ ብስክሌት ተንቀሳቅሶ ለመሄድ ወሳኝ የሚባሉ ክፍሎች አሉት፡፡ እነሱም አካል ወይም ቦዲ፣ ፔዳል፣ ጊር እና ችንጋ ናቸው፡፡ እነዚህ ክፍሎችም እርስ በእርሳቸው መስተጋብር ፈጥረው እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ሳይክሉ እንዲጓዝ ያስችሉታል፡፡ እነዚህ ወሳኝ የተባሉ ክፍሎች እርስ በእርሳቸው የሚያደርጉት ትስስርና ዝምድና ሳይክሉ የተሳካና የሰመረ ጉዞ እንዲኖረው ያደርጉታል፡፡ ነገር ግን ይህ እንዲሆን ችንጋ የተባለው የሳይክሉ ክፍል በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ችንጋ ላይ ችግር ከተፈጠረ ሳይክሉ መንቀሳቀስ አይችልም፡፡ የዚህ ችንጋ ችግር ደግሞ መላላት፣ መርገብ፣ ማጠር ወይም መርዘም ሊሆን ይችላል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ቁልፉ ነገር የችንጋውን ርዝመት መጠን ለክቶ ማወቅና የመግጠም ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ለማወቅ የፈለገ ሰው ሳይክል ጠጋኞች ጋ ሄዶ ማስተዋል ይችላል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ሲታገሉ የሚታዩት ይህን የላላውን ችንጋ በሬጅስትሮ ለማስተካከል ሲሞክሩ ነው፡፡ በተመሳሳይ የአንድ አገር ኢኮኖሚ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ችንጋ ተብሎ የሚጠራው የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሣሪያ ነው፡፡ ይህ መሣሪያ ደግሞ ልኬት ያስፈልገዋል፡፡  ልኬቱ ደግሞ ተርኒንግ ፖይንት ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ ኢኮኖሚው የተስተካከለና የሰመረ ጉዞ እንዲያደርግ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሣሪያ ልኬቱ ትክክለኛ ቦታ ላይ መቀመጥ አለበት፡፡

 ይህ ከሆነ የአንድ አገር ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መሠረታዊ ግብዓት ናቸው የሚባሉት  የሰው ኃይል፣ ተቋም፣ የኢኮኖሚ ሴክተርና የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትስስር ፈጥረው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የተሳካና የሰመረ በመሆን ኢኮኖሚን በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጉታል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የተርኒንግ ፖይንትን ምንነት ከተረዳን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ችግር መረዳትና መፍታት ይቀለናል ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ችግር የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት እንደሆነ ታምኖበታል፡፡ ይህ ከሆነ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት ማለት ምን ማለት ነው? የተሰበረውስ የቱ ጋ ነው? የሚለውን ማወቅ ችግሩን ለመፍታት መሠረታዊ ጥያቄ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ እንግዲህ ማክሮ ኢኮኖሚ ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መሠረታዊ  ሲሆን፣ ችግር ከደረሰበት ግን ለሁለንተናዊው ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ማኅበራዊ ቀውስ የሚዳርግ መሆኑ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ማክሮ ኢኮኖሚ ማለት የአንድ አገር አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሁኔታ የሚያጠና ሲሆን፣ በአብዛኛው ትኩረት የሚያደርግባቸው ጉዳዮች ደግሞ የገንዘብ አስተዳደር፣ የመንግሥት በጀት አስተዳደር፣ የታክስ አስተዳደር፣ የውጭ ንግድ ሚዛን አስተዳደር፣ የውጭ አገር ገንዘብ አስተዳደር፣ የመሠረታዊ ሸቀጦች አቅርቦትና ዋጋ አተማመን ይገኙበታል፡፡ እነዚህን ለመቆጣጠርና ጤናማነታቸውንም ለመጠበቅ ደግሞ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መሣሪያዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የገንዘብ ፖሊሲ፣ የፊሲካል ፖሊሲና የመሠረታዊ ዕቃዎች ዋጋ ይገኙበታል፡፡ ከዚህም በመነሳት አብዛኛውን ጊዜ የኢኮኖሚ ስብራት ገጥሟል የሚባለው ከፍተኛ የዋጋ ንረት ወይም ውድቀት  ሲገጥም፣ የውጭ ንግድ ሚዛን ሲዛባ፣ ከፍተኛ የአገር ውስጥና የውጭ ብድር ጫና ሲገጥም ወይም የመክፈል አቅም ሲዳከም፣ የሥራ አጥ ቁጥር ሲጨምር፣ የመንግሥት በጀት ጉድለት ሲታይ፣ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ሲቀንስና የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሣሪያዎችን ጥቅም ላይ በማዋል ችግሩን መቅረፍ ሳይቻል ሲቀር ማክሮ ኢኮኖሚው ስብራት ገጥሞታል ማለት ይቻላል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ለሚገጥሙ የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮች፣ እየተወሰዱ ያሉ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ዕርምጃዎች ፈጣን መፍትሔን እያመጡ አይደሉም፡፡ ምሳሌ አሜሪካና አውሮፓ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቀውስን ተከትሎ የመጣውን የኢኮኖሚ ቀውስ ለማስተካከል የተወሰደው የወለድ ምጣኔ ፖሊሲ ዕርምጃ፣ እስካሁን ድረስ የሚፈለገውን የሁለት በመቶ የተረጋጋ የዋጋ ንረት ምጣኔ ሊያመጣ አልቻለም፡፡ በመሆኑም የዚህ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሣሪያ ውጤታማነት እያከተመ የመጣ ይመስላል፡፡ ከዚህም በመነሳት አገሮች አማራጭ የፖሊሲ ዕርምጃ መሣሪያዎችን የማፈላለግ ሥራ ሊሠሩ ይገባል፡፡ እዚህ ጋ ዋነኛውና ወሳኙ መመለስ የሚገባው ጥያቄ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መሣሪያዎቹ ጥቅም ላይ ሲውሉ ለምን የማክሮ ኢኮኖሚውን ስብራት መጠገን ይሳናቸዋል የሚለው ነው፡፡

