የ32 ዓመቷ እናት ከልጆቿ ጋር

ከ 4 ሰአት በፊት

በሰሜን ናይጄሪያ አንድ እናት ቆዳው የተቃጠለውን እና ፊቱ እና እግሩ የተለያየ ቀለም ያለውን የሁለት ዓመት ልጇን እቅፍ አድርጋ ብስጭት ስትል ትታያለች።

የ32 ዓመቷ እናት በቤተሰቦቿ ጫና ቆዳን የሚያነጡ ምርቶችን ለስድስቱም ልጆቿ ተጠቅማለች። ውጤቱ ግን ከፍተኛ ፀፀት ውስጥ ከትቷታል።

የቤተሰቦቿን ማንነት ለመጠበቅ ስሟ የተቀየረው ፋጢማ እንደምትለው አንዷ ሴት ልጇ ከቤት ስትወጣ ጠባሳዋን ለመደበቅ ፊቷን ትሸፍናለች።

ሌላኛዋ ልጇ ደግሞ የበለጠ ጠቁራለች። በዐይኖቿ ዙሪያም ገርጥታለች።

ሦስተኛ ልጇ ነጣ ያለ ጠባሳ በከንፈሮቿ እን ጉልበቷ ላይ ይገኛል።

ህፃኑ ልጇ አሁንም ጠበሳ ያለው ሲሆን ቆዳው ለመዳን ረጅም ጊዜ ወስዷል።

“እህቴ ቆዳቸው ቀላ ያሉ ልጆችን ነው የወለደችው። ነገር ግን የእኔ ልጆች ጠቆር ያለ ቆዳ ያላቸው ናቸው። በመልካቸው ምክንያት እናቴ ከእኔ ልጆች ይልቅ የእህቴን ልጆች ስታቀርባቸው ታዘብኩ። ይህም በጣም ስሜቴን ጎዳው” ትላለች ፋጢማ።

ካለ ሐኪም ትዕዛዝ ኮኖ ከተማ ከሚገኝ የገበያ ማዕከል የገዛችውን ክሬም እንደተጠቀመች ትናገራለች።

በመጀመሪያ ለውጥ ያመጣ ይመስላል። በወቅቱ ከሁለት ዓመት እስከ 16 ዓመት እድሜ የነበራቸውን የፋጢማ ልጆች አያታቸው መቅረብ ጀመረች።

ነገር ግን ውሎ ሳያድር ቃጠሎ እና ጠባሳዎች ወጣባቸው።

ከፋጢማ ልጆች አንዷ በተጠቀመችው የቆዳ ማንጫ ክሬም ምክንያት ከንፈሯ ላይ ጠባሳ ወጥቷል
የምስሉ መግለጫ,ከፋጢማ ልጆች አንዷ በተጠቀመችው የቆዳ ማንጫ ክሬም ምክንያት ከንፈሯ ላይ ጠባሳ ወጥቷል

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

ቆዳ ማቅላት (ማንጣት) ለውበት በሚል በመላው የዓለም ክፍል ጥቅም ላይ ቢውልም ሰፊ ባህላዊ መሰረት ግን አለው።

የናይጄሪያ ሴቶች የቆዳ ማንጫ ምርቶችን በመጠቀም የሚደርስባቸው የለም።

እንደ ዓለም የጤና ድርጅት መረጃ 77 በመቶዎቹ የቆዳ ማቅያ ምርቶችን ይጠቀማሉ።

በኮንጎ ብራዛቪል ይህ አሀዝ 66 በመቶ፣ በሰኔጋል 50 በመቶ እንዲሁም በጋና 39 በመቶ ነው።

የሚጠቀሟቸው ክሬሞች የሚሰሩባቸው ንጥረ ነገሮች መጠናቸው ከፍተኛ ሲሆን ጎጂ እና በብዙ አገራት በሐኪም ትዕዛዝ የሚሰጡ ናቸው።

የተመረዘ ብረት፣ ሜርኩሪ እና አሲድ የመሰሉ ሌሎች ንጥረ ነገሮችም አንዳንዴ ይይዛሉ።

የቆዳ በሽታ፣ ቡግር እና የቆዳ ቀለም መቀየር ሊከሰቱ የሚችሉ ውጤቶች ናቸው። ከዚህ ባለፈም የቆዳ ማቃጠል እክል፣ የሜርኩሪ መመረዝ እና የኩላሊት ጉዳትም ሊያስከትል ይችላል።

ቆዳ መሳሳትም ሊደርስ የሚችል ሲሆን ቁስሉ ለመዳን ረጅም ጊዜ ሊወስድ እና ኢንፌክሽን ሊፈጥር እንደሚችል የዓለም የጤና ድርጅት ይገልፃል።

ሁኔታው ከመክፋቱ የተነሳ የናይጄሪያ ምግብ እና መድኃኒት አስተዳደር እና ቁጥጥር እ.አ.አ በ2023 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል።

እንደ ፋጢማ ሁሉ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለማንጣት ምርቶችን መጠቀም እየተለመደ መጥቷል።

በናይጄሪያ የቆዳ ክሊኒክ ባለቤት የሆኑት ዶ/ር ዘይነብ በሽር ዩ “ብዙ ሰዎች ቀላ ያለን ቆዳ ከቁንጅና እና ከሀብት ጋር ያያይዙታል። እናቶች ልጆቻቸውን ከአድልዎ ለመጠበቅ ከልጅነታቸው ጀምሮ ቆዳቸውን ያቀላሉ” ይላሉ።