ይህን ጥያቄ በአግባቡ  ለመመለስ ቀላል ምሳሌ ወስደን ለማየት እንሞክር

በአሁኑ ጊዜ አንድ አገር ራሷን ከወራሪ ጠላት ለመከላከልም ሆነ ለማጥቃት ግድ ዘመናዊ መሣሪያ መታጠቅ አለባት እንበልና ስናይፐር ጠመንጃ ለመታጠቅ ብትወስን፣ ይህንን ስናይፐር ለመታጠቅ ከአምራች አገሮች መግዛት ይጠበቅባታል፡፡ ስትገዛ ደግሞ በተመሳሳይ ለእሱ የሚስማማ ተተኳሸ ጥይት አብሮ መገዛት አለበት፡፡ ነገር ግን ተተኳሽ ጥይቱን አጥታ ስናይፐር ጠመንጃ ብቻ በመግዛት ለወታደሩ ከሌላ ኋላቀር ከሆነ ተተኳሽ ጥይት ጋር አስታጥቃ፣ ሄደህ ተሠለፍና ጠላትን ተከላከል ወይም አጥቃ ብላ ብታሠልፈው ሊከላከል ወይም ሊያጠቃ አይችልም፡፡ ምክንያቱም የያዘው ስናይፐር የሌላ ወይም የኋላቀር መሣሪያ ተተኳሽ ጥይትን ተኩሶ ጠላትን ማጥቃት አይችልም፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ ወታደሩ ሊያደርግ የሚችለው ጠላትን እጅ በእጅ፣ በሰደፍ ወይም ደግሞ በአፈሙዝ ገጥሞ መፋለም ነው፡፡ ይህን ሲያደርግ ግን በጠላት መሸነፉ አይቀሬ ነው፡፡ ነገር ግን አገሪቱ ጠንካራ ከሆነች፣ ቆራጥነትና አንድነት ካላት ዘመናዊ መሣሪያ ታጥቆ አገርን ሊወር የመጣውን ጠላት ልክ እንደ ዓድዋ ጦርነት መክታ ማሸነፍ ትችላለች፡፡ አሁን እዚህ ጋ ትልቁ ኃይል ዘመናዊ መሣሪያ መታጠቅ ሳይሆን ቆራጥነትና አንድነት ሆነ ማለት ነው፡፡

በተመሳሳይ አንድ አገር ድህነትን ለመዋጋትና ለማጥፋት ተቋማትን በዘመናዊ መልክ ገንብቶ፣ በሰው ኃይልና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አደራጅቶ የሚጠቀመው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ኋላቀርና የቆየ ከሆነ ስናይፐሩ የቆየ ተተኳሽ ጥይትን ተኩሶ ጠላትን ማጥቃት እንደማይችለው ሁሉ፣ በዘመናዊ መልክ የተገነቡት ተቋማትም በቆየ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መሣሪያ ኋላቀርነትንና ድህነትን ተኩሰው ማጥፋት አይችሉም፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ እየተባለ ያለው ኋላቀርነትንና ድህነትን በሕዝቦች ዘንድ ቁርጠኝነትና አንድነት ፈጥረን እናጥፋ የሚል ሐሳብ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የሚፈለገውን ቁርጠኝነትና አንድነት አሁን ያለው ትውልድ ላይ በቀላሉ ማምጣት ይቻላል ወይ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ አለ ከተባለስ በሰላም ዕጦት፣ በድህነትና ኋላቀርነት ማጥፋት ላይ ትውልዱ ልክ እንደ ቀድሞ አባቶቹ ቆራጥንነቱንና አንድነቱን አምጥቶ ለምን አይደግመውም የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡

 ስለዚህ ለዚህ ጉዳይ መልስ ለማግኘት በእኔ በኩል አዳጋችና አስቸጋሪ ስለሚሆን መልሱን ለአንባቢ ልተው፡፡ ነገር ግን በእኔ በኩል ለአሁኑ ዘመን ችግር መፍትሔ ሊሆን ይችላል የሚለውን ለማመላከት ወደድሁ፡፡ አንድ አገር ራሷን ከጠላት ለመከላከል ዘመናዊ መሣሪ የመታጠቅ ዓላማ ካላት የተተኳሽ ጥይቱንም ጉዳይ ልታስብበት ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ስናይፐሩ ከእጅ አይሻል ዶማ ሆኖ የወጣበት ገንዘብና ጉልበት ጥቅም ሳያስገኝ ቀርቶ አገርን ለከፍተኛ ኪሳራ ይዳርጋል፡፡ በተመሳሳይ ድህነትና ኋላቀርነትን ለማጥፋት ተቋም ሲገነባ፣ የዘመናዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲው ጉዳይም አብሮ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ አለበለዚያ ግን በዘመናዊ መንገድ የተገነቡት ተቋሞች ልክ እንደ ስናይፐሩ ዘመናዊ አስፈሪና ግርማ ሞገስ ኖሮት ጠላትን ማጥቃት እንደማይችለው ሁሉ፣ ተቋማትም አምረውና ተውበው ቢገነቡም ድህነትንና ኋላቀርነትን የማጥፋት አቅም ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ነገር ግን ዘመናዊ የማክሮ ኢኪሚ ፖሊሲ ወይም ቺንጋ ቢገጠምላቸው ጠቀሜታቸው በጣም የጎላ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ውበታቸው ያማረ ሆኖ የሚያመርቱት የኢኮኖሚ ቁጥር የዜጎችን ሕይወት በመሠረታዊነት ሲቀይር አይታይም የሚሉ አስተያየቶች በስፋት ሲሰጡ ይሰማል፡፡ እንግዲህ መልክና ውበት ታጥቦ አይጠጣም የሚሉት ብሂል አለ እና ሙያም እንዲኖራቸው ሥራ ሊሠራ ይገባል፡፡ 