80 በመቶ የምታውቃቸው ሴቶች የልጆቻቸውን ቆዳ አንጥተዋል አሊያም ለማንጣት ውጥን ይዘዋል ብላ ይገምታሉ።

አንዳንዶቹ እነሱም በልጅነታቸው ቆዳቸው እንዲነጣ በመደረጉ ልምዱን እያስቀጠሉ ነው ይላሉ።

የቆዳ ማንጫ ክሬሞችን የተጠቀሙ የአንዳንድ ሰዎች እጆች የእፅ ሱሰኞች ላይ የሚወጡ ምልክቶችን ይመስላሉ
የምስሉ መግለጫ,የቆዳ ማንጫ ክሬሞችን የተጠቀሙ የአንዳንድ ሰዎች እጆች የእፅ ሱሰኞች ላይ የሚወጡ ምልክቶችን ይመስላሉ

በናይጄሪያ አንድ ሰው የቆዳ ማንጫ ምርቶችን መጠቀሙን እና አለመጠቀሙን ለማወቅ በጣም የተለመደው መንገድ የጣት መገጣጠሚያዎች ጥቁረት ማየት ነው። ሌላው የሰውነት ክፍል እጅ እና እግር የሚቀላ ሲሆን ጉልበት ግን እንደጠቆረ ይቀራል።

ነገር ግን አጫሾች እና አደገኛ እፅ ተጠቃሚዎች እጆቻቸው ላይ ጥቁር ምልክት ይታይባቸዋል።

የቆዳ ማንጫ የተጠቀሙ አንዳንድ ሰዎች በስህተት የዚህ ቡድን አባል ተደርገው ይታያሉ።

የፋጢማ የ14 ዓመት እና የ16 ዓመት ልጆቿም የገጠማቸው ይኸው ነው።

“ከማኅበረሰቡ አድልኦ ገጠማቸው። ሁሉም ጣቱን በመቀሰር የእፅ ሱሰኞች ብለው ይጠሯቸዋል። ይህ በጣም ተፅዕኖ አሳድሮባቸዋል” ትላለች።

ወንዶች እፅ ሊወስዱ ከሚችሉ ሴቶች ጋር መታየት ባለመፈለጋቸው ሁለቱም ልጆቿ እጮኛ ሊሆኗቸው የሚችሉ ወንዶች ተለይተዋቸዋል።

በካኖ ታዋቂ ገበያ ራሳቸውን ቀማሪ ብለው የሚጠሩ ሰዎች ከባዶ ነገር የቆዳ ማንጫ ክሬሞችን ይሰራሉ።

በገበያው አንድ ረድፍ ሙሉ ሱቆች በሺዎች የሚቆጠሩ እነዚህን ክሬሞች ይሸጣሉ።

አብዛኞቹ የቆዳ ማንጫ ክሬሞች ለልጆች መሆናቸውን የሚያሳይ መለያ የተለጠፈባቸው ናቸው።

በዚህ ገበያ አንድ እናት “ምንም እንኳ እጄ የተለያየ ቀለም ቢኖረውም ልጆቼ ቀላ ያለ ቆዳ እንዲኖራቸው ክሬም ለመግዛት ነው የመጣሁት። እጄ እንደዚህ የሆነው የተሳሳተ ክሬም በመጠቀሜ ነው ብዬ አምናለሁ። ልጆቼ ላይ ምንም አይፈጠርም” ትላለች።

አንድ ሻጭ በበኩሉ አብዛኞቹ ደንበኞቹ ህፃናት ልጆቻቸው ፈካ እንዲሉ ወይንም እንዲቀሉ ክሬም የሚገዙ ናቸው ይላል።

አብዛኞቹም የተፈቀደውን መጠን የሚያውቁ አይመስሉም።

የናይጄሪያ ምግብ እና መድኃኒት አስተዳደር እና ቁጥጥር ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ሌነርድ ኦሞካፓሪኦላ ስለ አደጋው ለማስገንዘብ እየተሞከረ ነው ይላሉ።

የቆዳ ማንጫ ንጥረ ነገሮች ወደ አገሪቱ ከመግባታቸው በፊት ድንበር ላይ ለመያዝ እየሞከርን ነውም ብለዋል።

ሆኖም ሕግ አስከባሪዎች እነዚህን ንጥረ ነገሮች ለመለየት እንደሚቸገሩ ተናግረዋል።

ፋጢማ በተለይም የልጆቿ ጠባሳዎች የማይጠፉ ከሆነ የሰራችው ስራ ለዘላለም እንቅልፍ እንደሚነሳት ትናገራለች።

ሌሎች ወላጆችም እንደ እርሷ አይነት ስህተት እንዳይሰሩ ለማስተማር ቁርጠኛ ናት።

“ምንም እንኳ መጠቀም ባቆምም የጎንዮሽ ጉዳቱ አሁንም አለ። ሌሎች ወላጆች የእኔን ሁኔታ ተምሳሌት እንዲያደርጉ እለምናለሁ” ትላለች።

ቀማሪዎች በደንበኞቻቸው ጥያቄ መሰረት አደገኛ ንጥረ ነገሮችን በመቀላቀል ቆዳ ማንጫ ክሬሞችን ያዘጋጃሉ
የምስሉ መግለጫ,ቀማሪዎች በደንበኞቻቸው ጥያቄ መሰረት አደገኛ ንጥረ ነገሮችን በመቀላቀል ቆዳ ማንጫ ክሬሞችን ያዘጋጃሉ