አሁን በሥራ ላይ ያሉት የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መሣሪያዎች እንዴት እንደማይሠሩ ቀጥለን ለመመልከትና ችግሩ የቱ ጋ እንዳለ ለማየት እንሞክር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስት እንደ ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መሣሪያ ሊያገለግሉ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡት የገንዘብ ፖሊሲ፣ የፊሲካል ፖሊሲና የመሠረታዊ ዕቃዎች ዋጋ (ነዳጅ፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ ስንዴ፣ ዘይት፣ ስኳር፣ ሲሚንቶ፣ መድኃኒት) እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ በተወሰደው ጥብቅ የገንዘብ፣ የፊሲካልና የውጭ ምንዛሪ ግብይት ፖሊሲ ለውጥ ምክንያት የተወሰደውን ዕርምጃ ተከትለን  የነዳጅ ዋጋን  እንደ ምሳሌ በመውሰድ እንዴት የዋጋ ንረትን ማረጋጋት እንደሚችል ለማየት እንሞክር፡፡ የነዳጅ ዋጋ ከነበረበት 102 ብር ወደ 112 ብር  በመንግሥት ጭማሪ ተደረገ እንበል፡፡ ይህም በመሆኑ ምክንያት በገበያው ላይ ምን ሊፈጠር ይችላል የሚለውን እንይ። ለምሳሌ የጤፍን ዋጋ እንውሰድ፣ የጤፍ ዋጋ ምን ሲሆን ይጨምራል? ይቀንሳል ወይስ በነበረበት ይቀጥላል? በዚህም መሠረት የጤፍ ዋጋ የሚጨምርበት፣ ባለበት የሚቆይበት፣ ወይም የሚቀንስበት ተርኒንግ ፖይንት ይኖረዋል።

ይህንን ተርኒንግ ፖይንት ለማወቅ ደግሞ የገንዘብና የፊሲካል ፖሊሲ ዕርምጃ ደረጃው እንዲሁም የመሠረታዊ ዕቃዎች (Strategic Goods)  የዋጋ ጭማሪ መጠንን ማመጣጠን ያስፈልጋል። ስለዚህ የነዳጅ ዋጋ ከ102 ወደ 112 ብር ሲጨምር የጤፍ ዋጋ ተርኒንግ ፖይንት 16,000 ብር ቢሆን ምን ይፈጠራል የሚለውን እንይ። ነዳጅ የጨመረው በአሥር በመቶ ከሆነ የትራንስፖርት ዋጋ በአሥር በመቶ ይጨምራል ማለት ነው፡፡ በተመሳሳይ የጤፍ ዋጋ በአሥር በመቶ በመጨመር 17,600 ብር ይሆናል። ሸማች ግን በዚህ ዋጋ የመግዛት አቅም አይኖረውም። ምክንያቱ ደግሞ የመግዛት አቅሙ በኩንታል 16,000 ብር ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ነጋዴው ሽያጩ በ17,600 ብር ሊከናወንለት አይችልም። ሽያጭ ካልተከናወነለት ደግሞ  ከገበሬው ተጨማሪ ጤፍ መግዛት አይችልም፡፡ ስለዚህ ነጋዴው እንዲገዛው  ገበሬው  በአሥር በመቶ ቀንሶ ለመሸጥ ይገደዳል። በዚህም የተነሳ የነዳጅ ጭማሪው ዋጋ ሸማቹ ላይ ማረፉን ትቶ አምራች ላይ አረፈ ማለት ነው። በዚህም ምክንያት የጤፍ አምራቹ ገበሬ ገቢ በአሥር በመቶ መቀነሱ ግድ ነው።

በዚህም መሠረት የሸማች አቅም ተርኒንግ ፖይንት ላይ ከደረሰ በኋላ፣ በመሠረታዊ ሸቀጦች (Strategic Goods) ላይ የሚደረግ የዋጋ ጭማሪም ሆነ የሚወሰዱ ጥብቅ የገንዘብና የፊሲካል ፖሊሲ ዕርምጃዎች ተፅዕኖ የሚያሳድሩት በሸማቾች ላይ ሳይሆን፣ በአምራቾች ወይም በአቅራቢዎች ላይ ይሆናል ማለት ነው። አምራቾች ወይም አቅራቢዎች ስንል ሪል ስቴት አልሚዎች፣ ፋብሪካዎች፣ የገንዘብ ተቋማት፣ አገልግሎት ሰጪዎች፣ የግብርና ምርት አምራቾች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችና ሌሎችም ይገኙበታል። ስለዚህ የነዳጅ ጭማሬው ከተርኒን ፖይንት በኋላ 50 በመቶ ከጨመረ የጤፍ አምራች ገበሬው ምርት ዋጋ በ50 በመቶ ይቀንሳል ማለት ነው። እንግዲህ ገበሬው ምርቱን በርካሽ ከሸጠ በኋላ ለቀጣይ የግብርና ዝግጅት መሬት፣ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ እንዲሁም በሬ በመግዛት መዘጋጀት አለበት፣ ስለዚህ በነዳጅ መወደድ ምክንያት በርካሽ ዋጋ ሸጬ ተገላገልኩ ሲል በሌላ በኩል ደግሞ ሌላው ስትራቴጂካዊ ዕቃ የሆነው ማዳበሪያ ዋጋው ከጨመረ፣ በሌላ በኩል ተጎጂ ይሆንና ቀጣይ የግብርና ምርትና ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በመፍጠር አጠቃላይ የአገር ምርትና ምርታማነት ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡ በመሆኑም የፖሊሲ አውጪዎች በሚወስዱት ጥብቅ የገንዘብና ፊሲካል ፖሊሲ ዕርምጃ፣ ከፍተኛ የግብር ተመን፣ የስትራቴጂክ ዕቃዎች ዋጋ ጭማሪ፣ (የነዳጅ፣ ማዳበሪያ፣ ቴሌኮም፣ ውኃ፣ መብራት፣ መድኃኒትና ሌሎችም)  ላይ የሚደረጉ የዋጋ ለውጦችን ኢኮኖሚው በደምሳሳው በከፍተኛ ደረጃ እንደ ጥብቅ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዕርምጃ ወስዷቸው፣ በኢኮኖሚው ላይ ያልታሰበ ጫና ሊያሳድሩ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡

አዎ ልክ ነው ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ ሁል ጊዜ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ምክር ብቻ ጥቅም ስለሌለው የኢትዮጵያን ትንሳዔ ለማብሰርና ለመከወን ፖሊሲ አውጪዎች አመለካከታቸው በብዙ ነገር መቀየር አለበት፡፡ በመሆኑም ትንሳዔውን ለማብሰርና ለመከወን ይረዳ ዘንድ አስቸጋሪና አንዱ መስተካከል ያለበት ግብዓት የዋጋ ንረትን የተረጋጋ የማድረግ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንንም ለማድረግ የኢትዮጵን የዋጋ መጠን (Genral Price Level) እና የፖሊሲ ዕርምጃን ተርኒነግ ፖይንት ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ከታወቀ የዋጋ ንረትን መቆጣጠር ቀላል ይሆናል ማለት ነው፡፡

እንበልና የዋጋ ንረትን ሁለት በመቶ የተረጋጋ ለማድረግ የፖሊሲ ዕርምጃውን የተረጋጋ የዋጋ መጠን ባለው የተፅዕኖ ምጣኔ መጠን ከፍ ማድረግ ነው፡፡ ይህም ሲባል የዋጋ መጠን ተርኒንግ ፖይንት ላይ እንዲደርስ የፖሊሲ ዕርምጃዎች ያላቸው ጉልበት ምን ያህል ፐርሰንት ድርሻ እንደሆነ ማወቅ ተገቢነት ያለው ጉዳይ ሲሆን፣ ትልቁንና ትንሹን ድርሻስ የያዘው የትኛው የፖሊሲ መሣሪያ ነው የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ምሳሌ ወስደን ለማየት እንሞክር፡፡ የማዕከላዊ ባንክን የወለድ ምጣኔ ፖሊሲ በ0.50 በመቶ ከፍ ማድረግ የዋጋ ንረትን በአንድ በመቶ ከፍ የማድረግ አቅም ቢኖረው፣ የግብር ተመንን በአምስት በመቶ ከፍ ማድረግ የዋጋ ንረትን በአንድ በመቶ ከፍ የማድረግ አቅም ቢኖረው፣ የነዳጅ ዋጋን በአሥር በመቶ ከፍ ማድረግ የዋጋ ንረትን በአንድ በመቶ ከፍ የማድረግ አቅም ካለው፣ በተርኒን ፖይንት ጊዜ የሚኖረውን ዜሮ በመቶ የዋጋ ምጣኔ ወደ ሦስት በመቶ ከፍ ለማድረግ የማዕከላዊ ባንክን የወለድ ፖሊሲ በ0.50 በመቶ ከፍ ማድረግ፣ የግብር ተመንን በአምስት በመቶ ከፍ ማድረግና የነዳጅ ዋጋን በአሥር በመቶ ከፍ ማድረግ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡

በሌላ በኩል የዋጋ ንረትን ከነበረበት ተርኒንግ ፖይንት ተነስቶ በሦስት በመቶ ለመጨመር አንድ የፖሊሲ መሣሪያ (የማዕከላዊ ባንክን የወለድ ምጣኔ ፖሊሲ) ብቻ መጠቀም ካስፈለገ በ1.5 በመቶ ከፍ ማድረግ ነው፡፡ የግብር ተመን ፖሊሲ መሣሪያን ብቻ መጠቀም ካስፈለገ የግብር ተመንን በ15 በመቶ ከፍ ማድረግ፣ እንዲሁም የነዳጅ ዋጋን እንደ ፖሊሲ መሣሪያ በብቸኝነት መጠቀም ከፈለግን ዋጋውን በ30 በመቶ ከፍ ማድረግ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ በተመሳሳይ አሁን ያለውን 17 በመቶ የዋጋ ንረት ወደ ሁለት በመቶ የተረጋጋ የዋጋ ንረት ምጣኔ ለማውረድ በተናጠል ወይም በመተጋገዝ በምን ያህል ፐርሰንት የፖሊሲ ዕርምጃ ምጣኔ የዋጋ ንረትን በ15 በመቶ  መቀነስ ይቻላል የሚለውን አውቆ፣ የፖሊሲ ዕርምጃውን መውሰድ የሚቻል ይሆናል ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ፖሊሲ አውጪዎች የፖሊሲ ዕርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት የፖሊሲ መሣሪያዎቹን ለይቶ ማወቅ፣ የፖሊሲ መሣሪያው በማን እጅ እንደሚገኝ ማወቅ (ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ የፖሊሲ መሣሪያ በግል ሞኖፖሊስቶች እጅ ሊገባ ይችላል ምሳሌ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ፣ የወርቅ ዋጋ፣ የሪል ስቴት ዋጋ በግል ሞኖፖሊስቶች ሲዘወርና እንደ ሞኖፖሊ መሣሪያ አገልግሎት ላይ ሲውሉ የተስተዋለበት ጊዜ ነበር)፡፡ እና ምን ያህል ክብደት ወይም ኃይል እንዳላቸው ለክቶ ማወቅ ተገቢነት አለው፡፡ ይህ ከሆነ የዋጋ ንረትን በቀላሉ የሚፈለገው የዋጋ ንረት ምጣኔ ቁጥር ላይ ማሳረፍ ይቻላል ማለት ነው፡፡

ምሳሌ ወስደን ለማየት እንሞክር፡፡ የአፈር ማዳበሪያ እንደ አንድ የፖሊሲ መሣሪያ አድርገን እንውሰድ፡፡ የአንድ ኩንታል ዋጋ 5,000 ብር ነው ብለን ብንወስድ፣ ገበሬው እስከ ስንት ብር የመግዛት አቅም ይኖረዋል የሚለውን ማወቅ ተገቢነት አለው፡፡ የገበሬው የመግዛት አቅም ደግሞ የሚወሰነው በሸማቾች ጤፍ የመግዛት አቅም ላይ ነው፡፡ የሸማቾችን የመግዛት አቅም ለማወቅ ደግሞ የጤፍ ዋጋ ተርኒንግ ፖይንቱን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ እንበልና አሁን ያለው የጤፍ ዋጋ በኩንታል 15,000 ብር ነው ብለን ብናስብና የሸማቾች የመግዛት አቅም ወይም ተርኒንግ ፖይንት 25,000 ብር ነው ቢሆን፣ የጤፍ ዋጋ እስከ 67 በመቶ የመጨመር አቅም አለው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ካወቅን በተጨባጭ ምን እናድርግ? ማድረግ ያለብን ተርኒንግ ፖይንቱን ወደ 15,000 ብር ማውረድ ነው፡፡ ይህን እንዴት አድርገን እናውርድ? ይህን ለመወሰን በተርኒንግ ፖይንትና አሁን ባለው የጤፍ ዋጋ መካከል ያለውን ልዩነት 10,000 ብር በማቅለጥ (Meltdown) በማድረግ አልያም ደግሞ ሌላ ልማት ላይ በማዋል የጤፍ ዋጋ ባለበት 15,000 ብር እንዲቀጥል ማድረግ ነው፡፡

 በተመሳሳይ የጤፍ ዋጋን ተርኒንግ ፖይንት ከነበረበት 25,000 ብር በ150 በመቶ በማውረድ ዋጋውን 10,000 ብር ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህንንም ለማድረግ መጀመሪያ የጤፍ ዋጋ ተርኒንግ ፖይንት ላይ የነበረውን የጤፍ ዋጋ 25,000 ብር ወደ 10,000 ብር ዝቅ ለማድረግ ልዩነቱን 15,000 ብር ማምከን ወይም ደግሞ ወደ ልማት መቀየር ያስፈልጋል፡፡ ይህም ማለት ለሌላ ምርትና ምርታማነት ወይም የመዋዕለ ንዋይ ማስፋፊያ ሥራ ላይ ማዋል፣ አልያም ደግሞ ይህን ገንዘብ ከገበያ ማስወገድ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ወይም የጤፍን ዋጋ ከተርኒንግ ፖይንት ዋጋ 25,000 ብር ወደ 10,000 ብር ለማውረድ ደግሞ የአየር ትራንስፖርት ቃላትን (Avatione Terms) የሚባሉትንና የአውሮፕላን አስተራረፍ (Landing Mechanism) በማስመሰል የዋጋ ንረትን ለማውረድ የሚጠቅሙንን ዘዴዎች መጠቀም ግድ ይለናል፡፡  እነዚህንም ዘዴዎች ለስላሳ ማረፊያ (Soft Landing)፣ ጠንካራ ማረፊያ (Hard Landing)፣ የተጨናነቀ ማረፊያ (Bumpy Landing)፣ ያለ ምንም ማረፊያ (No Landing) በመባል የሚታወቁ ሲሆን፣ የዋጋ ንረትን በጥንቃቄ ለማውረድ ዓይነተኛ ዘዴዎች ናቸው፡፡   

በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ ወስጥ በተርኒንግ ፖይንት አጠቃላይ ዋጋ (General Price Level) እና በተጨባጭ ያለው ዋጋ (Actual price level) መካከል ያለው ልዩነት በአብዛኛው በኣማካይ በ1,000,000,000,000 ብር እና በ5,000,000,000,000 ብር መካከል በመጫወት የዋጋ ንረት ከፍ እንዲል ሲያደርግ፣ በተቃራኒው ደግሞ አልፎ ልፎ ከዜሮ በታች እስከ -1,000,000,000,000 ብር ዝቅ በማለት የገንዘብ ተቋማትን ኢንቨስትመትንና የንግድ ተቋማትን ሲያናውጥና ሲያደናግጥ በስፋት ይታያል፡፡ በመሆኑም ይህ ሁኔታ በመፈጠሩ ምክንያት ኢኮኖሚው በሚንቀሳቀስበት ጊዜ በችንጋውና በጊሩ መካከል ያለው ግንኙነት በጣም በመላላት የኢኮኖሚውን ዕድገት ትርጉም አልባ አድርጎ ዜጎችን ግራ ሲጋባ የሚታይ ሲሆን፣  በሌላ በኩል ደግሞ በጣም ጠብቆ ኢኮኖሚው ላይ የመውደቅ ሥጋትን ሲደቅን ይታያል፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያት ደግሞ የፖሊሲ ዕርምጃዎች የሚወሰዱት በግመታ (Error And Trial) በመሆኑ ነው፡፡

በመሆኑም ይህን ችግር በማስተካከልና የተርኒንግ ፖይንቱን መጠን ኖርማል ላይ አድርጎ ኢኮኖሚውን በሙሉ አቅም ለማንቀሳቀስ፣ ብሎም የኢትዮጵያን ትንሳዔ ለማብሰርና ለመከወን የኢትዮጵያውያን ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡ ይህንንም ለማድረግ ለኢኮኖሚ ፖሊሲ ልኬት መሠረት የሆነውን የዋጋ ንረት ወይም ኢኮኖሚ ዕድገት አልያም ደግሞ ውድቀት መሠረት የሆነውን ተርኒንግ ፖይንት ትክክለኛ መጠን ማወቅ መሠረታዊ መሆኑን መረዳት አስፈላጊ ጉዳይ ሲሆን፣ የፖሊሲ አውጪዎች ያለዚህ ግንዛቤና መረዳት የቱንም ያህል የፖሊሲ ዕርምጃ ቢወስዱ የአንድን ያላደገ አገር ኢኮኖሚ በመሠረታዊነት ሊቀይሩ እንደማይችሉና ሰላምን፣ ዕድገትንና ብልፅግናን ማረጋገጥ እንደማይችሉ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ይህ ባለመታወቁ ምክንያትም በኢትዮጵያውያን ዘንድ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፍጥነት የማሳደግና ትንሳዔዋን የማምጣት ሐሳብ ሕልም መስሎ እንዲታያቸው አድርጎ የቆየ ቢሆንም፣ አሁን ግን ወደ እውነታ መቀየር ያለበት ጉዳይ ሊሆን ይገባል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ፖሊሲ አውጪዎች ፈተና ያለው የኢኮኖሚውን ተርኒንግ ፖይንት ልኬት አለመገንዘብና አለመረዳት ጋር ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህን ተርኒንግ ፖይንት ለይቶ ማወቅና ቁጥሩን ኢኮኖሚው የሚፈልገው ቦታ ላይ ማስቀመጥ በጣም ተገቢነት ያለው ተግባር ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ኢኮኖሚው ጤናማ ሆኖ እንዲጓዝ ይረዳዋል፡፡ የችንጋውን ርዝመት በትክክል ተለክቶ ጊሩ ላይ ሲገጠም ኢኮኖሚው የሰመረ ጉዞ ያደርጋል ማለት ነው፡፡

 ይህ የሰመረ ጉዞ ደግሞ የኢትዮጵያውያንን አካላዊ፡ አዕምሮአዊና መንፈሳዊ ደኅንነትን የሚያጎለብትና የሚያድስ ይሆናል፡፡ የዚህ ውጤት ደግሞ የዜጎችን ወንድማማችነት፣ ፍቅር፣ ትህትና፣ አንድነት፣ ሰላም፣ ዕድገትና ብልፅግናን በተጨባጭ የሚያመጣ ይሆናል፡፡ ይህ ማለት የኢትዮጵያ ትንሳዔ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ደግሞ እዚህ ደረጃ ላይ ስትደርስ ዩቶፕያ ትሆናለች፡፡ ኢትዮጵያ ዩቶፕያ ሆነች ማለት ደግሞ በዓለም ላይ የታወቀችና የገነነች አገር፣ ለብዙኃን መጠጊያና መጠለያ በመሆን የዓለም ምድረ ገነት ቦታ ትሆናለች ማለት ነው፡፡ ለዚህ መሳካት ደግሞ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያን አንድ እንዳደረገን የዓድዋ ጦርነትና የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሁሉ፣ የትንሳዔው መበሰርና መከወን አንድ ሊያደርገን ይገባል፡፡ አዎ በእርግጥ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያውያንን አንድ ሊያደርገን የሚገባው ሕልም ነው እየተባለ  ሲነገር ይሰማል፡፡ ነገር ግን እስከ ዛሬ ብዙ ስናልም ቆይተናል፣ አሁን ማድረግ ያለብን ሕልማችንን መፈጸምና መኖር ስለሆነ የሕልምን አንድነት ወደ ተግባር ቀይረን በትንሳዔው አንድ ልንሆን ይገባል የሚል መረዳት መኖሩ ጥሩ ይሆናል እላለሁ፡፡    

ከአዘጋጁ፡– ጸሐፊው የባንክና የኢኮኖሚ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው getaneh25@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